በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ እና በኢትዮጵያ ዋንጫ(ጥሎማለፍ) አሸናፊ መካከል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ አንድ ሳምንት በፊት የሚደረገው የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ዛሬ ተደርጎ መከላከያ ጅማ አባጅፋርን በመለያ ምት በማሸነፍ ከጥሎ ማለፉ ቀጥሎ ሁለተኛ ዋንጫውን ማሳካት ችሏል።
ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አብዛኛውን ጊዜ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ላይ ያመዘነ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው የመጀመሪያውን አስደንጋጭ ሊባል የሚችል ሙከራ ለማግኘት 21 ደቂቃዎች ፈጅተውበታል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ያሻገረለትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ በቀጥታ ሞክሮት ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል። ከዚህች ሙከራ 2 ደቂቃዎች በኋላ 23ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ኤርሚያስ ኃይሉ ወደሳጥን ውስጥ ሲያሻግረው ኤልያስ ማሞ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሯት ጅማ አባጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ መነቃቃት ያሳዩት መከላከያዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም የተሳካ አልነበረም። 25ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ ያሻገረውን ኳስ ሳሙኤል ታዬ በግንባሩ ሞክሮት የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄዬ በቀላሉ ይዞታል።
27ኛው ላይ የጨዋታውን መልክ የቀየረ ነገር ተከስቷል ይህም የመከላከያው ቴዎድሮስ ታፈሰ የጅማ አባጅፋሩን አስቻለው ግርማ በክርኑ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወገዶ መከላከያ ቀሪዎቹን ከ60 በላይ ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት ተገዷል። ከዚህ ሁነት በኋላ በጨዋታው የረባ የሚባል እንቅስቃሴ ሳይደረግበት የመጀመሪያው አጋማሽ በጅማ አባጅፋር መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ መከላከያ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጅማ አባጅፋር ደግሞ ውጤቱን በማስጠበቅ በጨዋታው የሚገኙ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጪ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ የመለሰችበት አጋጣሚ በጅማ አባጅፋር በኩል የሚያስቆጭ ነበር። ከዚህች ሙከራ 4ደቂቃዎች በኋላ 59ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ታዬ ሳጥን ውስጥ የተገኘውን ኳስ አስቆጥሮ መከላከያን አቻ ማድረግ ችሏል። 77ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ ይሁን እንዳሻው ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቷል። እንዲሁም የመደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ሰዓት 90+1ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ዳዊት እስጢፋኖስ ከመሀል ሜዳ ያሻገረውን ቅጣት ምት በሀይሉ ግርማ በግንባሩ ሞክሮት የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል ኤጄዬ አድኖበታል።

ሙሉ 90 ደቂቃው በዚህ ውጤት ተጠቃሎ አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት ያመሩ ሲሆን በመለያ ምቱም መከላከያ 4-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆን ችሏል። ከጅማ አባጅፋር በኩል ንጋቱ ገብረስላሴ እና ከድር ኄረዲን እንዲሁም ከመከላከያ ሽመልስ ተገኝ መለያ ምቶቹን የሳቱ ተጫዋቾች ናቸው።

አስተያየት ይስጡ