በኢትዮጵያ ኘሪሜየር ሊግ 13ኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ አዳማ ላይ አዳማ ከተማን ከ ወልዋሎ.አ.ዩ አገናኝቶ በባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው ጅማሬ በፊት በርካታ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች ለወልዋሎ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በዚህ አቀባበልም የወልዋሎ የክለብ አመራሮች፣ ተጫዋቾች እና መላው ደጋፊ ደስታውን ሲገልፅ መመልከት ተችሏል።

ጨዋታው ሲጀምር በአዳማ ከተማ በኩል 4-3-3 አሰላለፍ ሲገቡ በወልዋሎ አዲግራት በኩልም በተመሣሣይ ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
የጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች መሐል የሜዳው ክፍል ላይ ያማከለ የኳስ ፍሰት በሁለቱም ቡድኖች ተግባረዊ ሲደረግ ተስተወሏል፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ ወልዋሎ አ.ዩ ያገኘውን ቅጣት ምት ሮቤል ግርማ መቶት ጃኮ ፔንዜን ተክቶ የገባው ተስፈኛው የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ አድኗታል። 28ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው በረከት ደስታ ለግብ የቀረበ ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከዚህች ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ ለአዳማ ከተማ የተገኘችውን ቅጣት ምት በግምት ከ17 ሜትር ዳዋ ሁቴሳ አስቆጥሮ አዳማ ከተማ 1-0 እንዲመራ አስችሎታል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ብዙም ሳቢ ያልሆነ እና መሐል ላይ የኳስ ፍሰት የነበረው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 1-0 መሪነት ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል፡፡
በ2ኛው አጋማሽ እንደ ተጀመረ 49ኛው ደቂቃ ላይ ወልዋሎ አዲግራት ከመስመር የተገኘችውን ኳስ ከድር ሳሊህ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ በመገኘቱ ጎሏዋ ልትሻር ችላለች። የሀይል አጨዋወት በተስተዋለበት ሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክ/ጊዜ አዳማ ከተማ በጨዋታ ብልጫ እና ወደ ግብ በመድረስ የበላይ ነበሩ፡፡ 62ኛው ደቂቃ ላይ ሱሊማን መሀመድ ያስቆጠራት ግብ ፋውል ተሰርቷል በሚል የእለቱ አርቢትር አሸብር ሰቦቃ ሸረዋታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ሆኖም ውጤታማ መሆን የቻሉት አዳማ ከተማዎች ነበሩ። 74ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተሻገረውን ኳስ የአዳማ ከተማው ድንቅ አማካይ፡ከነዓን ማርክነህ ግብ ጠባቂውን በማለፍ 2ኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ አዳማ ከተማ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሲሳይ ቶሊን በኤፍሬም ዘካሪያስ በመቀየር 3ኛ ግብ እንዲቆጠር ምክንያት ሆኗል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 11 ደቂቃዎች ሲቀሩት 79ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው በረከት ደስታ ከመሀል የሜዳ ክፍል የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሆኔታ ቺፕ በማድረግ አስቆጥሮ 3-0 እንዲመሩ አስችሏል፡፡ ከዚህም በኋላ ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ይህንን ውጤትም ተከትሎ አዳማ ከተማ ከመሪው ደደቢት በ4 ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ መቀመጥ ሲችል በሰሞንኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ ያለው ወልዋሎ.አ.ዩ በአንፃሩ ከወራጅ ቀጠና በ4 ነጥቦች ብቻ ርቆ በ13 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ~ አዳማ ከተማ
ባለፈው ሰምንት ነጥብ መጣለችን ተከትሎ ውጤቱን እንፈልገው ነበር ። ከተጫዋቾቼ ጋር በተነጋገርነው መሰረት በሁለቱም የጨዋታው አጋማሾች ልጆቼ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል። ከለፉት ጨዋታዎች ያልነበሩ ተጨዋቾቻችን ከጉዳት አገግመው ጥሩ ውጤት እንድናስመዘግብ አግዞናል።
አሰልጣኝ ሀብቶም ኪሮስ ~ወልዋሎ አዲግራት ዮንቨርሲቲ
“በጨዋታው አዳማ ከተማዎች ከኛ የተሻሉ ሆነው ሳይሆን ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ረገድ የተሻሉ ስለነበሩ አሸንፈውናል። የሙሉአለም በጉዳት ምክኒያት አለመኖር የተጫዋች ለውጥ እንድናደርግ አስገድዶናል። በአሰላለፉ ላይ ግን የቅርፅ ለውጥ አልነበረንም።”
አስተያየት ይስጡ