በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ቀሪ አንድ ጨዋታ ዛሬ(ማክሰኞ) 11:30 ሲል ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና መከላከያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገናኝተው ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ ውጤት ማጠናቅ ችለዋል።

በጨዋታው ግብ የማግባት ቅድሚያ መውሰድ ችለው የነበሩት ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች ሲሆኑ በአ.አ ከተማ ዋንጫ ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ካሉሻ አልሀሰን በ34ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር። ከግቡ መቆጠር በኀላም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተጭኖ ለመጫወት ቢሞክርም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው መቅረብ የቻሉት መከላከያዎች ግብ ለማስቆጠር 2ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁባቸው። 47ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ መከላከያን ከሽንፈት አድኖታል።

በፕሪምየር ሊጉ የተደረጉትን 6 ጨዋታዎች ተከትሎ ወልድያ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር በ 3 ነጥብ እና በ 2 ግብ ልዩነት ፕሪምየር ሊጉን ሲመሩ ሽንፈትን ያስተናገዱት አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።
የፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ማለትም ቅ/ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ቀንና ሰዓት ወደፊት እንደሚገለፅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል።
አስተያየት ይስጡ