የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት 8ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ይርጋለም ስታዲየም ላይ ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ የሚገናኙ ይሆናል።

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ወጣ ገባ የሚል አቋም እያሳዩ የሚገኙ ሲሆን ወደ ወጥ አቋማቸው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በ12ኛው ሳምንት የተለያየ ውጤት የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡና በ11ኛው ሳምንት ወልዋሎ አ.ዩን በሜዳው አስተናግዶ 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ቢችልም፣ በቀጣዩ ጨዋታ ግን በአዲስ አበባ ስታዲየም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ6-2 ከባድ ሽንፈት አስተናግዷል። ይህም ሲዳማ ቡና በርካታ ግብ ማስቆጠር ቢችልም፣ በተቃራኒው በርካታ ግብ የሚያስተናግድ መሆኑን ያሳያል።

አዳማ ከተማ በበኩሉ ከሜዳ ውጪ ባሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እየታመሰም ቢሆን ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። የዳዋ ሁቴሳ፣ ከነዓን ማርክነህ እና የሱሌይማን ሰሚድ ጥሩ ብቃት ላይ መገኘት የተከላካይ ክፍሉ ለሚያፈሰው ሲዳማ ቡና ፈታኝ ነው የሚሆነው። በ11ኛው ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ሆኖም ግን አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጪ ወጥቶ ሲጫወት ያለው ደካማ ውጤት ለሲዳማ እፎይታ የሚሰጥ ነው።

በዚህም ምክንያት ሲዳማ ቡና ከደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት ለመውጣት እንዲሁም አዳማ ከተማ ደግሞ አሸናፊነቱን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በጉጉት እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

ዛሬ 9:00 ሲል ይርጋለም ስታዲየም ላይ በሚደረገው እና ፌደራል አርቢትር አክሊሉ ድጋፌ በሚመሩት ጨዋታ በሲዳማ ቡና በኩል ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እና ሚሊዮን ሰለሞን የማይሳተፉ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል የከነዓን ማርክነህ መግባት አጠራጣሪ ነው።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website