“…የባህር ዳር ከተማ ደጋፊን መዝሙር እየሰማሁ በእነሱ ድጋፍ ታጅቦ መጫወት ከምንም ነገር በላይ ናፍቆኛል”ፍፁም አለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

“ረዥም ጊዜ ካለ ኳስ ማሳለፍ በጣም ያማል… ያስጨንቃልም…፤
…አምላክ በቃችሁ ብሎ ምህረትን ካላወረደልን በስተቀር አሁን

ያለው ነገር በጣም አስፈሪ ነው”

 

“…የባህር ዳር ከተማ ደጋፊን መዝሙር እየሰማሁ በእነሱ ድጋፍ

ታጅቦ መጫወት ከምንም ነገር በላይ ናፍቆኛል”

ፍፁም አለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

 

ሙሉጌታ ከበደን የመሰለ እስከአሁን ምትክ ያልተገኘለት ተጨዋች እንደ ብርሃኑ ፈይሳ (ፈየራ) አይነት መቼም በኢትዮጵያ እግር ኳስ የማይዘነጋ ተጨዋችና ሌሎች በርካታ ስመ-ጥር
ተጨዋቾችን ያፈራው የደሴ ማህፀን አሁንም የአብራኳ ክፋይ የሆነውን ፍፁም አለሙን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እነሆ በረከት ብላለች፡፡
የመጪው የኢትዮጵያ እግር ኳስን በበላይነት ይቆጣጠራሉ በሚል ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣት ኮከቦች አንዱ የሆነው የባህር ዳር ከተማው ፍፁም አለሙ በተለይ በያዝነው አመት
በፕሪሚየር ሊጉ አንፀባርቀው ካበሩ ኮከቦች በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ይገኛል፡፡
ከተሰጠው የጨዋታ ሚና ለግብ የሚሆኑ ምቹ ኳሶችን ከማቀበል ስራው በዘለለ ዘጠኝ ጎሎችን በስሙ በማስቆጠር ሁለተኛው ጎል አግቢ በመሆን ፉክክሩን የተቀላቀለው ፍፁም አለሙ
ፕሪሚየር ሊጉ በክፉው ወረርሽኝ ኮሮና ምክንያት ባይቋረጥ ኖሮ ከመሪው ፋሲል በሶስት ነጥብ (በአንድ ጨዋታ) ርቆ የሚገኘው ባህር ዳር ለዋንጫው የሰፋ እድል ይኖረው ታሪክም እንሰራ
ነበር ሲልም ተናግሯል፡፡ በስልክ ሞገድ አሳብሮ ደሴ የሚገኘውን የነገውን የእግር ኳሱን ኮከብ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያነጋገረው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር
የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ዘንድር የተሻለ አቅም ብታሳይም፣ከአማካይ ተጨዋች በማይጠበቅ መልኩ ዘጠኝ ጎሎችን ብታስቆጥርም ይህ ስኬትህ የብሔራዊ ቡድንን ማልያ
እንድትለብስ እድል አልፈጠረልህም በዚህስ አትበሳጭም? ብሎ ጠይቆት ፍፁም በራስ መተማመን የተሞላበት አስገራሚ ምላሽ ሰጥቶታል፤የደሴ ምድር ያፈራችው የባህር ዳር ከነማው
ቁልፍ ሰው ምን ብሎት? ይሆን ምላሹን ከቆይታችን ያገኙታል፤አብራችሁን ሁኑ፡፡

ሀትሪክ፡-ማን ብዬ እንደምጠራህ ግራ ገብቶኛል…?
ፍፁም፡-አልገባኝም…?…ስሜ ፍፁም አለሙ ነዋ…!…ከዚህ ውጪ ማን ብለህ ልትጠራኝ ነው…?
ሀትሪክ፡- …የአሁኑ መጠሪያህ…የፓስፖርት ስምህ ፍፁም አለሙ ቢሆንም ከዚህ ስም በፊት ግን ኤፍሬም አለሙ እንደምትባል ነው የሰማሁት…ተሳሳትኩ…?
ፍፁም፡-…እ…ሣቅ…!…ልክ ነህ አልተሳሳትክም…የመጀመሪያው ስሜ ኤፍሬም ነበር፤በኋላ ላይ ነው ወደ ፍፁም የቀየርኩትና የእስከአሁኑ ዋናው የመጠሪያ ስሜ ሆኖ የቀረው፡፡
ሀትሪክ፡- ልክ ፓርቲዎች እንደሚያደርጉት ሽግግር ከኤፍሬም ወደ ፍፁም የስም ሽግግር ማድረግ ለምን አስፈለገ…?
