ሲዳማ ቡና መደበኛ ልምምዱን በቴሌግራም ጀመረ፡፡

የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከመንግስት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሁሉንም ሊጎች ላልተወሰነ ግዜ ማገዱ ይታወሳል፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግ ክለቦች ተጨዋቾቻቸውን ወደ የቤታቸው ልከዋል፡፡

ይህን ካደረጉ ክለቦች መካከል አንዱ ሲዳማ ቡና ሲሆን ዛሬ ተጨዋቾቹ በያሉበት ሆነው መደበኛ ልምምድ ሰርተዋል፡፡ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ይህን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው ማብራሪያ ዛሬ (13-08 2012 ዓ.ም) ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ለ45 ደቂቃዎች ያህል ሰርተዋል፡፡ የልምምዱ ይዘት በፅሁፍና በተንቀሳቃሽ ምስል ለሁሉም ተጨዋቾች በቴሌግራም ተልኮ መስራታቸውን አሰልጣኙ ጨምሮ ነገሮናል፡፡
የትናንትናው (13-08 2012 ዓ.ም) ልምምድ ኢንዱራንስ ላይ ያተኮረ ነበር ያለው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በዛሬው እለት (በ14-08-2014 ዓ.ም) ደግሞ ከኳስ ጋርና ከኳስ ውጪ የጥንካሬ ስራችን እንደሚሰሩና በዚህ መንገድ የሚሰጠው መደበኛ ልምምድ እስከ ቅዳሜ ይዘልቃል ብሏል፡፡

የቡድኑ አምበል አዲስ ግደይ በበኩሉ ’’ ምንም እንኳን ሁላችንም በያለንበት እንቅስቃሴ እያደረግን ቢሆንም አሰልጣኛችን ያመጣልን አማራጭ ሁላችንም ተመሳሳይ ዝግጅት እንድንሰራ የሚያደርገን በመሆኑ በጥሩ ሁኔታ ተቀብለን ሰርተናል፡፡ ወደፊትም በሚሰጠን አቅጣጫ መሠረት ስራችንን እንቀጥላለን’’ ሲል አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