መነሻ ገጽ ዜናዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ባካሄደው ውይይት ለረጅም ጊዜያት ተጓቶ የነበረውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል
ዜናዎችየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንየኢትዮጵያ እግርኳስ ዳኞች ማህበር

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ባካሄደው ውይይት ለረጅም ጊዜያት ተጓቶ የነበረውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል

አጋራ
አጋራ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ባካሄደው ውይይት ለረጅም ጊዜያት ተጓቶ የነበረውን የፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ለአራት ጊዜ መራዘሙ የሚታወስ ነው።

ፊፋ ከሁለት ሳምንት በፊት የምርጫ አስመራጭ ኮሚቴው “ነጻና ገለልተኛ” ባለመሆኑ አዲስ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋምና ተቋሙ የላከው የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያ ጸድቆ የምርጫው ቀን እንዲወስን ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

የዛሬው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ውሳኔን ታሳቢ በማድረግ የተካሄደ ሲሆን በጉባኤ ላይ 140 የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተሳትፈዋል።

የጠቅላላ ጉባኤው አባላት የቀረቡትን አጀንዳዎች ከማጽደቃቸው በፊት የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

አሁን ያለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ የአራት ዓመት የስራ ጊዜያቸውን ከጨረሱ ከ10 ወራት በላይ በማስቆጠሩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን የመጥራትና የመምራት ስልጣን የላቸውም የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በተጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንዲራዘም ወሰንን እንጂ አሁን ያለውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ውሳኔ እንዳላሳለፉ ገልጸዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ውክልና የመሻር ህጋዊ ስልጣን አለው ስለዚህ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያውን ከማጽደቃችን በፊት አሁን ስልጣን ላይ ባለው አካል ላይ ጉባኤው ግልጽ የሆነ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል።

ስልጣን ላይ ለመቆየት ባላችሁ ፍላጎት ምክንያት ምርጫውን እያራዘማችሁ የእግር ኳስ እድገቱ እንዲቀጭጭ አድርጋችኋል፤ ጥፋታችሁን አምናችሁ ቀድማችሁ በገዛ ፈቃዳችሁ ስልጣን መልቀቅ ነበረባችሁ ሲሉ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተናግረዋል።

ፊፋና ካፍ ይቀጣናል የምትሉት የስልጣን ጊዜያችሁን ለማራዘም ነው ሌላ ምንም ምክንያት የለውም ብለዋል።

በምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያ አንቀፅ 2 መ’ መሰረት የስራ አስፈፃሚው ሌላ ተመራጭ እስኪመጣ መቀጠል አለበት ይላል፡፡

አንዳንዶቹ ተወዳዳሪዎች የስራ አስፈጻሚው ተወዳዳሪ ናቸው፤ ይህ ዲሞክራሲያዊ አይደለም፤ ስለዚህ ይህ አንቀፅ መሰረዝ አለበት በአንድ ጎን ተወዳዳሪ ናችሁ፤ የማይወዳደሩት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይቀጥሉ፤ የምትወዳደሩት ደግሞ በኮሚቴው መቀጠል የለባችሁም ተብሏል።

በምርጫ ማስፈጸሚያው መመሪያ የተፈጻሚነት ወሰን፣በአንዳንድ መሰረታዊ ሀሳቦች የአተረጓጎም ስህተት፣አንዳንድ አንቀጾች ግልጸኝነት፣የእጩዎች አመራረጥ ሂደት፤ የምርጫው ሂደትና በመመሪያው ላይ የፌደሬሽኑ ዋና ጸሐፊ የስራ ድርሻ በግልጽ መቀመጥ አለበት የሚል ሀሳብም ተነስቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ ይህ መመሪያ ለአሁን ምርጫ ለማስፈፀም ነው እንጂ ፊፋ እንዳለው ችግሮች ስላሉብን የተሻለ መመሪያ ለቀጣይ ጊዜ እናዘጋጃለን በመመሪያው ላይ የተነሱትን ሀሳቦች ከግምት ውስጥ እናስገባለን ብለዋል።