ፍፁም፡- …(አሁንም ሳቅ)…የቤተሰቤ የመጨረሻ ልጅ ስለሆንኩ ማዘሬ (እናቴ) ፍፁም ብላ ስም አወጣችልኝ፤እኔም እሷ ደስ እንዲላት ኤፍሬም የሚለውን ትቼ የእሷን መጠሪያ አፀደኩት፡፡
ሀትሪክ፡-..ኳስን በክለብ ደረጃ በእግርህ ከነካህ ወደ 3 ወር አካባቢ የሆነህ ይመስለኛል፤ የዕለት ተዕለት ሥራው እግር ኳስ ለሆነ ሰው ይሄን ያህል ጊዜ ኳስ ጥግ ሣይደርስ ማሳለፍ ከባድ አይሆንም… የህመሙ ስሜት እንዴት
እንደሆነ እስቲ ግለፅልኝ…?
ፍፁም፡- … ኡ…!…በጣም ያማል…!…በጣምም ያስጨንቃል…፤…ይረብሻልም…፤እግር ኳስ…ሙያችን… ስራችን በመሆኑ…ረዥሙን አመት ያሳለፍኩት ከእግር ኳስ ሳልለይ ነው…አሁን ደግሞ ሀገራችንንም
አለምንም በወረርው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት…ከእግር ኳስ ሣንወድ በግድ ተገልለን ነው ያለነው፤ አሁን እያሳለፍን ያለነው
ያልለመድ ነውን… ይሆናል ብለን ያልገመ ትነውን ነው…፤…ይሄን በራሱ ማስተናገድ በጣም ከባድ ነው…፤…ረዥም ጊዜ ካለ ኳስ ማሳለፍ በጣም ያማል…ያስጨንቃልም…፤…ደግሞም በዚህ መልኩ ማሳለፍ የራሱ የሆነ
የጎንዮሽ ጉዳት አለው…፤…በጣም ድብርት ውስጥ ይከታል፤ያስጨንቃል፤ የምንወደውን ስራችን የሆነን ነገር ከእኛ ውጪ በሆነ ነገር ተነጥቀን ነው እየኖርን ያለነው፤
በጣም ከባድ፣በጣም አዲስ ፈተና ነገር ነው የገጠመን፤መኖር ስለመቻሉም እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት ክፉ ጊዜ ነው የመጣብን፤መቼ እንደሚያበቃ መቼ ከአለም እንደሚጠፋ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል
በድብርት ውስጥ ሆነን መላመድ ነው ብቸኛው ምርጫችን፡፡

ሀትሪክ፡-..ለዚህን ያህል ወራት ከእግር ኳስ ርቃለሁ ብለህ የገመትክበት ጊዜ አለ…?
ፍፁም፡- …በፍፁም..አስቤ አላውቅም…! …እንኳን መገመት አይደለም ለሰከንድም ቢሆን ከእግር ኳስ ጋር እቆራረጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፤ሁላችንም የከበደን እኮ የገመትነው ያሰብነው ስላልሆነ አሊያም
ከዚህ በፊት ደርሶ ያየነው ነገር ስላልሆነ እኮ ነው፡፡ አሁን የምናወራው ስለ ሶስት ወር ነው…ግን መቼ እንደሚያበቃ…በዚህ መልኩ ስንት ወር እንደምንገፋ አናውቅም፤የፈጠረን አምላክ በቃችሁ ብሎ ምህረትን ካላወረደልን
በስተቀር አሁን ያለው ነገር በጣም አስፈሪ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ኮቪድ 19 ብዙዎችን አስገድዶ ከእንቅስቃሴያቸው ውጪ አድርጎ እቤት አስቀምጦአቸዋል፤ አንተስ ጊዘህን በምን መልኩ እያሳለፍክ ነው…?
ፍፁም፡- …በጣም አስገዳጅ ነገር ካልሆነ በስተቀር ከቤት አልወጣም፤ብዙውን ጊዜዬን ቤቴ ነው የማሳልፈው፤ለለውጥ ያህል ከጓደኞቼ ጋር ርቀቴን ጠብቄ በጥንቃቄ እየተገናኘሁ በመጫወት ኮሮና ያመጣውን ድብርት
ለመሸሽ እየሞከርኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አብዛኛውን ጊዜ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች ከክልል ክልል ስለምትዞሩ በካምፕ (በሆቴል) ስለምታሳልፉ የቤተሰብ ናፍቆት የበዛ ነበር፤አሁን ግን ናፍቆትህን የምትወጣበት ከባለቤትህ ቅድስትና ከልጅህ ጋር ፍቅርህን
የምታጣጥምበት በቂ ጊዜ ያገኘህ ይመስለኛል….?
