ባሳለፍነው ሳምንት የጀመረው የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በ5 የክልል ከተማዎች ተደርገዋል። 5ቱም ጨዋታዎች 9:00 ሲል የጀመሩ ሲሆን በዚህ ሳምንት የውድድር አመቱ አዳዲስ ሪከርዶች ተመዝግበውበታል።
አዳማ ላይ አዲስ አዳጊውን ወልቂጤ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በአመቱ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። ዳዋ ሁቴሳ 13ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ አዳማ ከተማን የአመቱን የመጀመሪያ 3ነጥብ እንዲያስመዘግብ አስችሎታል። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማ በሁለቱም ሳምንት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻለ ሲሆን የመጀመሪያውን ሳምንት ጨዋታ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ያለግብ አቻ መውጣቱ ይታወሳል። በሌላ ጨዋታ በጉጉት የተጠበቀው እና ባህርዳር ላይ የተካሄደው የባህርዳር ከተማ እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በባህርዳር ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ባህርዳር ከተማ አዳማ ሲሶኮ 23ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ መምራት የቻለ ሲሆን 37ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል መቐለ 70 እንደርታን አቻ ማድረግ ችሎ ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ ባህርዳር ከተማ መሪነቱን ለማስመለስ 3ደቂቃዎች ብቻ ሲፈጁበት 48ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ግብ አስቆጥሮ መምራት ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር 12ደቂቃዎች በኋላ ፍፁም አለሙ በድንቅ የግል ብቃት የባህርዳር ከተማን መሪነት ያጠናከረች 3ኛ ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታው በዚህ ውጤት ለጥቂት ደቂቃዎች የተጓዘ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታን ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ ስዩም ተስፋዬ ማስቆጠር ሲችል ይሄም ውጤት ለባህርዳር ከተማ የመጀመሪያ ድሉ ለመቐለ 70 እንደርታ ደግሞ የመጀመሪያ ሽንፈቱ ሆኖ ተመዝግቧል።
በሌላ ጨዋታ ደቡብ ደርቢ ሀድያ ሆሳዕና ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግብ ለማግኘት የመጨረሻዎቹ 10ደቂቃዎች እስኪቀሩ መጠበቅ ግድ ሆኖ ነበር። 82ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ሀዋሳ ከነማን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ቢችልም ከ5ደቂቃዎች በኋላ 87ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፍጮ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ ሀድያ ሆሳዕናን በጨዋታው አቻ ወጥቶ በሊጉ የመጀመሪያ ነጥቡን ማስመዝገብ ችሏል። በሌሎች ጨዋታዎች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤቱ ፋሲል ከነማ አፄ ፋሲለደስ ስቴዲየም ላይ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። በዚህ ጨዋታ ሙጂብ ቃሲም 3ግቦችን በማስቆጠር በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሀትሪክ የሰራ ተጫዋች መሆን ችሏል። ቀሪዎቹን የፋሲል ከተማ ግቦች ሽመክት ጉግሳ ማስቆጠር ችሏል። በሌላ ጨዋታ መቐለ ላይ ወልዋሎ አ.ዩ. ወላይታ ድቻን ገጥሞ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ለወልዋሎ ካርሎስ ዳምጠው እና ሰመረ ሀፍተይ ሁለቱን ግቦች ሲያስቆጥሩ ፀጋዬ ብርሀኑ የወላይታ ድቻን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ውጤቶችን ተከትሎ ወልዋሎ በ6 ነጥቦች ሊጉን ሲመራ ድሬደዋ ከተማ ያለምንም ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል።
አስተያየት ይስጡ