የጨዋታ ዘገባ | ኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

 

የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግንቷል።

ባለሜዳዎቹ ከባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው የአንድ ተጫዋች ላይ ለውጥ በማድረግ አቤል ከበደን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ሲመልስ ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ኤፍሬም ዘካርያስ፣ አዳነ ግርማ እና አህመድ ሁሴን ወደ በቋሚ አሰላለፍ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


ኢትዮጵያ ቡና ከወራጅ ቀጠናው የሚላቀቅበት በጥሩ መነቃቃት ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከተከታታይ አራተኛ ያለመሸነፍ ጨዋታውን ለማስቀጠል ተጠባቂ እንዲሆን ያደረገው ይህ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 10ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለመደው አጨዋወታቸው ከራሳቸው የግብ ክልል ጀምሮ ኳስ መስርቶ በመውጣት ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ፣ ክትፎዎቹ በበኩላቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጨወት ሞክረዋል። ጥቃት በመሰንዘር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች 3ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ሴቾ በራሱ ጥረት አግኝቶ የሞከረውን ኳስ የቡና ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውታል። ከሶስት ደቂቃ በኋላ አሥራት ቱንጆ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ሳይደርስበት ቀርቶ ያመለጠው ኳስ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በጣም የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። ቀስ በቀስ ወደ ወደ ጨዋታ መስመር የገቡት እንግዳዎቹ መሪ የሆኑበትን ግብ አግንተዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ሴቾ በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ አህመድ ሁሴን በተረጋጋ ሁኔታ ወደግብነት ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ለቀጣዮቹ 5ደቂቃዎች ወልቂጤ ከተማዎች ጫናን ፈጥረው መጫወት ችለዋል።


የተወሰደባቸውን ብልጫ ወደ ራሳቸው መልሰው ማስገባት የቻሉት ቡናማዎቹ 18ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ፈቱዲን ጀማል መቶት በተከላካዮች ተደርባ የወጣችበት ጥሩ የምትባል አጋጣሚ ስትሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ኤፍሬም ዘካርያስ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት በወልቂጤ በኩል ለግብ የተቃረበች ሙከራ ነበች። በጨዋታ ሂደት እንግዳዎቹ በአንድ ለአንድ አጨዋወት በመጫወት የኢትዮጵያ ቡናን ተጫዋቾች ኳስ እንዳይቀባበሉ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ወደኋላ በማፈግፈግ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ሲተገብሩ በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ፍፁም የበላይነትን ወስደው መጫወት ችለዋል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል በግምት ከ25ሜ ርቀት መትቶ የግቡ ብረት ለትማ የተመለሰችው ምናልባትም ኢትዮጵያ ቡናን አቻ ልታደርግ የምትችል ነበረች። ብልጫቸውን በሚገባ በመጠቀም ባለሜዳዎቹ 30ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ መኮንን ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግብ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ለሙሉ የወልቂጤ ከተማ የሜዳ ክልል ላይ በመጫወት ጫና መፍጠር ቢችልም አጋጣሚዎችን ከመፍጠር ወደኋላ ያላሉት ክትፎዎቹ በድጋሚ መሪ የሚያደርጋቸውን ኳስ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው በረከት አማረ ጋር ተገናኝቶ በድንቅ ሁኔታ አድኖበታል። በዚሁ የመጀመሪያው አጋማሽ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት አስበው ቢገቡም በተለይ ተጋጣሚያቸው ጫና በመፍጠር ምክንያት እንደልብ ኳሱን እንዳይጫወቱ አድርገዋቸዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ተሺታ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚቆራረጡ ኳሶች ሲስተዋልባቸው ነበር። በእንግዳዎቹ በኩል 65ኛው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ከማዕዘን ያሻሻገረውን ኳስ አህመድ ሁሴን በግንባር ገጭቶት ወደውጭ ስትወጣ። ከሁለት ደቂቃ በኋላ መልስ የሰጡት ባለሜዳዎቹ ሚኪያስ መኮንን በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ አቤል ከበደ መቶት ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቷል።

ወልቂጤ ከተማዎች ወደኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት በመጫወት 70ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወደ ውጭ የወጣችበት ጥቃት ለማስተናገድ ተገደዋል። ከዚህ በኋላ ጫና የፈጠሩት ክትፎዎቹ 79ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ለጫላ ተሺታ የሰጠውን ኳስ ጫላ ወደግብ ሞክሮት በረከት አማረ በቀላሉ ሲይዝበት ከፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ያሻገረለትን ኳስ ሚኪያስ መኮንን በመቀስ ምት ሞክሮት ይድነቃቸው ኪዳኔ በቀላሉ የያዘበት በቡናማዎቹ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።ኢትዮጵያ ቡና ወደ ድል ለመመለስ የተቸገረ ሲሆን በ14 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገዱት ወልቂጤ ከተማ በ18 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website