ፍፁም፡- …የባለቤቴ ስም ደግሞ በምን አወከው…?…(በጣም ሳቅ)… በጣም የሚገርምህ ኮሮና መጥፎ አስጨናቂ…ህይወትን የሚነጥቅ ነገር ነው ይዞ የመጣው…፤…በአንድ በኩል ስታየው ግን መልካም
ነገርንም ይዞ መጥቷል ብለህ የምትናገርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በተለይ ለእንደኛ አይነቱ በሙያው ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር የማይገናኝ ሰው ቤተሰቦቹን በግላጭ የሚያገኘበት…ፍቅሩን የሚኮሞክምበት ጥሩም
አጋጣሚ ይዞ መጥቷል፡፡ እኔን ብትወስደኝ አሁን ለባለቤቴና ለልጄ እንደሰጠሁት ሰፊ ጊዜ ከዚህ በፊት ሰጥቼ አላውቅም፤ምን ያህል እንዳበደልኳቸው ፍቅር ነፍጌያቸው እንደኖርኩ የተረዳሁት አሁን በኮሮና ምክንያት እቤቴ
ሙሉ ጊዜዬን ማሳለፍ ስጀምር ነው፤በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከባቤቴም ከልጄም ጋር በጣም ጣፋጭና ደስ የሚል ጊዜን እያሳለፍኩ ነው፤ከኮሮና የሚገኝ መልካም ነገር ባይኖርም ከዚህ ክፉ በሽታ ጥሩ የሚባል ፍቅርን
ከቤተሰቦቼ የማገኝበትን እድልም አግኝቻለሁ፡፡


ሀትሪክ፡- …ስለ ባለቤትህና ልጅህ ካነሣህ እስቲ በዚህ አጋጣሚ አስተዋውቀኝ….?
ፍፁም፡- …(ሣቅ)…ባለቤቴ ቅድስት አንድአምላክ ትባላለች፤ የጎንደር ልጅ ናት፤ፋሲል ከነማ ስጫወት ጠብሼያት ነው የግሌ ያደረኳት…(ሣቅ)…፤…ቅድስት በጣም ደስ የምትል በጣም አሪፍ ልጅም ናት፤
ከአመልዋም፣ከመልኳም፣ከስብዕናዋም አንፃር አምላክ ትክክለኛዋን ሰው ነው የሰጠኝ፡፡ የበለጠ እንድወዳት፣ህይወቴም ይበልጥ የተሟላ እንዲሆን ደግሞ ናታናሄም ፍፁም የሚባል ወድ ልጅ አስታቅፋኛለች፡፡ ናታንሄም
ከሶሰት ቀን በኋላ አንድ ሻማ በመለኮስ ወደዚህች ምድር የመጣበትን አንደኛ አመቱን ያከብራል፤በአጠቃላይ ባለቤቴ በህይወቴ ደስተኛ እንድሆን አድርጋኛለች፤እኔነቴንም የቀየረች መልካም ሰው ናት፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙ ተጨዋቾች ትዳር ሲፈሩ ሲሸሹ ይታያል…ፍፁም ደግሞ ይበልጥ ጎልቶ መታየት የጀመረው ትዳር ከያዘና አንድ ልጅ ከባለቤቱ ካገኘ በኋላ ነው የሚሉ አሉና…በዚህ በኩል ምን ትላለህ…?
ፍፁም፡- …እውነት ነው፤…ብዙ ተጫዋቾች ወደ ትዳሩ አለም ለመግባት ሲፈሩ ወይም ሲያንገራግሩ ይታያል፤እንደ እኔ ተሞክሮ ከሆነ ግን የምትሆንህን ውሃ አጣጪ ቶሎ ይዞ መሰብሰብ በጣም ብዙ ጥቅም ያለው ብቻ
ሳይሆን…ከብዙ ነገር እንድትሰበሰብ፣ራስህን እንድትጠብቅ፣የበለጠ ነገሮችን በኃላፊነት ስሜት እንድትመራ ያደርግሃል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከራስህ አልፈህ ቤተሰብ መምራት ስትጀምር ኃላፊነት መሸከም
ትጀምራለህ፣ከጀርባህ ባለቤትህ፣ልጅ እንዳለህ ስታስብ…ከራስህ አልፈህ ለሰው መኖር ትጀምራለህ…ትጠነቀቃለህ…ከብዙ ነገርም ትጠበቃለህ…በፕሮግራም የምትመራ ሰውም ትሆናለህ…ራስህንም ጠብቀህ ብዙ አመት በብቃት
እንድትጫወት ያደርጋሀል፤እነዚህንና ሌሎች ያልጠቀስኳቸው ብዙ የትዳር ጥቅሞች አሉት፤ስለዚህ ከተሞኩሮዬ ያየሁት ትዳር የሚያስፈራ እንዳልሆነ ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ፍፁም እግር ኳስን በእግሩ ከነካ ከመደበኛ እንቅስቃሴ ከራቀ ሶስት ወራትን አስቆጥሯል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በዋናነነት ምንድነው የናፈቀው?
