መነሻ ገጽ ሪፖርት ሪፖርት | ቅ/ጊዮርጊስ በውጤት ቀውስ ውስጥ እሚገኘውን አርባምንጭ ከተማን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል 
ሪፖርትቅዱስ ጊዮርጊስአርባምንጭ ከተማየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

ሪፖርት | ቅ/ጊዮርጊስ በውጤት ቀውስ ውስጥ እሚገኘውን አርባምንጭ ከተማን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል 

አጋራ
አጋራ

በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታ ቅ/ጊዮርጊስ በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።
10:05 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የቅ/ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በቅ/ጊዮርጊስ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። ለቅ/ጊዮርጊስ ጎሎቹን ኢብራሂም ፍፋና፣ አብዱልከሪም ኒኪማ እና ምንተስኖት አዳነ አስቆጥረዋል።
እጅግ በቀዘቀዘ እና በተዳከመ ስሜት የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ይሄ ነው የሚባል የረባ እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ለመጠናቀቅ ተገዷል። ቅ/ጊዮርጊስ ጨዋታውን በ 4-3-3 ሲጫወት አርባምንጭ በበኩሉ በ4-5-1 የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ ገብቷል። እንደወትሮው በደመቀ የደጋፊዎች ዝማሬ እና ድጋፍ የታጀበው ጨዋታ 4ኛው ደቂቃ ላይ የቅ/ጊዮርጊሱ አጥቂ ኢብራሂም ፍፋና በግራ እግሩ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቷል።

በጨዋታው 7ኛ ደቂቃ ላይ በስታዲየሙ የታደሙት የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ለቀድሞ የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታላቅ እና ድንቅ ተጫዋች እንዲሁም የመጀመሪያው የካፍ ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ በመቆም ለ1 ደቂቃ ያህል በማጨብጨብ አስታውሰውታል። መንግስቱ ወርቁ ከ7 ዓመት በፊት ታህሳስ 7 2003 ዓ.ም ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

16ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጩ ምንተስኖት አበራ ከርቀት ወደግብ የሞከረው ኳስ ወደውጭ ወጥቶበታል። በዚህኛው አጋማሽ የአርባምንጭ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ በመውደቅ ሰዓት ለማባከን ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት የእለቱ ዳኛ ተጨማሪ 2 ደቂቃዎች ሲያሳዩ ከቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች በጥሩ የመከላከል ብቃት እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

በዚህም የተነሳ የአርባምንጭ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ(Offside) ሲሆኑ ተስተውለዋል። ሆኖም ይህ የመከላከል ብቃት መዝለቅ የቻለው እስከ 43ኛው ደቂቃ ድረስ ነበር። ኢብራሂም ፎፋና ከአርባምንጭ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ መቶት የመጀመሪያውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ሰዓት አዳነ ግርማ የአርባምንጭ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ድንቅ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

የቅ/ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ ደምቆ በዋለበት በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው መቅረብ የቻሉት አርባምንጭ ከተማዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅይታደስ አበበ ከረጅም ርቀት የሞከረውን ኳስ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ይዞታል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው የአርባምንጩ ብርሀኑ አዳሙ በድንቅ ሁኔታ ተከላካዮቹን አታሎ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያሻገረውን ኳስ አጥቂዎቹ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ያሻገረውን የማዕዘን ምት ኢብራሂም ፎፋና በግንባሩ ሞክሮት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ቅ/ጊዮርጊሶች አዳነ ግርማን በማስወጣት ምንተስኖት አዳነን ቀይረው በማስገባት የጨዋታውን ሂደት ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረግ ችለዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 7ደቂቃዎች ሲቀረው 83ኛው ደቂቃ ላይ ከአበባው ቡጣቆ የተቀበለውን ኳስ አብዱልከሪም ኒኪማ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮታል።


ከ6 ደቂቃዎች በኋላ 92ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ 3ኛውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በቅ/ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የቅ/ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

“ጎል እስክናገኝ ድረስ ጨዋታው ከባድ ነበር። ተጋጣሚያችን ወደኋላ አፈግፍጎ ስለሚጫወት እንደ ፈለግነው የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻልንም። አሁንም በማጥቃቱ ላይ ጠንክረን መስራት እንዳለብን ይሰማናል። የኛ ቡድን 3ኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጫዋቾቻችን ከኳስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ደካማ ነው። እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ እንፈልጋለን ስለዚህ ችግራችንን ማሻሻል ይጠበቅብናል።” በማለት  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው

“በመጀመሪያው አጋማሽ እስከ 40ኛው ደቂቃ ድረስ አቅደነው የገባነው ታክቲክ የተሳካ ነበር። በኛ ቡድን በኩል የተከሰቱት የማርኪንግ ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል። ቅ/ጊዮርጊሶች ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው አሸንፈውናል። ለመከላከል ብለን ወደሜዳ አልገባንም። በመስመር በኩል ክፍተት እንዳያገኙ ጥረት አድርገናል። ብዙ የማጥቃት ባህሪይ ያላቸው ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ነበሩን ነገር ግን የቅ/ጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል ማስከፈት አልቻልንም።”

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

1. ፉአድ ኢብራሂም (ኢትዮጵያ ቡና) : ከታች በተጠቀሱት 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ድንቅ የቅጣት ምቶች በነበሩት ጨዋታ ነገሌ ሲያሸንፍ ሀዋሳ በወልዋሎ ነጥብ ጥሏል

7 ጎሎች እና ሁለት ድንቅ የቅጣት ምት ጎሎች በነበሯቸው ሁለት ጨዋታዎች ነገሌ...