የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዲህ እንዲህ እያለ 12ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። በነዚህ 12ሳምንታት ውስጥ 96ጨዋታዎች ሲደረጉ በጥቅሉ 220 ግቦች ተቆጥረዋል። ይህም ማለት በየጨዋታው በአማካይ 2.29 ግቦች ይቆጠራሉ ማለት ነው። ይህም ከአለፉት አመታት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጋር ሲወዳደር ይበል የሚያሰኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሊጉ ከ2 ጨዋታዎች በቀር በፍፁም ሰላማዊ እና ባማረ የደጋፊዎች ድባብ እንዲሁም በጥሩ እንግዳ ተቀባይነት እየተካሄደ ይገኛል።
በነዚህ 96 ጨዋታዎች 71 ጨዋታዎች በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ 25 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ማለቅ ችለዋል። ከነዚህ ሁሉ ጨዋታዎች ግን 15 ብቻ ከሜዳ ውጪ የተገኙ ድሎች ናቸው። ይህ ደግሞ በሊጉ ከሜዳ ውጪ ወጥቶ ማሸነፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ለዚህም የተለያዩ አሰልጣኞች የተለያዩ ምክንያቶችን ሲያቀርቡ ይሰማሉ።
ብዙዎቹ ከሜዳ ውጪ ያሉ ሜዳዎች ለጨዋታ አመቺ አለመሆናቸውን ሲናገሩ እንደ አዳማ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ አስቻለው ኃ/ሚካኤል ገለፃ ደግሞ ከአዳማ እና ከአዲስ አበባ ውጪ የሚኖሩ ጨዋታዎች ላይ ዳኞች በተፅዕኖ እንደሚዳኙ እና በራስ መተማመን እንደማይታይባቸው ይገልፃሉ።

ከነዚህ ከሜዳ ውጪ ድል ከተመዘገበባቸው 15 ጨዋታዎች መካከል ወልዋሎ አ.ዩ. 3ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከሜዳ ውጪ ድል በመቀዳጀት ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ ሲዳማ ቡና፣ ወልቂጤ ከተማ እና መቐለ 70 እ. በእኩል 2ጨዋታዎችን በማሸነፍ ይከተላሉ። ስሑል ሽረ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ወላይታ ድቻ፣ ሰበታ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ (ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሸገር ደርቢ ሲጫወቱ ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና በመሆኑ) እኩል 1 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

ወላይታ ድቻ፣ ጅማ አባጅፋር እና ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በሜዳቸው እያንዳንዳቸው 2 ጊዜ የተሸነፉ ሲሆን ሰበታ ከተማ፣ ስሑል ሽረ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ መቐለ 70 እ.፣ ሲዳማ ቡና፣ ወልዋሎ አ.ዩ.፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ እያንዳንዳቸው 1 ጊዜ በሜዳቸው ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
ፋሲል ከነማ፣ ባህርዳር ከነማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ጅማ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር፣ እና ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻሉ ቡድኖች ናቸው።
እስከ ሊጉ ፍፃሜ ምን ያህል ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎችን ያሸንፉ ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