ፍፁም፡- …ሁለት ነገሮች በጣም ናፍቀውኛል፤ወደ ቀደመው ህይወቴ መመለስ በጣም ናፍቆኛል፤ አሁን አዲስና የማላውቀው ከእግር ኳስ ውጪ ያለ ህይወትን እየመራሁ ነው፤ይሄ በጣም ያስጨንቃል…ድብርት ላይም
ስለሚጥል…የበፊተኛው ህይወቴ በጣም ናፍቆኛል…፤…ሁለተኛው ደግሞ ምትክ በሌላቸው በምወዳቸው በባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች ታጅቦ መጫወትም እንዲሁ በጣም ናፍቆኛል…፤…የባህር ዳር ከተማ ደጋፊን መዝሙር
እየሰማሁ በእነሱ ድጋፍ ታጅቦ መጫወት ከምንም ነገር በላይ ናፍቆኛል፤አምላክ የእስከዛሬው በቃችሁ ብሎ ወደ ቀድሞ ህይወታችን ተመልሰን ይሄንን ናፍቆቴን ብወጣ ከምንም በላይ እንደሰታለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ፕሪሚየር ሊጉ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከመቋረጡ በፊት ፍፁም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጎልቶ የታየበት ለግብ አግቢነት የተፎካከረበት አመት ነው ከሚል ሃሣብ በመነሣት ይሄ አመት የፍፁም
አመት ነበር የሚሉ አሉ…እውነት አመቱ የአንተ ነበር ማለት ይቻላል?
ፍፁም፡- …ሁለት አይነት ስሜት ነው ያለኝ…፤…እንዳልከውም ከዚህ በፊት ዘጠኝ ጎል አቆጥሬ ለኮከብ ጎል አቢነት ተፎካክሬ ስለማላውቅ…ክለቤ ባህር ዳር ከተማም ከመሪው ፋሲል ከተማ በ3 ነጠብ ተበልጦ
ለዋንጫ ፉክክር የተጠጋበት አመት በመሆኑ አመቱን የእኔ የሆነ ተደርጎ እንዲታስብ እንዳደረገው ይገባኛል፤ በእርግጥ ከነበረው ሁኔታ በተለይ ዘጠኝ ጎል አግብቼ በኮከብ ጎል አግቢዎች ተርታ ውስጥ መሆኔ አባባሉ እውነትነት
አለው ብዬ እንዳስብም ያደርገኛል፤ነገር ግን ባለፈው አመትም ከፋሲል ጋር በጣም ጥሩ የሚባል አመትን ነበር ያሳለፍኩት፤እንደ አሁኑ ዘጠኝ ጎል አላገባሁም እንጂ።ከዚህ ውጪ መጨረሻው አላማረም እንጂ ባለፈው
አመትም ከፋሲል ጋር በጣም ጥሩ የሚባል ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፤እስከ መጨረሻ ለዋንጫ ተፋልመን ነው አመቱን የጨረስኩት፡፡

ሀትሪክ፡- …በያዝነው የውድድር ዘመን ባልተለመደ ሁኔታ ፍፁም ከመሃል ሜዳ በርካታ እየተነሳ ግቦችን በማስቆጠር የክለቡ ብቸኛው ጎል አግቢ ከመሆን ባለፈ በፕሪሚየር ሊጉም ለኮከብ ግብ አግቢነት በሁለኛነት እየተፎካከረ
ነው፤ የዚህን ምስጢር ምንድነው ማለት ይቻላል…?
ፍፁም፡- …እኔ እንጃ…!…ብዙም የተለየ ተዓምርና ምስጢር ያለው አይመስለኝም…፤…እኔ እንደ ዋና ምክንያት ወይም ምስጢር የማነሣው የመጀመሪያው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሰጠኝ ነፃ የጨዋታ ሚና
ይመስለኛል…፤…አሁን በባህር ዳር ነፃ ሚና ተሰጥቶኝ እየተጫወትኩ ነው እያሳለፈኩ ያለሁት፤ በዚህ የተነሣም ብዙ የጨዋታ ጊዜዬን ያሳለፍኩት በማጥቃቱ ላይ ነው፤ይሄ በጣም ጠቅሞኛል ብዬ አስባለሁ፤ ከዚህ ውጪ
በአሰልጣኞቼ የሚሰጠኝን ትምህርትና ስልጠና በአግባቡ መከታተሌ…የተሻለ ነገር ለመስራት በግል ጥረት ማድረጌና እግዚአብሔርም ተጨምሮበት ለጎል የሚሆን ኳስን ከመስጠት በዘለለ ጎልም በብዛት ማስቆጠር ችያለሁ፤
በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ አሰልጣኝ ፋሲል ነፃ የጨዋታ ሚና ከመስጠት ባለፈ ብዙ ድክመቶቼን አርሞ በጎደለኝ ሞልቶ ያለኝን ይበልጥ አሳድጎ…ለዚህ እንድበቃ እሱም ምክንያት
ነውና አመሰግነዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን በዚህ ደረጃ የተሻልክ በሆንክበት…ጎልተህ በታየህበት…ከመሀል እየተነሣህ 9 ጎል ባስቆጠርክበት አመት…የብ/ቡዱኑን ማልያ እንድትለብስ የተጠራህ የለም፤ ይሄ አያበሳጭህም…ተስፋስ አያስቆርጥህም…?
