ወላይታ ድቻ በግብጹ ዛማሌክ ላይ ያስመዘገበው ድል አስመልክቶ ቡድኑ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ የአየር ማረፊያ ሲደርስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የወጣቶችን ስፖርት ቢሮና የወላይታ ልማት ማህበር የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።
ወላይታ ድቻ ቡድን በኢትዮጵያ ሆቴል አቀባባል የተደረገለት ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙ የክለቡ ደጋፊዎችም በዚያው ተገኝተው ቡድናቸውን በዝማሬ አበረታተዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የሙለጌ አስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ሙስጠፋ አወልና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ክለቡ ላስመዘገበው ድል በቅደም ተከተል የ200 እና የ150 ሺህ ብር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የደቡብ ክልል ነዋሪዎች ከ350 ሺህ ብር በላይ ለክለቡ ያበረከቱ ሲሆን ሌሎች ግለሰቦችም ቃል ገብተዋል።

የወላይታ ድቻ ቡድን ልዑክ ከሰዓት ወደ ሐዋሳ ያቀና ሲሆን በሀዋሳ ስታዲየም ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።ዛሬ ማለዳም ወደ ሶዶ እሚያቀና ሲሆን ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቡድኑ ዛሬ በካይሮ በሚካሄደው የእጣ አወጣጥ ስነ ስርአት ቀጣይ ተጋጣሚውን የሚያውቅ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