ከህዳር 29 ጀምሮ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰናጅነት በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የዘለቀው የአዲስ አበባ ሻምፒዮና ዛሬ ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስና በሰበታ ከተማ የፍጻሜ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በአራት የአዲስ አባባ ክለቦች፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያና ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም በአራት ተጋባዥ ክለቦች፤ ሰበታ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል፣ ባህር ዳር ከተማ ከአማራ ክልል፣ ወልቂጤ ከተማ ከደቡብ ክልል እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ከትግራይ ክልል በስምንት ክለቦች መካከል ሲካሄድ ቆይቶ በመጨረሻም በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
በውድድሩ ከተሳተፉት ስምንት ክለቦች ሁለቱ የአዲስ አበባ ተወካዮች መከላከያና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ስድስቱ ግን የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ናቸው፡፡ ከስምንቱ ክለቦች መካከል ከኢትዮ ኤሌክትሪክና ከወልዋሎ አዲግራት በቀር ስድስቱ ክለቦች በአዳዲስ አሰልጣኞች እንደመቅረባቸው ውድድሩ በመጪው ሳምንት ለሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በእጅጉ እነደሚያግዛቸው ይታመናል፡፡
በዝግጅት ጥራት ከፕሪሚየር ሊጉ ሳይቀር ሁሌም የተሻለ መሆኑ የሚነገርለት የከተማዋ ሻምፒዮና በተለይ ዘንድሮ፣ ከትኬት አቆራረጥና ከቴሌቪዥን ሽፋን ጋር በተያያዘ የተሸለ ነገር አሳይቶን አልፏል፡፡ አምና የተጀመረው የጨዋታውን ኮከብ ተጫዋች በዕለቱ የመሸለም ባህል ዘንድሮ ተጠናክሮና በሽልማት አድጎ የመጣ ቢሆንም በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ እንዴ እንዴት ነው ነገሩ የሚያስብሉ ተሸላሚዎች እንደነበሩበት መናገር ግን ግድ ይላል፡፡
ከዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር የአሞሌ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ትኬት ሽያጭ አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ሌላው የውድድሩ ጠንካራ ጎን ነው፤ ይሁንና ጎን ለጎን በስታዲየም በሮች የትኬት ሽያጭ ጋር አነስተኛ የትኬት አስተዳደሮች በተለይም በሚስማር ተራ፣ በዳፍ ትራክና በትሪቢዩን በሮች ላይ ቢከሰቱም የአዲሱን የትኬት አሰራር ጠንካራ ጎን ማንሳት አለመቻል ግን ስስታምነት ነው፡፡
እንደኮከቦች ሽልማት ሁሉ የባለፈው ዓመት የውድድሩ ጠንካራ ጎን የነበረው የመረጃ አስተዳደር፣ በተለይ ለሚዲያው መረጃዎችን በፍጥነትና በአግባብ ማድረስ ዘንድሮ በእጅጉ ተዳክሞ ተስተውሏል፡፡ በተጨማሪ ከመረጃ ባሻገር የሚዲያ ባለሙያዎችን የመግቢያ ካርድ እንዲያስተዳድሩ የተመደቡት ባለሙያ በፌዴሬሽኑ ሰው ጠፍቶ ካልሆነ በቀር ለሚዲያው የተሰጠውን ትኩረት ያሳብቃል፡፡ የሚዲያና የስም ዝርዝር ተጽፎ የተሰጣቸው ቢሆንም የንጉሱ “ሠ” እና የእሳቱ “ሰ” ን ልዩነት ስምህ የለም ለማለት ሲጠቀሙት ተስላውሏል ይህ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ ሚዲያው የሚያገለግላቸው ጨዋታውን በግንባር መጥተው ወይም በቴሌቪዥን ለማየት የማይችሉ አያሌ ሰዎች አሉ፡፡
በዘንድሮው የአዲስ አባባ ዋንጫ 16 ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ 33 ግቦች ተቆጥረዋል ከዚህ ውስጥ 13ቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተቆጠሩ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ሳላሃዲን ሰይድ አራት ግቦችን በስሙ በማስመዝገብ የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኗል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ምንም ጎል በስሙ ሳያዝመዘግብ የውድድሩን ሌላ ታሪክ ጽፏል፡፡
በአጠቃላይ ሁሉንም ጨዋታዎች 17,384 ተመልካች በትኬት ገብቶ የተመለከተ ሲሆን በአማካይ በየጨዋታው 19,276 ተመልካች ውድድሩን በስታዲየም ተገኝቶ ተመልክቶታል፡፡
እንደሁልግዜውም የከተማይቱ ሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች የውድድሩ ድምቀት የነበሩ ሲሆን በተለይ ረቡዕ ዕለት በተደረገውና ሁለቱን እርስ በርስ ባገናኘው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ በጋራ ያሳዩት ድጋፍ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ሲሆን የውድድሩ አዘጋጆችም የሁለቱንም ክለብ ደጋፊዎች የውድድሩ ልዩ ዋንጫ ተሸላሚ አድርገው ዕውቅና ሰጥተዋቸዋል ፡፡
