በ6ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ(ቅዳሜ) 6ጨዋታዎች ተደርገዋል። ከነዚህ ጨዋታዎች አንዱ የነበረው እና በሲዳማ ቡና እና ድሬደዋ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በእንግዳዎቹ ድሬደዋ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ በነበሩት የመጀመሪያው አጋማሽ ከጅምሩ የግብ አጋጣሚዎች የተስተዋሉበት ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ 1ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ያገኘውን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከዚህ ሙከራ 1ደቂቃ በኋላ ሚካኤል ሀሲሳ ያሻገረለትን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ ግብነት ቀይሮት ሲዳማ ቡና 1-0 መሪ መሆን ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም ሲዳማ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ድሬደዋ ከተማ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርቶዋል። ግቡ ከተቆጠረ 9ደቂቃዎች በኋላ 11ኛው ደቂቃ ላይ የድሬደዋ ከተማው ግዙፍ አጥቂ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር እንግዳዎቹን ድሬደዋ ከተማን አቻ በማድረግ የመጀመሪያው አጋማሽ በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጨዋቾች ለውጥ አድርገው የቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች ሚካኤል ሀሲሳን አስወጥተው ዳዊት ተፈራን በማስገባት መሀል ሜዳውን ለመቆጣጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ለአጥቂዎች ሲደርሱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። 67ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ፍሬድ ሙሽንዲ ወደ ግብነት ቀይሮት ድሬደዋ ከተማን 2-1 እንዲመራ አስችሎታል። ሆኖም ግን ግቧ ከመቆጠሯ አስቀድሞ ረዳት ዳኛው ምልክት አሳይቷል በሚል የሲዳማ ቡና የቡድን አመራሮች ክስ አስይዘው ጨዋታው ቀጥሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4ደቂቃዎች ሲቀሩት 86ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ መቶት አምክኖታል።

ውጤቱንም ተከትሎ ድሬደዋ ከተማ በ7ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅ ቀጠና መውጣት ሲችል ተሸናፊው ሲዳማ ቡና ደግሞ በ9ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሊጉን ፋሲል ከተማ እና ወልዋሎ አ.ዩ. 11 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተለያይተው አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆኑ መቐለ 70 እንደርታ በ10 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም በ6 ግቦች ሲመራ የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ፣ የባህርዳር ከተማዎቹ ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ፣ የፋሲል ከተማው ኦሴይ ማውሊ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነ በእኩል 4 ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
አስተያየት ይስጡ