የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶስዬሽን በጎ ጅምር……

 

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የሁሉም ችግር ሆኗል፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግ ሁሉም በያለበት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡
ከተመሰረተ ከስምንት ወር የማይበልጥ እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶስዬሽን በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ባለው ዘመቻ ላይ ሰፊ ተሳትፎ ካደረጉ የስፖርት ማህበራት ውስጥ ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡ ማህበሩ የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል ለሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ከፕሪሚየር ሊግ ተጨዋቾች፤ ከአሰልጣኞችና ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስፖርት ኮምሽን ኮምሽነር ለአቶ ኤሊያስ ሽኩር ትላንት በማስረከብ ከመንግስት ጎን መቆሙን አሳይቷል፡፡


ስፖርት ማህበራዊ ሚናን ከመጫወት አኳያ ድርሻው ከፍተኛ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሲየሽን የስፖርት ማህበራትን ደርሻ አጉልቶ ባሳየ መልኩ በሰራው ስራ ከፍተኛ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለማህበሩ በጎ ስራ ታላቅ እውቅና ይሰጣል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

👉ማህበሩ እንዴት ተመሰረተ?

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋች ማህበር ስለመኖሩ በተደጋጋሚ ሲነገር ስንሰማ ቆይተናል፡፡ ሆኖም መሪው ማን እንደሆነና? ምን እየሰራ እንደነበር? ለብዙ አመታት አይታወቅም ነበር፡፡
ነገር ግን ባለፈው ነሃሴ ወር የተፈጠረው አንድ ያልተጠበቀ ነገር አሁን ስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ለመመስረቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ነሃሴ 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አመራሮችና ተወካዮች ቢሾፍቱ ላይ ባደረጉት ስብሰባ የፕሪሚየር ሊግ ተጨዋቾች የደሞዝ ጣሪያ ሲወጣ ከፍተኛው 50 ሺህ ብር ዝቅተኛው ደግሞ 5 ሺህ ብር እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ይህ ውሳኔ በርካታ የሃገራችንን ተጨዋቾች ቅር ያሰኘ በመሆኑ በጥቂት ተጨዋቾች ተነሳሽነት ውሳኔውን ለማስቀልበስ ጥረት መደረግ ተጀመረ፡፡ ምንም እንኳን ውሳኔውን ለማስቀልበስ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ቢሆንም ሳይሳካ ቀረ፡፡ ቢሆንም ግን ማህበሩ እንዲመሰረት መነሻ ምክንያት ሆኖ ከመንግስት እውቅና አግኝቶ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

👉የማህበሩ አቅም ምን ድረስ ነው?

ማህበራት በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ታላቅ ተፀኖ የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡ ይህንን በተለያዩ ግዜት በሃገራችን ተመልክተናል፡፡ ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ምክንያት በማድረግ በርካታ ማህበራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድጋፍ እየሰጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ጠተቃሽ ነው፡፡
ምንም እንኳን ማህበሩ ከተመሰረተ አጭር ግዜ ቢሆነውም የማህበሩ መኖር ጥቅሙ ለማህበሩ አባላት ብቻ ሳይሆን ለሃገርም እንደሆነ ከመንግስት ጎን በመቆም አሳይቷል፡፡ በርግጥ የማህበሩ ዋና አላማ የአባል ተጨዋቾቹች መብትና ጥቅም ማስከበር ቢሆንም በበጎ አድራጎት ስራ ላይ በመሰማራት የመንግስትን ሃገራዊ ጥሪ ተቀብሎ እገዛ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ያኮራል እንጂ ለምን የሚል ጥያቄ አያስነሳም፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ብዙ ተጨዋቾች በክለቦቻቸው በደል እንደሚደርስባቸውና ከኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ፍትህ አካላት መፍትሄ እንደማያገኙ አልያም ሂደቱ እጅግ እንደሚዘገይ ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ አባል ተጨዋቾች እንዲህ አይነትና ሌሎች ችግሮች በሚያጋጥማቸው ግዜ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ ካልሆነም ጉዳዩን በህግ አስይዞ መፍትሄ እስከማምጣት በመስራት ለተጨዋቾቹ መብት ሊሰራ ይችላል፡፡
ነገር ግን ተጨዋቹ ከማህበሩ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ግዴታውን ማወቅና ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ በአባልነት መመዝገብ፤ ከዚያም መዋጮውን በአግባቡ መክፈልና በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጡትን መብትና ግዴታዎችን ማወቅ ከተጨዋቾቹ የሚጠበቁ ቅድመ ሁኔታዎ ናቸው፡፡ ይህን ያላደረገ ተጨዋቾች ከማህበሩ የሚያገኘው ጥቅም አይኖርም፡፡

