የጨዋታ ዘገባ | ፋሲል ከነማ በበዛብህ መላዮ ብቸኛ ግብ በግዜያውነት የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል

የሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ የመጀመርያ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን አስተናግዶ በጠባብ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ችሏል፡፡

በተለመደው በአጼዎቹ በኩል የታየው ውብ የደጋፊዎች ዝማሬ እና የስታዲየም ድባብ የጀመረው ጨዋታው በአዳማ ከተማዎች በኩል በጉዳት ወሳኝ አጥቂያቸውን ዳዋ ሆቴሳን ሳይዙ ነበር የገቡት፡፡

በመጀመሪያው በሁለቱም ቡድኖች አሪፍ የጨዋታ ፍሰት ማለት በሚቻል መልኩ ኳስ መቆጣጠር ችለዋል ቢሆንም አልበገር ያለውን የአፄዎቹን የፊት መስመር የመልሶ ማጥቃት ማስቆም አልቻሉም፡፡

በዚህም ገና እንደተጀመረ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው የተሻገረለትን ኳስ የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሙጅብ ቃሲም ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

በአዳማ ከተማ በኩል ቡልቻ ከበረኛው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ የሳተው ኳስ ተጠቃሽ ነው።12ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች በመስመር በኩል አንድ ሁለት ብለው ተጫውተው አምሳሉ ጥላሁን ያሻማውን ኳስ በእለቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የዋለው በዛብህ መለዮ በሚገርም ሁኔታ አስቆጥሯል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ፋሲል ከነማዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በተገኘው አጋጣሚ ወደ ጎል ሲሞክሩ ተስተውለዋል :: ከዚህም ውስጥ በ32ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከ ሀብታው ተከስተ(ጎላ) ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ተጠቃሽ ነው።የመጀመሪያውም አጋማሽ በፋሲል ከነማዎች መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ብዙም ማራኪ ባልነበረው እና ብዙ ሽኩቻ በበዛበት በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል ሙከራ አልታየበትም ነበር፡፡ይልቁንስ በየጊዜው ጨዋታው ባላስፈላጊ ጥፋት ሲቆም ነበር ይህም ተመልካችን ሲያሰለች ነበር።ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤት ተጠናቋል።