የኢትዮጵያ ተጋጣሚ በወዳጅነት ጨዋታ ቻድን ረታች

የዛሬ ወር ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ አቻውን የሚገጥመው የኒጀር ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት በኒያሚ በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ ከዕረፍት በኋላ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች የቻድ ብሔራዊ ቡድንን ሁለት ለምንም ረታ፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ፈረንሳያዊውን አሰልጣኝ ዣን-ሚሸል ካቫሊን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጋ መሾሟን ያሳወቀችው ኒጀር በዚህ ሳምንት ከቻድ እና ከሴራሊዮን ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ቀጠሮ መያዟ ቀድሞ የተነገረ ሲሆን የትናንት ምሽቱን የመጀመሪያ ጨዋታ በአሸናፊነት ደምድማለች፡፡ ድሉ ለአዲሱ አሰልጣኝ ዣን-ሚሸል ካቫሊም በኒጀር መለያ የመጀመሪያ ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል፡፡

ትናንት ምሽት በጄኔራል ሴኚ ኩንቼ ብሔራዊ ስታዲየም የተደረገውን ጨዋታ ኒጀር ሁለት ለባዶ ስታሸንፍ ሁለቱም ግቦች ከዕረፍት መልስ በዛካሪ አደባዮር እና በኢሳ ጂብሪላ የተቆጠሩ ናቸው፡፡

ኒጀር ቀጣዩን የወዳጅነት ጨዋታ ማክሰኞ ምሽት 12፡00 ሰዓት በሃገር ውስጥ ሊግ ብቻ በሚጫወቱ ተጫዋቾቿ ከሴራሊዮንን ጋር ታደርጋለች፡፡

Editor at Hatricksport

FacebookTwitter

Teshome Fantahun

Editor at Hatricksport