👉ነገሮችን በእርጋታ መመልከት

ማህበሩ በክለቦች ስምምነት የተወሰነውን የደሞዝ ጣሪያ ውሳኔ ለማስቀልበስ ከተጨዋቾች ጋር ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን አድርገው ሀሳብ ተለዋውጠዋል፡፡ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አልፎ አልፎ ስሜታዊነቶች ይታዩ ነበር፡፡ ይህ አይነቱ ስሜት ሊመንጭ የቻለው አንዳንዶቹ ካለመገንዘብ አንዳንዶቹ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ከውሳኔው በፊት የተጨዋቾቹ ሃሳብ መካተት ነበረበት በሚል ነው፡፡
ይህንን ምክንያት በማድረግ የደሞዝ ጣሪያ ገደብ መቀመጡ አግባብ አይደለም ስለዚህ ወሳኔው መስተካከል አለበት ይህ የማይሆን ከሆነ ፍትህ ለማግኘት ጉዳዩን ወደ ፊፋ፤ ወደ ካፍ ካልሆነም መደበኛ ፍርድ ቤት እንወስዳለን ማለታቸው ለአብነት ይጠቃሳል፡፡
በእነዚህ ተቋማት በኩል መፍትሄ የማይገኝ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩን ወደ CAS አለም አቀፍ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት እንወስዳለን ሲሉ ሰምተናል አንብበናል፡፡ ነገር ግን ፊፋና ካፍ ጣልቃ መግባት ይላሉ የሚለው ጉዳይ መታየት ነበረበት፡፡
እኔ ግን ሁለቱ የእግር ኳስ ተቋማት መግባት አይችሉም በሚል በዚህ ዙሪያ ከጥቂት ተጨዋቾች ጋር ብዙ ክርክር አድርጊያለሁ፡፡ በወቅቱ የእኔ መከራከሪያ የነበረው በመንግስት በጀት ፊፋም ሆነ ካፍ ጣልቃ ሊገቡ አይችሉም፡፡
ፊፋ ክለቦች የራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ደጋግሞ የሚሳስበው እንዲህ አይነት ተፅኖዎች ወይም ጣልቃ ገብነቶች እንደያይኖሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ፊፋ በመንግስት በጀት ጣልቃ የመግባት ስልጣን የለውምና የሚል ነበር፡፡ በዚህ ሃሳቤ የተስማሙም ያልተስማሙም ነበሩ፡፡ በግዜው አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች በሃሳቤ ያልተስማሙት እውነቱን ለማወቅ ፈልገው ሳይሆን መስማት የሚፈልጉትን መስማት ስለፈለጉ መሆኑን የተረዳሁት ቆይቼ ነው፡፡
የሆኖ ሆኖ ላልተስማሙት የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር ከላይ ምክንያቱን አስረድቼ ነበር የተለያየሁት፡፡ እንዳልኩትም ይኸው እስከ አሁን ድረስ ምንም ለውጥ ሳይኖር ክለቦች በወሰኑት ውሳኔ መሠረት ተጨዋቾች ደሞዝ እየተከፈላቸው ይገኛል፡፡ ጥያቄው ለምን ውሳኔው ሳይቀለበስ ቀረ የሚል ሊሆን ይችላል? ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገሩ ለውጥ ሳይኖረው ዛሬ ድረስ ሊቆይ የቻለው ውሳኔውን ማስቀልበስ የሚያስችል የህግ መሠረት ባለመኖሩ ነው፡፡