ፍፁም፡- …እንዴ ለምን እበሳጫለሁ?…(ሣቅ)…ለምንስ ተስፋ እቆርጣለሁ?…እኔ ለብሔራዊ ቡድን ባልጠራም በጣም ጥሩ ጥሩ ልጆች ናቸው የተመረጡት…፤…ሁሉም ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ተጨዋቾች
በመመረጣቸው ለብ/ቡድኑ አልተጠራሁም…፤…አንድ ማመን ያለብህ ነገር እኮ በፕሪሚየር ሊጉ ያሉ ጥሩ የተንቀሳቀሱ ተጨዋቾች…በአመቱ ውድድር ጥሩ ስለተንቀሳቀሱ ብቻ አይመረጡም፤ እኔም የዚህ አካል በመሆኔ
አልተመረጥኩም ብዬ አልበሳጭም…ምክንያቱም አሰልጣኙ መምረጥ የሚችለውን 25 ተጫዋቾችን መርጧል፤እዚህ ውስጥ ብኖር ከማንም በላይ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፤ ግን ባለመጠራቴ ብዙም
አልበሳጭም…ባለመጠራቴ ከመበሳጨትና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ነገ ለመመረጥ ይበልጥ ጠንክሬ እንድሠራ ነው የሚያደርገኝ፤እኔ ለብ/ቡድኑ ባልጠራም ጓደኞቼ በቡድኑ ውስጥ በመኖራቸው በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-.. ከዚህ በኋላስ እድሉን አግኝተህ የብ/ቡድኑን ማልያ የምትለብስ፣ከ100 ሚሊዮን የሚበልጠውን ህዝብ የምትወክልበት ወርቃማውን እድል የምታገኝ ይመስልሃል….?
ፍፁም፡- … አዎን በደንብ ይመስለኛል…እኔ እኮ አሁን የምገኘው ገና የጨዋታ መጀመሪያዬ ላይ እንጂ መጨረሻዬ ላይ ባለመሆኑ ከጠነከርኩ ከፊቴ ያሉትን እድሎች ማሳካት እንደምችል አምናለሁ፤ጠንክሬ ከሰራሁና
የአሰልጣኙን አዕምሮ በአጨዋወቴ ማሸነፍ ከቻልኩ የብ/ቡድን ማልያ ከመልበስ የሚያግደኝ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ የደርቢ ተፎካካሪ ከሆኑ ከአንድ የከተማ ቡድኖች ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ተቀናቃኝ ቡድን መዘዋወር እምብዛም በማይታይበት ሁኔታ አንተ ግን ከፋሲል ከተማ ወደ ሌላው ተቀናቃኝ የባህር
ዳር ከተማ ቡድን ተዘዋውረሃል፤ይሄ መሆኑ የፈጠረብህ ምንም ችግር የለም… እንደ ሉዊስ ፊጎ ይሁዳ ተብለህስ የተወረወረብህ ነገር የለም?
ፍፁም፡-…(በጣም ሳቅ)…በዚህ በኩል ምንም የገጠመኝ ነገር የለም…፤…እንደውም በጣም በሚገርምህ ሁኔታ በሁለቱምም ክለቦች ደጋፊዎች መልካም አቀባበል ነው የተደረገልኝ፤አንተ እንዳልከው በፋሲል
ባለፈው አመት እስከዋንጫ ድረስ የተጓዘ መልካም የሚባል ጊዜን አሳልፌያለሁ፤በክለቡም አራት አመት ያህል አሳልፌያለሁ…ይሄ ረዥም ጊዜ ነው፤ክለቡም ልክ የቤተሰቤ ያህል ነው የነበረው…የከበደኝ ነገር ከፋሲል ወጥቶ
ባህር ዳር መግባቱ ሣይሆን እንደ ቤተሰብ የምታየውን ክለብ ለመልቀቅ መወሰኑ ላይ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ከባድ ሆኖብኝ ነበር…ነገርግን ያልተስማማንባቸው ነገሮች ቢኖሩም በስምምነት… በሠላም ነው
የተለያነው…ከፋሲል ወጥቼ ለባህር ዳር ስፈርምም የገጠመኝ መልካም የሚባል አቀባበል ነው…ከሁለቱም ደጋፊዎች ፍቅር እንጂ የተለየ ችግር አልገጠመኝም፤የፋሲልም የባህር ዳር ደጋፊዎችም ለእኔ ጥሩ ፍቅርና ክብር
አላቸው፤በዚም የሁለቱንም ክለብ ደጋፊዎች ባሳዩኝ ፍቅርና ድጋፍ ይበልጥ እንድወዳቸው እንዳከብራቸው አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …የአንድ ከተማ ተፎካካሪና የደርቢ ተቀናቃኝ የሆኑ የሁለት ክለቦችን ማልያ በተለያየ ጊዜ ለብሰህ የደርቢ ጨዋታ ማድረግህስ ምን አይነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርግሀል?
