በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል 6ቱ ዛሬ የተደረጉ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ጅማ ላይ ጅማ አባጅፋር ከቅ/ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ አንዱ ነው። ይህን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

9:00 ሲል በጀመረው ጨዋታ ጅማ ላይ ጅማ አባጅፋር ቅ/ጊዮርጊስን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። እስከ 4ኛው ሳምንት ድረስ ጅማ አባጅፋር ድል ማስመዝገብ ተስኖት ቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት አቅቶት የተገናኙበት ወቅት በመሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ድል ለማግኘት ያደረጉት ጨዋታ ነበር። ጥሩ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የመጀመሪያውን ግብ ለማግኘት 16ደቂቃዎች ነበር የፈጀባቸው። 16ኛው ደቂቃ ላይ ብዙአየሁ እንደሻው ግብ አስቆጥሮ ጅማዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ 61ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ ግብ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 7ደቂቃዎች ሲቀሩት የጅማ አባጅፋሩ አምረላ ደልታታ ያስቆጠራት ግብ ጅማ አባጅፋር በዘንድሮው የውድድር አመት የመጀመሪያ ድሉን እንዲያስመዘግብ ረድቶታል። ውጤቱንም ተከትሎ ጅማ አባጅፋር በ6ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተጋጣሚው ቅ/ጊዮርጊስም በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሊጉን አንድ ጨዋታ የሚቀረው ወልዋሎ አ.ዩ. በ10 ነጥቦች ሲመራ ሲዳማ ቡና በ9 እንዲሁም ባህርዳር ከተማ በ8ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም፣ የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ፣ የባህርዳር ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በእኩል 4 ግቦች ሲመሩ አዲስ ግደይ፣ ዳዋ ሁቴሳ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ይገዙ ቦጋለ እና ሰመረ ሀፍተይ በእኩል 3ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
አስተያየት ይስጡ