ከ16 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደሃገሩ የተመለሰው የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ ተጫዋችና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሰራውን ቡድን ለማየት እድል ያገኘ ሲሆን በመጀመሪያው ቀን ጨዋታ ወቅትም አሰልጣኙ በደጋፊው ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ አሰልጣኙ ሊሰራ ያሰበውን ነገር ፍንጭ የሚሠጥ ነገር ሜዳ ላይ ማሳየት የቻለ ቢሆንም አሁንም ግን ክለቡ ግብ የማግባት ችግር እንዳለበት በግልጽ ታይቷል፤ በውድድሩም በአጠቃላይ ያገባው ጎል ሁለት ብቻ መሆኑ የክለቡን የማጥቃት ክፍተት ጠቋሚ ማሳያ ነው፡፡
በዚህ ዓመት ከሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል በሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠ ብቸኛ ተጫዋች ሲሆን ከባህር ዳር ከተማ ክለቡን ከተቀላቀለው ሌላው የተከላካይ ክፍል ተጫዋች ወንድሜነህ ደረጀ ጋር የሚፈጠሩት ጥምረት በዓመቱ ሊታዩ ከሚችሉ ክስተቶች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናን በግማሽ ፍፃሜ ጥሎ የመጣው ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያን ከፍጻሜው ጨዋታው ባስቀረው በሰበታ ከተማ መካከል የተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ በደማቅ ሁኔታ በደጋፊዎች ድጋፍ ታጅቦ በታታሪው የእግር ካስ ዳኛ ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ እየተመራ ይጀመራል ከተባለበት ሃያ አምስት ደቂቃ ዘግይቶ 10፡25 ሲሆን ተጀመረ፡፡ ተቀዛቅዞ የጀመረው ጨዋታ እየቆየ በቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ጫና በተለይ በሁለቱ ረዣዥም አጥቂዎች ሳላሃዲን ሰኢድና ዛቦ ቴጎይ ግብ ፍለጋ ጨዋታው ያለግብ የተጓዘው ለአስራ ስድስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ዣቦ ቴይጎ ከክንፍ የተሸገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት በአስራ ስድስተኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ፡፡
በከፍተኛ ዝናብ የታጀበው የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ክለቦች ብርቱ ፉክክር ቀጥሎ እረፍት ለመውጣት በተቃረቡበት ሰዓት በ39ኛው ደቂቃ በሳለሃዲን ሰይድ አማካኝነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛውን ግብ አስቆጠረ፡፡
ከእረፍት መልስ ሰበታ ስህተቶችን አርሞ ጫና ፈጥሮ ለመጫወት የሞከረ ሲሆን በተለይ ታደለ መንገሻ ከሩቅ መትቷት የግቡን አናት ለትማ የተመለሰችው ኳስ እጅግ የምታስቆጭ ነበረች፡፡ የቀድሞውን የመከላከያ አጥቂ ፍጹም ገብረማርያምን፣ አስቻለው ግርማን፣ ወጣቱን ተከላካይ ኃይለሚካኤልን ቀይረው ወደሜዳ በማስገባት ጫና ፈጥረው የተጫወቱት የሰበታው አሰልጣኝ ውበቱ ግብ ለማግባት ያደረጉት ሙከራ እጅግ ዘግይቶ በ82ኛው ደቂቃ የሰመረላቸው ሲሆን ፍጹም ገብረማርያም የግቧ ባለቤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከግቧ ባሻገር ፍጹም በተሰራበት ስህተት ለቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ጋናዊው ፍሪምፖንግ ሜንሳህ በቀይ ካርድ መሰናበት ምክንያት ሆኗል፡፡ የአንድ ሰውን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም በተደጋጋሚ የሞከሩት ሰበታዎች ሙከራቸው ሳይሳካ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ የሁለት ለአንድ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2012 የአዲስ አበባ ከተማ ሻምፒዮና አሸናፊ በመሆን ከዕለቱ የክብር እንግዳ የከተማይቱ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እጅ ሜዳሊያና የወርቅ ሜዳሊያ ተቀብሏል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመሃል ሜዳ ተጫዋች ያብስራ ተስፋዬ የጨዋታው ኮከብ በመሆን የ10000 ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የውድድሩ ሁለጠና የሰበታ ከተማ ሲሆን የ3ተኛ ደረጃውን በደረጃው ጨዋታ በመለያ ምት ኢትዮጵያ ቡናን 4-2 ያሸነፈው መከላከያ አግኝቷል፡፡ አዘጋጁ ፌዴሬሽን የውድድሩን ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ አሰልጣኝ በቀጣይ ጊዜያት ውስት መርጦ እንደሚያሳውቅ ቃል ገብቷል፡፡

አስተያየት ይስጡ