*….ተጠርጣሪው ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል…
ዛሬ ጠዋት የጠፋው የወልቂጤ ከተማ ተጨዋቾች ንብረት በቡድን አባላቱ ከፍተኛ ርብርብ መገኘቱ ታውቋል።
ተጨዋቾቹ ከጠዋት ልምምድ ሲመለሱ ገንዘብ፣ ሰአት፣ በርካታ ሞባይሎች ፣ ሀብልና ጌጣጌጦች የጠፋ ሲሆን ተጨዋቾቹ ወዲያውኑ ለአዳማ ከተማ ፖሊስ በማሳወቅ የከሰአት ልምምዳቸውን በማቋረጥ ተጠርጣሪ የነበረውን ሆቴሉ ውስጥ ተጠግቶ ሲሰራ የነበረውን ተጠርጣሪ ለመያዝ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከክለቡ ውስጥ አዋቂ በተገኘ መረጃ ተጠርጣሪው በሰረቀው ስልክ መደወሉን ተከትሎ ተጨዋቾቹ ባገኙት መረጃ ፍለጋቸውን ቀጥለው ተጠርጣሪው ከአዳማ ወጥቶ ወደ ሀዋሳ በተቃረበበት ወቅት ደርሰውበት ከአንድ ስልክ ውጪ ሁሉም የጠፋው ንብረት ተመልሶ ለባለቤቶቹ እንዲደርስ ተደርጓል። ተጨዋቾቹም ተጠርጣሪውን ለአዳማ ፖሊስ ማስረከባቸው ታውቋል።
ይህን መሰል ፈተና የገጠማቸው የወልቂጤ ከተማ ተጨዋቾች በ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር የፊታችን ዓርብ ከፋሲል ከነማ ጋር ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።