የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት የዕለተ ቅዳሜ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ በሚደረጉ 3 ጨዋታዎች ጅማሬውን ያደርጋል። በአ/አ 1 ጨዋታ ሲደረግ በክልል 2 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል።
አ/አ ላይ 10፡00 ሲል ቅ/ጊዮርጊስ ከ መከላከያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በ8ኛው ሳምንት ቅ/ጊዮርጊስ ወደ አዲግራት ተጉዞ ከወልዋሎ አ.ዩ. ጋር ተጫውቶ ያለግብ አቻ ተለያይቶ በመመለስ መከላከያ በአንፃሩ ምንይሉ ወንድሙ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፎ ነው ለዛሬው ጨዋታ የሚገናኙት። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቅ/ጊዮርጊስ ካደረጋቸው 6ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ 3ቱን በማሸነፍ 3ቱን አቻ በመውጣት በ12 ነጥቦች ከመሪው ደደቢት በ4 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በአንፃሩ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች 2 በማሸነፍ 3ቱን አቻ በመውጣት 3ቱን ተሸንፎ ማሳካት ከነበረበት 24 ነጥቦች 9ኙን ብቻ ሰብስቦ 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በቅ/ጊዮርጊስ በኩል ረጅም ጉዳት ላይ የሚገኙት ሳላዲን ሰይድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ አሁንም ለቡድናቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን በሸገር ደርቢ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ ጉዳት ያስተናገደው አሜ መሐመድም የመግባቱ ነገር አሁንም አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ከላይ ከተጠቀሱት ተጫዋቾች ውስጥ አማካዩ ታደለ መንገሻ በቅርቡ ልምምድ እንደሚጀምር ተገልጿል። ከእነዚህ በተጨማሪ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ ቡድኑ በትናንትናው እለት ባደረገው ቀለል ያለ ልምምድ ላይ ያልተሳተፈ መሆኑን ያገኘናቸው ምንጮች ያስረዳሉ። በመከላከያ በኩል ሳሙኤል ታዬ እና አዲሱ ተስፋዬ በጉዳት ሳሙኤል ሶሊሶ ደግሞ በቅጣት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ላይ የማይኖሩ ይሆናል።
በሌላ ጨዋታ በክልል ከሚደረጉት 2ጨዋታዎች አንዱ የሆነው ጅማ ላይ የሚደረገው የሁለቱ አዲስ አዳጊዎች ጅማ አባጅፋር እና ወልዋሎ አ.ዩ. የሚያገናኝ ነው። በጥሩ ግስጋሴ ላይ የሚገኙት እነዚህ 2 ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት እየተጠበቀ ነው። በ8ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋር ወደ አርባምንጭ ተጉዞ እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ በአርባምንጭ ከተማ 1-0 ሲመራ ቆይቶ በቀሩት 15 ደቂቃዎች ውስጥ በኦኪኪ አፎላቢ ሀትሪክ ከሜዳው ውጪ ጣፋጭ 3ነጥቦች ሰብስቦ መመለስ ችሏል። ይህ ውጤት ለአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ስንብት አንዱ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። ውጤቱንም ተከትሎ ጅማ አባጅፋር በ11 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወልዋሎ በአንፃሩ በሜዳው የአምናውን ሻምፒዮን ቅ/ጊዮርጊስን በሜዳው አስተናግዶ ያለምንም ግብ አቻ መለያየቱ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ወልዋሎ.አ.ዩ ከጅማ አባጅፋር ጋር በእኩል 11 ነጥብ ነገር ግን በ1 ግብ ክፍያ ዝቅ ብሎ 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በጅማ አባጅፋር በኩል አማካዩ ሄኖክ ኢሳያስ የማይኖር ሲሆን ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት አሸናፊ ሽብሩ እና ዝናቡ ባፋ አሁንም ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል። በወልዋሎ በኩል ከመከላከያ ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው እና 4ጨዋታዎችን የተቀጣው እንየው ካሳሁን በቅጣት የማይገባ ይሆናል።

በሌላ የዛሬ ጨዋታ ድሬ ላይ 09፡30 ሲል ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው(ሞሪንሆ) ጋር በስምምነት የተለያየው ድሬደዋ ከተማ ከፋሲል ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። በውጤት መዋዠቅ ውስጥ የሚገኘው ድሬደዋ ከተማ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር በስምምነት መለያየቱን ተከትሎ በምክትል አሰልጣኙ ስምዖን አባይ እየተመራ ወደሜዳ የሚገባ ይሆናል። እስካሁን ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 1ብቻ አሸንፎ በ4ቱ አቻ ተለያይቶ በ2ቱ ተሸንፎ 7ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። እስካሁን ሽንፈት ካላስተናገዱት 3ቡድኖች አንዱ የሆነው ፋሲል ከተማ በአንፃሩ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 2ቱን በማሸነፍ በ5ቱ አቻ በመውጣት 1 ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከመሪው ደደቢት በ5 ነጥቦች ዝቅ ብሎ 11ነጥቦች ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ከድሬደዋ በኩል ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ እና አማካዩ ሀብታሙ ወልዴ እንዲሁም ከፋሲል ከተማ በኩል ኤፍሬም አለሙ እና ያሬድ ባዬህ በጉዳት ለቡድኖቻቸው ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