“´ኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ ስኬታማ ከሆነባቸው ነገሮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ነው”……..መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

 

5ተኛው ዙር የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ የሩጫ ውድድር ዘንድሮ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የቡና ቤተሰቦችን በአንድነት እንቀድሞው በአንድ መድረክ ማገናኘት አልተቻለም፡፡
ሆኖም የዘንድሮው ውድድር ታስቦ እንዲውል የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ዛሬ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን በሚወክለው 12/12/12 ታስቦ የሚውለው ይህ ውድድር በርካቶች በያሉበት ሆነው የሩጫውን ቲሸርት ለብሰው እንደ በዓል የሚያከብሩት ይሆናል ተብሏል፡፡
የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ከተማ ይህንን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ’’ ኢትዮጵያ ቡና የገንዘብ ችግር ያለበት በመሆኑ ዝግጅቱ የክለቡን የገቢ አቅም ከፍ ከማድረጉ ባሻገር ወደ ፊት የሚያሻግረው በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው’’ ብለዋል፡፡

#ያለፈው ተሞክሮ

ኢትዮጵያ ቡና እንዲህ አይነት ውድድር ቀደም ሲል አራት ግዜ ያህል አካሄዷል፡፡ ’’´ይህ ደግሞ ክለቡን በገንዘብ ከመደገፍ በተጨማሪ በደጋፊዎቻችን መካከል ማህበራዊ ትስስር ከመፍጠር አኳያ ስኬታማ ሆነናል ያሉት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸን ከተማ ናቸው፡፡
የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ በበኩላቸው ’´ኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ ስኬታማ ከሆነባቸው ነገሮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ነው’’ ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ደጋፊዎችን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ በእለቱ የሚከናወን መርሃ ግብር ሲሆን ደም መለገስ፤ ችግኝ መትከልና የበጎ አድረጎት ስራዎችን መስራት ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