“የስልጣን ግዜን በተመለከተ ከዚህ በፊት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ምርጫው ሲራዘም መቀጠል ትችላላችሁ ብሎናል ለዚህም ማስረጃ አለኝ ምርጫው ስለተራዘመበት ጉዳይ በሚዲያ ተላልፏል” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ፊፋ ጠቅላላ ጉባኤውን እንድንጠራ ለአሁኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ፕሬዝዳንት ስልጣን ሰጥቷል፤ በዚህ ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤው መጠራቱን ተናግረዋል።

ከስልጣን አትወርዱም የተባለው ሁሉም በስርዓት የሚሆን ነው፤ ዝም ብለን ስራ ለቀን ፌደሬሽኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዳዩን መሬት ላይ መበተን አግባብ አይደለም፤ በስልጣን የመቆየቱ ጉዳይ ሁሉንም የስፖርት ቤተሰብና እኛንም ያሰለቸ ጉዳይ ነው ብለዋል።

እናንተ ባትሉም ከግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ ፊፋ ለኛ እውቅና አይሰጥም፤ ፊፋ ባስቀመጠው ገደብ ምርጫው ተካሂዶ ስልጣን እንለቃለን እስካሁን፤ ላጠፋነው ነገር ይቅርታ፤ አሁን ትኩረታችን የኢትዮጵያን እግር ኳስን መስመር ለማስያዝ በጋራ መስራት ላይ ነን ብለዋል፡፡

ከተነሱ ሀሳቦች በኋላ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያው በ109 ድጋፍ በዘጠኝ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

በህጉ መሰረት አሁን ያለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአስመራጭና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ እጩዎችን ያቀርባል በሚለው መሰረት ኮሚቴው ለአስመራጭ ኮሚቴ ስምንት ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው አምስት እጩዎችን አቅርበዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው በሰጠው ድምጽ መሰረት አቶ አስጨናቂ ለማ በ126፣ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን በ108፣ አቶ መሐመድ ኑር አብዱልከሪም በ101፣ወይዘሮ ህይወት አዳነ በ76 እና አቶ ኢብራሂም አደም በ70 ድምጽ የኮሚቴው አባላት ሆነው ተመርጠዋል።

አቶ እስክንድር ጀምበሬ፣አቶ ሰለሞን ሎሀ እና አቶ ጌታቸው አበራ በተጠባባቂነት ተይዘዋል።

ባገኙት ድምጽ መሰረት አቶ አስጨናቂ ለማ የኮሚቴው ሰብሳቢ እንዲሁም ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል።

ለይግባኝ ኮሚቴ እጩዎች በተሰጠው ድምጽ አቶ ሽፈራው አመኑ በ106፣አቶ ኦባንግ ሀባላ በ86 እና አቶ ገዛሀኝ ለማ በ79 ድምጽ የኮሚቴው አባል ሆነው ተመርጠዋል።

ወይዘሮ ማህተ አምባዬና አቶ ኤፍሬም ሳህሌ በተጠባባቂነት ተይዘዋል።

አቶ ሽፈራው አመኑ የይግባኝ ኮሚቴው ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ ኦባንግ ሀባላ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡት የአስመራጭ ኮሚቴና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ቃለ መሐላ የፈጸሙ ሲሆን ምርጫውን በታማኝነት፣በፍትሐዊነት፣ሰላማዊና ግልጽ በመሆነ መልኩ ለማከናወን እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ከቃለ መሐላው ስነ ስርአት በኋላ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ፍጻሜውን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የምርጫ ቀን መወሰን የአዲሱ አስመራጭ ኮሚቴ ቀጣይ የቤት ስራ ይሆናል።

በተሰጠው ስልጣን አማካኝነት አስመራጭ ኮሚቴው ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን የሚወስን ሲሆን ጠቅላላ ጉባኤውም ምርጫውን ለማካሄድ ኮሚቴው በወሰነው ቀን በማካሄድ ምርጫው የሚከናወን ይሆናል።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሲዳማ ቡናዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

የሲዳማ ቡና ቡድን መሪ ታገደ

በዮሴፍ ከፈለኝ የፕሪምየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና የቡድን መሪው የቀድሞው ዳኛ ዕግድ...

ዜናዎችየዲሲፕሊን ውሳኔዎች

27ኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች አብዱላጢፍ ባምባ (መቐለ 70 እንደርታ) : ክለቡ ከ ወልዋሎ አዲግራት...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ሲያጠናክር ኤሌክትሪክ እና አፄዎቹም አሸንፈዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ ሲዳማ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...