የፋሲል ከነማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ሲዳሰስ

 

በዛሬው የክለቦች የመጀመሪያው ዙር እይታችን አፄዎቹ (ፋሲል ከነማ) በመጀመሪያው ዙር ምን ይመስል ነበር የሚለው እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

የሊጉ የመጀመሪያ ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ የተለያዩ ክለቦችን የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ምን ይመስላል የሚለውን ነገር እያነሳን ቆይተናል በዛሬው ፅሁፋችን ደግሞ የአምናው የዋንጫ ተፍካካሪ ፋሲል ከነማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞው ምን ይመስል ነበር የሚለውን እንመለከታለን።

የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ እና የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ተፎካካሪ ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲገኙ እስካሁንም በሊጉ በ15ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 45ነጥቦች 26ቱን ብቻ በመሰብሰብ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2ነጥቦች ብቻ በማነስ 2ኛደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እየተመሩ በሊጉ ጥሩ ግስጋሴ እያደረጉ የሚገኙት አፄዎቹ በሜዳቸው ሀያልነታቸውን እያሳዩ ለየትኛውም ተጋጣሚ ቡድን እጅ ሳይሰጡ ቆይተዋል። በሜዳቸው ድንቅ እንቅሰቃሴ የሚያደርጉት ፋሲሎች የሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ የመሀል ሜዳ ድንቅ ጥምረት ተጠቃሽ ነው ከዚህ በተጨማሪም የአይደክሜው ሽመክት ጉግሳ፣ በዘንድሮው የውድድር አመት ድንቅ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ብቅ ያለው ሙጂብ ቃሲም እና ኢዙ አዙካ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ላይ ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መምጣት ለፋሲል ተጨማሪ ጥንካሬ ተሰጥቶታል። ከዚህ ባሻገር ግን የግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኬ ድንቅ አቋም ላይ መገኘት አፄዎቹ ከመሪዎቹ ጎራ እንዲሰለፉ አስችሏቸዋል። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ጥንካሬ በሜዳቸው ብቻ የተስተዋለ እንጂ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ እጅግ ደካማ የሚባል ጉዞን እያደረጉ ነው የሚገኙት።

አፄዎቹ ካደረጓቸው 15 ጨዋታዎች 7ቱን በሜዳቸው ያከናወኑ ሲሆን ከነዚህ መካከልም 7ቱን በድል በመወጣት በአንዱ ብቻ አቻ ተለያይቶ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግዱ የመጀመሪያውን ዙር ማጠናቀቅ ችለዋል። ፋሲል ከነማ በሜዳው ባደረጓቸው 7 ጨዋታዎች 17ግቦችን ተጋጣሚያቸው ላይ ማስቆጠር ሲችሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በጋራ ያስቆጠሩባቸው 3ግቦች ደግሞ በሜዳቸው ያስተናገዷቸው የግብ ብዛት ናቸው። ይህም ማለት በሜዳቸው በአማካይ 2.42 ግቦችን በየጨዋታው ሲያስቆጥሩ በአንፃሩ 0.43 ግብ በየጨዋታው ይቆጠርባቸዋል ማለት ነው። ውጤቱ እንደሚያመለክተው አፄዎቹ በሜዳቸው ጠንካራ መሆናቸውን ያመላክታል። በሁለተኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ ያስቆጠሩት 5ግብ በሊጉ ያስቆጠሩት ከፍተኛ የግብ ብዛት ሲሆን በ14ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የተቆጠረባቸው 2ግቦች በሜዳቸው ያስተናገዱት ከፍተኛ የግብ መጠን ነው።

ፋሲል ከነማዎች ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ እጅግ ደካማ የሚባል ጉዞ ከሚያደርጉ ቡድኖች ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን ካደረጓቸው 8የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ማሸነፋቸው ለዚህ ጉልህ ማሳያ ነው። ከቀሪዎቹ 7ጨዋታዎች በ3ቱ ተሸንፈው በ4ቱ ደግሞ አቻ መለያየት ችለዋል። በነዚህ 8ጨዋታዎች 8ግቦች አስቆጥረው በአንፃሩ 10 ግቦች አስተናግደዋል። ይህም ማለት ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ በአማካይ በየጨዋታው 1ግብ ሲያስቆጥሩ በአማካይ 1.25 ግቦች ይቆጠሩባቸዋል ማለት ነው። አፄዎቹ በ5ኛው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ተጉዘው ሰበታ ከተማን በገጠሙበት እና 3አቻ በተጠናቀቀው ጨዋታ ያስቆጠሯቸው 3ግቦች ከሜዳቸው ውጪ ያስቆጠሩት ከፍተኛ ግብ ሲሆን በተመሳሳይ ጨዋታ እና በ15ኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ 3-2 ሲሸነፉ የተቆጠረባቸው 3ግቦች ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ያስተናገዷቸው በርካታ ግቦች ናቸው።

ሊጉ በአጠቃላይ ከ15ጨዋታዎች በ7ቱ ድል ሲቀናቸው በ5ቱ ጨዋታዎች አቻ ወጥተው የተቀሩትን 3ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። በነዚህ ጨዋታዎች 25ግቦች አስቆጥረው 13ግቦች ደግሞ ተቆጥረውባቸው 26ነጥቦችን ሰብስበው ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል። ቡድኑ ከ15ቱ ጨዋታዎች በ4ቱ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡ ሲሆን በ8ጨዋታዎች ደግሞ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል።

የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን

ቡድኑ ግብ ማስቆጠር የማይቸገር እና ጠንካራ የአጥቂ መስመር እንዳላቸው የሚታይ ሲሆን የተከላካይ ክፍላቸው ከሜዳ ውጪ ሲጓዙ በርካታ ግብ ማስተናገዳቸው እንደ ድክመት ሊታይ የሚችል ነው።

በሁለተኛው ዙር የሚጠበቅባቸው

ምንም እንኳን ከአጨዋወት ጋር መልካም የሚባል ቢሆንም ግን የ አማካይ እና ተከላካይ ቦታ ላይ ለቡዱኑ ጥንካሬ አዲስ ሃይል ሊስጡ የሚችሉ ተጫዎቶች ቢያስፈርሙ ባለፈው የውድድር ዓመት ያጡትን የሊጉን ዋንጫ ማንሳት አቅም እንዳላቸው አያጠራጥርም። በተጨማሪም የተከላካይ ክፍላቸውን አስተካክለው የሚመጡ ከሆነ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website