የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ወልቂጤ ከተማ

“የተጫወትነው ከጠንካራው ጊዮርጊስ ጋር ነው፤ ውጤቱ ይገባን ነበር ብዬ አስባለሁ።”አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ወልቂጤ ከተማ

“ከ20 ደቂቃ በኋላ ግን ለምን መጫወት እንዳቆምን አላውቅም፤ ከተጫዋቾቹ ጋር የማወራ ይሆናል።” አሰልጣኝ ሰርጂዮ ዚቪጅኖቭ ቅዱስ ጊዮርጊስ


አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው እንዳያችሁት ነው። ጠንካራ ጨዋታ ነው፤ ጊዮርጊስ ትልቅ ታሪክ ያለው ትልቅ ክለብ ነው። ጥሩ ተጫዋቾች ያለበት ስብስብ ነው። የተጫወትነው ከጠንካራው ጊዮርጊስ ጋር ነው። ወልቂጤ ስፖርት ክለብ ደግሞ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ ልጆቻችንም የጨዋታ ልምድ እያዳበሩ የመጡበት ሁኔታ ነው ያለው። ዛሬም ጨዋታው እንደሚከብደን እናውቅ ነበር። ይዘን የገባነውን ጨዋታ ለመተግበር የሚችሉትን ሁሉ ጥረዋል። ውጤቱ ይገባን ነበር ብዬ አስባለሁ።”

ስለሚባክኑ እድሎች

“ልጆቻችን ላይ ጉጉትም አለ። ከዚህ በተጨማሪም የልምድ እጥረትም አለ። ነገር ግን እንደ ቡድን የምናየው ያደረጉትን እንቅስቃሴ፣ ለማሸነፍ የነበራቸው ቁርጠኝነት፣ እነዚህ እኛ ትልቅ ቦታ የምንሰጣቸው ናቸው። ጎል ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እናያለን። እርግጥ ነው የባከኑ ኳሶች አሉ፤ በቀጣይ ደሞ እነዚህን ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን፤ እንደ ቡድን ግን ልጆቻችን ላይ እድገቶች እያየን ነው። ከምንም በላይ ግን ደጋፋዎቻችን በየሄድንበት ከጎናችን ነው ያሉት በዚህ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችንን ማመስገን እፈልጋለሁ።”


አሰልጣኝ ሰርጂዮ ዚቪጅኖቭ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

“ወልቂጤ አስቸጋሪ ቡድን በመሆኑ እና ጥቅጥቅ ብሎ የሚጫወት ቡድን እንደመሆኑ ከባድ ጨዋታ ነበር ጠብቀን የገባነው፤ እንደሚታወቀው ከኛ በመቀጠል ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን ነው። የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያው 20ደቂቃዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረነው ነበር፤ ከዛ በኋላ ግን ለምን መጫወት እንዳቆምን አላውቅም፤ ከተጫዋቾቹ ጋር የማወራ ይሆናል። ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ካላደረግን፣ ክሮሶች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ካላደረግን እንዴት ጎል ልናስቆጥር እንችላለን? በሁለተኛው አጋማሽም ቢሆን ወልቂጤ ከተማ የግብ እድል እየፈጠረ አልነበረም። እድለኞች ነበሩ። እኛ በሰራነው ስህተት ግብ አስቆጥረዋል። ከግቡ በኋላም ተጫዋቾቼ ጫና ውስጥ በመግባት ያለ እቅድ ሲጫወቱ አስተውያለሁ።”

ስለ ዋንጫ ጉዞው

” መጥፎ ጨዋታ ነው የተጫወትነው፤ አሁንም ዋንጫውን ለማንሳት ለምናደርገው ትግል እድል አለን። ፋሲል ከነማ በ1ነጥብ ብቻ ነው የሚበልጠን፣ 14ቀሪ ጨዋታዎች አሉን፤ ውድድሩ አላለቀም፤ የቻልነውን ሁሉ እንታገላለን።”

ከደጋፊው ስላለባቸው ጫና

“ደጋፊውን እረዳዋለሁ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀገሪቱ ትልቁ ክለብ እንደመሆኑ ከደጋፊዎች እና ከተለያዩ አካላት ሁሌም ጫና ይኖራል። ነገር ግን ማለት የምፈልገው አሁንም የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን እድሉ አለን።”

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website