ፍፁም፡- …ይሄ በጣም የሚገርም እድል ነው፤ የፋሲልንም የባህር ዳር ከተማንም ማልያ ለብሼ በደርቢ ጨዋታ በሁለቱም ወገን ሆኜ በመጫወቴ ራሴን የተለየ እድለኛ አድርጌ እንዳስብ ነው ያደረገኝ፡፡ ብዙ ተጨዋች
የዚህን መሰሉን እድል ሲያገኝ አይታይም፤ ከዚህ አንፃር በሁለቱም ወገን ሆኜ በተለያየ ጊዜ የደርቢ ጨዋታ ማድረጌና በሁለቱም በኩል ያለውን የደስታ ስሜት ማጣጣም በመቻሌ ራሴን እንደተለየ እድለኛ አድርጌ
እንድቆጥረው አድርጎኛል፡፡


ሀትሪክ፡-ፕሪሚየር ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ክለብህ ባህርዳር ከተማ ከመሪው ፋሲል በሶስት ነጥብ ርቀት የተቀመጠበት፤አንተም ከፋሲሉ ጎል አግቢ ሙጂብ ቃሲም በ5 ጎሎች ብቻ አንሰህ በሁለተኛ ደጃ ላይ
የምትገኝበት ሁኔታ ነው የነበረው…ከዚህ አፃር በመነሣት ሊጉ ባይቋረጥ ኖሮ ባህር ዳር ዋንጫውን…አንተም የፕሪሚየር ሊጉን የኮከብነት ክብር የምታሳኩበት እድል ይፈጠር ነበር ብሎ ማሰብ ይቻላል?
ፍፁም፡- …የእኔን እንኳን ተወው…ምክንያቱም እኔን ሁሉም የሚያስጨንቀኝ የግል ክብሬ ሣይሆን የክለቤ ሻምፒዮናነት ብቻ ነው፤ኮከብነትን በተመለከተ ከእኔ ይልቅ ሙጂብ ቃሲም ለክብሩ በጣም የቀረበ እንደሆነ
አድርጌ ነው የማስበው፤ምክንያቱም የሁለታችንም የጨዋታ ሚና የተለያየ ነው፡፡ እኔ ሚድፊልድ (አማካይ) ተጨዋች ነኝ፤ ሙጂብ ደግሞ ጎል ማግባት ብቻ ዋነኛ ስራው የሆነ ተጨዋች ነው፤አሁን ጎል የማግባት እድል
ባገኝም ዋነኛው ስራዬ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ነው፤እኔ ከመሀል ሜዳ ተነስቼ ነው ዘጠኝ ጎል ያስቆጠርኩት እንጂ እንደ ሙጂብ ቃሲም በየጨዋታው ጎል እያስቆጠርኩ ተፅዕኖ የምፈጥር አይነት ተጨዋች
አይደለሁም፤ስለዚህ ከጨዋታ ሚናችን…ለጎል ከመቅረባችን አንፃር…ከእኔ ይልቅ ሙጂብ ቃሲም ለክብሩ የቀረበ እንደሆነ ነው ውስጤ የሚያምነው፤ ወደ ቡድናችን ስትመጣ ግን በጣም ጥሩ ቡድን ነው ያለን…፤…ለዋንጫ
የመፎካከር አቅም ብቻ ሣይሆን የቀረበ ቡድን እንዳለን ነው ውጤቱ ራሱ የሚናገረው…በተለይ በሜዳችን ያለመሸነፍ መልካም የሚባል ሪከርድ ያለው ቡድን ነው ያለን፤ በቀጣይ በሜዳችን የምናገኛቸውን እድሎች
ከተጠቀምን…ያለንን የነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ ብቻ አይደለም ማሻሻል ከቻልን ከመሪው ፋሲል ጋር ለዋንጫው የሚፎካከር ጥሩ ቡድን እንደምንሆን ነው የማምነው፤ግን ምንታደርገዋለህ እግዚአብሔር አልፈቀደም እንጂ
አያያዛችን ወደ ዋንጫ የሚንደረድር ዋንጫ እስከማንሣት ሊሄድ የሚችል ቡድን እንዳለን ነው የሚጠቁመው፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የገነባው የዘንድሮውን ባህር ዳር እንዴት ነው የምትገልፀው?
ፍፁም፡- አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የገነባው ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነው፤ኳስ ይዞ በመጫወት ውጤት ማምጣት የሚፈልግ…ደጋፊው ብቻ ሣይሆን ማንኛውም ኳስ የሚወድ ተመልካች ለመመልከት የሚመርጠው
ቡድን ነው የገነባው፤ኳስ ይዞ በመጫወት ማጥቃት ላይ ፈታኝ የሚበል ጫናን የመፍጠር አቅም ያለው ጠንካራ ቡድን ነው የገነባው፤ አጨዋወቱም ውጤቱም እንደመጀመሪያ አመትም በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ብዙዎቹ
የቡድኑ ተጨዋቾች ለታክቲኩ የተመቹም ናቸው፤ በጣም አሪፍ ቡድን በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ባህር ዳር ሁለት አይነት ቡድን ነው…በሜዳው ሲጫወት ያለመሸነፍ ሪከርድ ቢኖረውም ከሜዳው ውጪ ሲጫወት በውጤትም በአጨዋወትም ይለያያል ሲሉ ይሰማል፤በአስተያየቱ ትስማማለህ?
