ትናንት ጅማሬውን ያደረገው እና እስከ ረቡዕ ድረስ የሚቆየው ሁለተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ቀጥሎ ውሏል። ሲዳማ ላይ ስሑል ሽረን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና የ4-1 ጣፋጭ ድል ማስመዝገብ ችሏል። በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች በይገዙ ቦጋለ የ34ኛ ደቂቃ ግብ መምራት ችለው የነበረ ሲሆን የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አጥቂ ዲዲየር ሊብሬ 44ኛው ደቂቃ ላይ ስሑል ሽረን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏቸው ነበር። ከእረፍት መልስ ሲዳማ ቡና ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው 4ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 49ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው አዲስ ግደይ ግብ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ወደ መሪነት መመለስ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ኮከብ ተጫዋች እጩ ውስጥ የነበረው ሐብታሙ ገዛኸኝ 59ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ 3-1 ማስፋት ችሏል። በዚህ ብቻ ያልተገቱት ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ 9ደቂቃዎች ሲቀሩት 81ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ በጨዋታው ለራሱ ሁለተኛ ለክለቡ ደግሞ አራተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና የውድድር አመቱን የመጀመሪያ 3ነጥብ ማሳካት የቻለ ሲሆን ስሑል ሽረ ደግሞ የመጀመሪያ ሽንፈቱ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም መሰረት ሲዳማ ቡና በ3 ነጥብ እና በ1 ንጹሕ ግብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ስሑል ሽረ በአንፃሩ በ3 ነጥብ እና በ2 የግብ እዳ 9ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሊጉን ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ወልዋሎ አ.ዩ. በ6 ነጥብ እና በ3 ንጹሕ ግብ መሪነቱን ሲይዝ ፋሲል ከነማ፣ ሐዋሳ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማና አዳማ ከተማ በእኩል 4ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ2ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለምንም ነጥብ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም እና የወልዋሎ አ.ዩ. ሰመረ ሐፍተይ በእኩል 3ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሲመሩ ሽመክት ጉግሳ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አዲስ ግደይ እና ዲዲየር ሊብሬ በእኩል 2ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ሊጉ ማክሰኞ እና ረቡዕ ሲቀጥል በብሔር ብሐረሰቦች በአል ምክንያት የተዛወሩት ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። ማክሰኞ 11:00 ሲል ቅ/ጊዮርጊስ በአ.አ ስቴዲየም ሰበታ ከተማን የሚያስተናግድ ሲሆን ረቡዕ በተመሳሳይ ሰአት ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባጅፋር ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