በ2018 የቶታል አፍሪካ ኮንፈደሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ የዛንዚባሩን ዚማሞቶን ዛሬ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም አስተናግዶ በጃኮ አረፋት ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ባለ ሜዳዎቹ ወላይታ ዲቻዎች ኳስን መስርተው መጫወት ቢችሉም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ የቻሉት እንግዳዎቹ ዚማሞቶዎች ነበሩ በ4ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ የዚማሞቶው ሀኪኖ ካሚስ በጭንቅላት የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ ሙባረክ ሽኩር በቀላሉ አውጥቷታል። በ13ኛው ደቂቃ የዚማሞቶ አሞር ሀጂ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ነያንግ ኦተማን አጊንቶ የመታት ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታለች። ባለ ሜዳዎቹ ወላይታ ዲቻዎች ኳስን መስርተው በመጫዎት በአንድ ሁለት ቅብብል እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ጫና መፍጠር ቢችሉም ለግብ የቀረበ ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም። በ25ኛው ደቂቃ በግራ መስመር የዚማሞቶው ሱሌማን ሰኢድ የወላይታ ድቻ አጥቂ ጃኮ አራፍት ላይ ጥፍት ሰርቶ የተገኘው ቅጣት ም በዛብህ መለዮ ወደግብ አሻምቶት ሐይማኖት መላኩ በጭንቅላት ገጭቶት የዚማሞቶ ተከላካዮች በቀላሉ አዉጥተውታል፡፡

በ26ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር እሸቱ መና ያሻገረውን የዚማሞቶ ተከላካይ ሀሰን ስዮን ፍ.ቅ.ም ክልል ውስጥ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን ፍ.ቅ.ም ጃኮ አራፋት ወደ ግብ ቀይሯት ባለ ሜዳዎቹን መሪ አድጓቸዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ወላይታ ዲቻዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ32ኛው ደቂቃ እሸቱ መና ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ጃኮ አራፍት አግኝቶ ሞክሮት ወደ ውጪ ወጥታለች። በዚሁ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንግዳዎቹ ዚማሞቶዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሲሆን በረጅም ኳስ ወደ ግብ በመድረስ ጫና ፈጥረው ተጫውተው ወደግብ መድረስ ቢችሉም የወላይታ ዲቻው ግብ ጠባቂ ወንደሰን ገረመው አምክኖባቸዋል። በአንፃሩ ወላይታ ዲቻዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተከላክለው በመጫወት በመልሶ ማጥቃ ወደ ግብ በመድረስ ሙከራዎችን አድርገዋል በ51ኛው ደቂቃ የዚማሞቶ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ዳግም በቀለ ከግቡ ቅርብ ርቀት ያገኛትን ኳስ መቷት በግቡ አናት ላይ ወጥታለች። በመሀል ሜዳ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ሀይማኖት ወርቁ ከመሀል ሜዳ በርቀት ያሻገረለትን ኳስ ጃኮ አረፋት ሳይጠቀምበት ግብ ጠባቂው ያወጣበት ኳስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወላይታ ዲቻዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ተከላክለው ሲጫወቱ በአንፃሩ ዚማሞቶዎች ወደ ፊት ተጭነው ተጫውተዋል። ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች 1ለ0 አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ በድምር ውጤትም 2ለ1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል፡፡ ወላይታ ድቻ በቀጣዩ ዙር ከግብፁ ሀያል ክለብ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ — ወላይታ ድቻ
“ከእረፍት በፊት የነበረው ጨዋታ እጅግ በጣም ጥሩ ነበር። ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። ከእረፍት በኋላም ተነቃቅተን ገብተን ነበር፤ ነገር ግን መቀዛቀዝ ታይቶብናል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ሞሱማ አብዱላሂ —- ዚማሞቶ
“እነሱ(ወላይታ ድቻዎች) በጨዋታው ከፍፁም ቅጣት ምቱ ውጪ አንድም ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። እኛ ሁለት ጊዜ የግቡ ቋሚ ኳስ መልሶብናል። የኛ ቡድን ትልቁ ችግር የኳስ ቁጥጥር እና ታክቲካሊ ዲስፕሊን አለመሆን ነበር። በአጠቃላይ እድለኞች አልነበርንም።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየት ይስጡ