በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ1ኛ ሳምንት ተስተካካይ 1ጨዋታ ዛሬ አ/አ ስታድየም ላይ ተከናውኖ ቅ/ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ተገናኝተው ጨዋታቸውን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀዋል።
እንደተለመደው ሞቅ ባለ የደጋፊዎች ዜማ እና ጭፈራ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ነበር ሙከራ ማስተናገድ የጀመረው። 1ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ ምንተስኖት አዳነ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ውጭ የወጣበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ በሜዳው በስተግራ በኩል የተገኘውን ቅጣት ምት የድሬዳዋ ከተማው አማካይ ወደ ጎል አሻምቶት የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ኳሱን በግሩም ሁኔታ አውጥቶታል። ከዚህ ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ 15ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሶቹ አብዱልከሪም መሃመድ እና አቡበከር ሳኒ በአንድ ሁለት ቅብብል በግቡ በስተቀኝ መስመር ይዘውት የገቡትን ኳስ አብዱልከሪም መሃመድ ወደ ጎል ቢያሻማውም ኳሱ በተከላካዮች ተመልሷል። 20ኛው ደቂቃ ላይ አብዱከሪም ኒኪማ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ኳስ አበባው ቡጣቆ ወደ ጎል ቢያሻማውም ኳሱ በተከላካዮች ተመልሶ የመዓዘን ምት ሊሆን ችሏል።
28ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከነማዎች ከግቡ ርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ኩዋሜ አትራም በቀጥታ መቶት ግብ በማስቆጠር እንግዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ ቅ/ጊዮርጊሶች አቻ ለመሆን ካላቸው ጉጉት የተነሳ ጨዋታውን ተረጋግተው መጫወት ሳይችሉ ቀርተዋል። ድሬዳዋ ከነማዎች በአንፃሩ በተደጋጋሚ ከርቀት አደገኛ ሙከራዎችን ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ድሬዳዋ ከነማዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ሰዓት ለመግደል ጥረት ሲያደርጉ የነበረበት ሂደት የተስተዋለ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ከቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተቃውሞን አስከትሏል። ከዚህ በኋላም ይሄ ነው የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ቅ/ጊዮርጊሶች ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው ሲጫወቱ ድሬዳዋ ከተማዎች በአንፃሩ ውጤቱን ለማስጠበቅ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ቅ/ጊዮርጊሶች በሜዳው በስተቀኝ መስመር ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ አበባው ቡጣቆ በጥሩ ሁኔታ ቢያሻማውም የፈረሰኞቹ ተጨዋቾች ዝግጁ ባለመሆናቸው ኳሱ ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህች ሙከራ 6ደቂቃዎች በኋላ 61ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ቅ/ጊዮርጊሶች ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ መትቶ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ መነቃቃት ያሳዩት ድሬዳዋ ከተማዎች 72‘ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክተው ከመሃል ሜዳ በረጅሙ የመቱት ኳስ እንዲሁም 74ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ይዘውት የመጡትን ጥሩ ኳስ ወደ ግብ ሞክረውት ወደ ውጭ በመውጣቱ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። የመደበኛው የጨዋታ ግዜ ተጠናቆ የተጨማሪ ሰዓት ላይ 92ኛው ደቂቃ ላይ ቅ/ጊዮርጊሶች ከርቀት ያገኙቱን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ ወደ ጎል አሻምቶ አዳነ ግርማ በጭንቅላቱ ቢገጨውም የድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በግሩም ሁኔታ መልሶበታል። በዚህም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ቅ/ጊዮርጊስ ወደ መሪው ለመጠጋት የነበረውን እድል አምክኗል።
አስተያየት ይስጡ