የጨዋታ ዘገባ | ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት 5ጨዋታዎች ዛሬ የተደረጉ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ያስተናገደበት ጨዋታ ተጠቃሹ ነው። በዚህ ጨዋታም ኢትዮጵያ ቡና ከ5ጨዋታዎች በኋላ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ባማረ የድጋፍ ዝማሬ እና ጭፈራ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ ለማስተናገድ 6ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀበት።

6ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው እዮብ አለማየሁ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ፀጋዬ አበራ አሻግሮት ተስፋዬ አለባቸው (ቆቦ) በቀጥታ ሞክሮት የግቡን ቋሚ ታካ ለጥቂት ወጥታለች። ከዚህች ሙከራ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሱን ከኋላ መስመር በማስጀመር ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ 13ኛው ደቂቃ ላይ ከታፈሰ ሰለሞን በግሩም ሁኔታ የተቀበለውን ኳስ አለምአንተ ካሳ ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል።

 

በርካታ ግጭቶችና ጥፋቶች የተስተዋሉበት ጨዋታ ኳስ ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጡበት ታይቷል። 22ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ የሰራውን ስህተት ባዬ ገዛኸኝ ቢያገኘውም ኳስ በመርዘሙ ምክንያት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከ2ደቂቃዎች በኋላ 24ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ ከክንፍ ያሻገረለትን ኳስ ፍ/የሱስ ተ/ብርሀን ሞክሮት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል።

ጫና መፍጠር የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ታይተዋል። በዚህም 27ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አስራት ቱንጆ በቀጥታ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ይዞታል።

ወደ ኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ 33ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ አለባቸው በግሩም ሁኔታ ያሾለከለትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በድንቅ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮት እንግዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። ከግቧ መቆጠር 2ደቂቃዎች በኋላ 39ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻ ተከላካዮችን ስህተት ተከትሎ የተገኘውን ኳስ አቡበከር ናስር ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረው ሲባል በግቡ አግዳሚ ወደ ወጥቶበታል።

ግቡን ካስተናገዱ በኋላ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በጣም ወደፊት በመጫን ሲጫወቱ እንግዳዎቹ የጦና ንቦች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ በማፈግፈግ ረጃጅም ኳሶችን ለባዬ ገዛኸኝ በመጣል የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪው 2ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አለምአንተ ካሳ ያሻገረለትን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ መቆጣጠር ሳይችል በመቅረቱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በዚህም የውጤት ለውጥ ሳይኖር የመጀመሪያው አጋማሽ በወላይታ ድቻ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በኢትዮጵያ ቡና የበላይነት ሲደረግ ለመቁጠር የሚታክቱ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በዚህኛው አጋማሽም የመጀመሪያውን ሙከራ ለማድረግ 2ደቂቃዎችን ብቻ ነበር የጠበቁት። 47ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ መኮንን ጥሩ አቋቋም ላይ ሆኖ የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ወጥቷል።

ኳስን በመቆጣጠር ሙሉ ብልጫ የወሰዱት ባለሜዳዎቹ ሙሉ የጨዋታ ጊዜውን ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል ላይ የነበሩ ሲሆን የጦና ንቦቹን ተከላካዮች ሲያስጨንቁ ውለዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር ከግቡ 2ሜትር ርቀት ላይ ያገኘውን ኳስ አገባው ሲባል የሳተው ኳስ በኢትዮጵያ ቡና በኩል እጅግ የሚያስቆጭ ነበር።

ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ቡናማዎቹ 54ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አቡበከር ናስር በቀጥታ መቶት ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህች ሙከራ 6ደቂቃ በኋላም 60ኛው ደቂቃ ላይ አለምአንተ ካሳ ከቅጣት ምት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። 64ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ለታፈሰ ሰለሞን ሰጥቶት የሞከረውን ኳስ ወደውጭ ወጥቶበታል።

የኢትዮጵያ ቡና ተደጋጋሚ ሙከራ እና ጫና ፈጥሮ መጫወት ውጤት አስገኝቶ 66ኛው ደቂቃ ላይ ከሚኪያስ መኮንን የተቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮት ቡናማዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ቡድናቸው ሁለተኛ ግብ እንዲያስቆጥር ከፍተኛ ድጋፍ ማሳየት ችለዋል። በጨዋታው 75ኛ ደቂቃ ላይ ሚኪያስ መኮንን ለታፈሰ ሰለሞን የሰጠውን ኳስ ታፈሰ ሞክሮት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል።

ከዚህ ሙከራ በኋላ ለማመን የሚከብድ ነገር ሜዳው ላይ ሲፈጠር ኢትዮጵያ ቡናዎች በ2ደቂቃ ውስጥ እጅግ ያለቁላቸውን 3ኳሶች ማመን በሚከብድ ሁኔታ ከግቡ አፍ ላይ ሲስቱት ተስተውለዋል። አቡበከር ናስር፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ሚኪያስ መኮንን ያበከኗቸው ኳሶች ደጋፊውን ቁጭ ብድግ ያደረጉ ነበሩ።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት 80ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አህመድ ረሺድ (ሽሪላው) በቀኝ ክንፍ እየገፋ ሄዶ ያሻማውን ኳስ የወላይታ ድቻው ውብሸት ዓለማየሁ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠሩ ባለሜዳዎቹ ከኋላ ተነስተው መሪ መሆን ችለዋል። ከ3ደቂቃዎች በኋላም በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው አጥቂው አቡበከር ናስር 3ኛ ግብ አክሎ ቡናማዎቹን ባለድል ማድረግ ችሏል።

ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተነሳ ፀብ በርካታ ደጋፊዎች ተጎድተው የመሮጫ መም (ትራክ) ላይ የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸዋል። በሰላም ረገድ ካለፉት ዓመታት አንፃር ሲታይ የዘንድሮው ውድድር የተሻለ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚታዩ የሰላም መደፍረሶች መታረም እንዳለባቸው እና የሊግ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር አፅንኦት ሰጥተውት መሰራት እንዳለበት ሀትሪክ ስፖርት ታምናለች።
📸#NathanimPhoto

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website