ፍፁም፡-…በፍፁም አልስማማም…ከሜዳችን ውጪ የምንሸነፈው እኛ ብቻ አይደለንም፤16ቱም የፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ከእኛ የተለየ ያን ያህል መልካም የሚባል ውጤት የላቸውም፤የሁላችንም
ከሜዳ ውጪ ያለው ታሪክ ተመሳሳይ ነው፤ እኛ እንደውም በሜዳችን የተሻለ ሪከርድ ነው ያለን ከሌሎቹ አንፃር፡፡
ሀትሪክ፡- …በሜዳችሁ ያለመሸነፍ ሪከርዳችሁን ምስጢር ከምን ጋር ማያያዝ ይቻላል?
ፍፁም፡- ዋናውና ትልቁ ምስጢራችን ደጋፊዎቻችን ናቸው፤የደጋፊው ድጋፍ በሜዳህ እንዳትሸነፍ ትልቅ ጉልበት የሚሰጥና የሚያግዝ ነው፤ደጋፊዎቻችን በሜዳችን ስንጫወት በብዛት ይገባሉ፤በብዛትም
ይደግፉናል፤ሲደግፉም ከልባቸው ነው የሚደግፉት፤ስሜታዊነት ሳይጫናቸው የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችንና ደጋፊዎችን አክብረው የሚደግፉ የተለዩ ደጋፊዎች ናቸውና የእነሱ ድጋፍ በሜዳችን ለተመዘገበው ያለመሸነፍ ሪከርድ
ዋነኛው ምስጢር እነሱ ናቸው ብዬ ነው የማምነው፤ከደጋፊዎቻችን ውጪ የአሰልጣኞች የቡድን አባላት የክለቡ አመራርና የህክምና ቡድን አባላት ድምር ውጤት በሜዳችን ለታየው ጥንካሬዬን ሌላኛው መገለጫ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የባህር ዳር የአጥቂው ክፍል ግብ ያመርታል፤የተከላካይ ክፍሉ ደግሞ ጎል የሚያፈስ ቀዳዳ ነው ብለው የሚተቹ አሉ…ይሄንንስ አትቀበልም…?
ፍፁም፡- …(ሳቅ)…ይሄንን እንኳን ሁሉም የሚያየው ስለሆነ መካድ አልችልም፤መከላከሉ ላይ ትልቅ ድክመት አለብን፤ሶስት አግብተን፣ ሶስት ይገባብናል፤3ለ0 ስንመራ ቆይተን ሁለት ገብቶብን ጨዋታው 3ለ2
የሚጠናቀቅበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡በዚህ በኩል ድክመት እንዳለብን ማመኑ እንጅ መከራከሩ አይጠቅመንም፡፡ ግን ለዚህ ችግር መወቀስ ካለብን እንደ ቡድን እንጂ ተከላካይ ክፍሉን አንድና ሁለት ተጫዋቾችን ብቻ ነጥለን
አውጥተን መወቀስ አለብን ብዬ አላስብም፡፡11ዱም ተጨዋቾች እንደ ቡድን ወደ ኋላ ተመልሰን ተከላካይ ክፍሉን ባለማገዛችን የተፈጠረ እንደሆነ ነው እኔ የማምነው፡፡ ከዚህ ውጩ ከጨዋታ በፊት የተነገረንን መርሣታችን
እንዲገባብንም አድርጓል ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ግን ድክመታችንን በማመን ጠንክረን በመስራት ለማረም ጥረት እናደርጋን፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን አንተ በባህር ዳር የምትለብሰው 14 ቁጥር ነው፤ይሄን የመረ ጥክበት የተለየ ምክንያት አለህ፤ብዙ ሰዎች 13 ቁጥርን ገደቢስ ሲሉት ይሰማል…በቁጥሩ ገደቢስነትስ ታምናለህ?
ፍፁም፡- …እኔ ብዙም ቁጥር ላይ የተለየ እምነት የለኝም…የተለየ ምክንያት ሳይሆን እንዲህ ቀልብህ የሚወደው ከሌሎች የምታስበልጠው ቁጥር ይኖራል፤ ለምሣሌ እኔ ባህር ዳር ስመጣ 6 ቁጥርን ነበር መልበስ
የፈለኩት…ግን ቁጥሩ የለም ተይዟል፤መጨረሻ ላይ ያልተያዘ ቁጥር ስፈልግ 14 ቁጥር ነፃ ሀኖ በማግኘቴ እንጂ በተለየ ምክንያት 14 ቁጥርን አልለበስኩም፤13 ቁጥር ገደቢስ ቁጥር ላልከው እኔም ሲባል እሰማለሁ ግን
አላምንበትም፤የቁጥር ገደቢስነቱ እኔ አይገባኝም፤በሜዳ ላይ ጥሩ ለመጫወት የሚያግዘው የለበስከው የማልያ ቁጥር ሣይሆን የአንተ ብቃትና ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው፤ ከቁጥር ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር
የለም…ገደቢስ ቁጥር በሚባለውም የማምን ሰው አይደለሁም፡፡


ሀትሪክ፡-አሁን ከምትጫወትበት ቦታ በሌላ ቦታ እንድትጫወት የሚል ውሳኔ ቢተላለፍብህ በየትኛው ቦታ መጫወትን ትመርጣለህ?
ፍፁም፡- …አጥቂ ሆኜ ራሴን ባየው ደስ ስለሚለኝ አጥቂ መሆንን ነው የምመርጠው፤
ሀትሪክ፡- …አብሮኝ ሲጫወት ጨወታ ያቀልልኛል የምትለው ተጨዋች?
ፍፁም፡- …ሀብታሙ ተከስተ (ጎላ) ጎኔ ሆኖ ሲጫወት…መጫወት በጣም ይቀለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-አብሬው ባለመጫወቴና እንደገና አብሬው ብጫወት ብለህ የምትቆ ጭበት ተጨዋችስ?
ፍፁም፡-ሠለሞን ገ/መድህን፣ ከሰሌ ጋር አብሬ ባለመጫወቴ በጣም ነወ የምቆጨው፤ከዚህ በኋላም የውስጤን አይቶ ዳግም አንድ ማልያ ለብሰን የምንጫወትበት እድል ባገኝ በጣም ነበር የምደሰተው፡፡
ሀትሪክ፡- …እነ ሙሉጌታ ከበደን የመሰሉ…እስከዛሬ ተተኪ ያልተገኘላቸው ህያው ጀግኖች የተወለዱበት ደሴ ከተማ ነው የተወለድከውና ይሄ መሆኑ ምን አይነት ስሜት በውስጥህ ይፈጥራል?
ፍፁም፡- …ትልቅ የኩራት ስሜት ይፈጥራል፤እነ ሙሉጌታ ከደሴ ከተማ ወጥተው ዛሬም ድረስ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሣ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ የእነሱ ስም ሲነሣ ደሴም አብራ ስለምትነሣ እኔም ከዚህች ታሪካዊ
ከተማ በመገኘቴ የተለየ ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል፤የእነ ሙሉጌታን ገድልና ታሪክ ስትሰማ ልክ እንደ እነሱ ለመሆን እንድትነሳሳ ያደርግሃል፤ከዘህ ወጣ ብለህ ስታየው እነሱ በተወለዱበት ከተማ መወለድ የበለጠ ኃላፊነት
እንድትሸከምም ያደርግሃል፤የከተማው ህዝብም እንደ እነ ሙሉጌታ አይነት ጀግኖችን እያየ ስላለፈ ከእኛም ብዙ ነው የሚጠብቀው …ይህ በራሱ እንዳትዝናጋ ያደርግሃል፤ በአጠቃላይ የተለየ ስሜት በውስጥህ እንዲፈጠር
ያደርጋል፡፡
ሀትሪክ፡- …ህልም አለህ…?
ፍፁም፡- …አዎን አልማለሁ…ህልም ከሌለህ የምትፈልገው ቦታ አትደርስም…፤…በሙያዬ በጣም ስኬታማ የመሆን…ከራሴ አልፌ ሀገሬን የማኮራ ጠቃሚ ተጨዋች መሆንን አልማለሁ…፤…እኔም ማለሜን
እቀጥላለሁ…አምላክም ይረዳኛል ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከባህር ማዶ የምታደንቀው…የተለየ ቦታ የምትሰጠው አሰልጣኝ…?
ፍፁም፡- …የማንቸስተር ሲቲው ፔፕ ጋርዲዮላ ለእኔ የተለየ አሰልጣኝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-…ከተጫዋቾችና ከክለብስ ምርጫህ…?
ፍፁም፡- …ከተጫዋቾች ሊዮኔል ሜሲ ሲሆን…ከክለብ ደግሞ ባርሴሎና የመጀመሪያ ምርጫዬ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- …በጨዋታ ዘመኔ መቼም የማልረሳውና ደስታን ያጣጣምኩበት የምትለው…?
ፍፁም፡- በጣም የተደሰትኩበት ጨዋታ ባለፈው አመት ፋሲል ከነማ እያለሁ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የ7 ነጥብ ልዩነት እያለን ሜዳችን ላይ 1ለ0 ያሸነፍንበትን ጨዋታ መቼም የማልረሳውና በጣም የተደሰትኩበት
ጨዋታ ነው፤ ይሄንን በዋኛነት አነሳውልህ እንጂ አመቱን ሙሉ እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ በጣም የተናነቅንበትና ለዋንጫ የታገልንበት ምርጥ የጨዋታ አመት ያሳለፍኩበት ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- …በጣም የምትቆጭበትና በመጥፎነት የምታነሣው ጨዋታስ?
ፍፁም፡- …በጣም የምቆጭበት ከፋሲል ጋር ዋንጫ የማንሣትና ታሪክ የማፅፍበት ወርቃማ አጋጣሚ ከሽሬ ጋር የነበረንን ጨዋታ ሁሌም በመጥፎነት ሳነሣው የምኖረው ጨዋታ ነው…ውጤቱ አምኜ የማልቀበለውን
ዋንጫ ያሳጣንን ይሄንን ጨዋታ ሁሌም ቁጭቱ አብሮኝ ይኖራል፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.