“የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተጣራ 120 ሺህ ብር ደመወዝና የሁለት ዓመት ኮንትራት ቢፈቅድልኝም ተፈጻሚ ሳይሆን ግን ሁለት ወር አልፎኛል”
አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል
/ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ/
‘”የቀረበለትን ውል አልቀበልም ያለው አሰልጣኙ ራሱ ነው”
አቶ ባህሩ ጥላሁን
/ የኢት.እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ /
- ማሰታውቂያ -
“ለወሳኙ ፍልሚያ የምንሄደው ሰው ሜዳ ነው ይሄ ቡድን ደግሞ በሰው ሜዳ አሸንፎ መምጣት የሚችል መሆኑን አሳይቷል” ሲሉ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ተናገሩ።
አሰልጣኙ የፊታችን ቅዳሜ ከሞሮኮ አቻቸው ጋር ባለው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ዙሪያ ዛሬ በፌዴሬሽኑ አዳራሽ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ” ቡድኑ ባለፉት 23 ቀናት ሲዘጋጅ ቆይቷል 31 ተጨዋቾች ጠርተን 23 በማስቀረትና አዳዲስ ፊት በማምጣት ስንዘጋጅ ቆይተናል ከ23ቱ ተጨዋቾች አንድ ተጨዋች ብቻ በፓስፖርት ምክንያት በመቅረቷ 22 ተጨዋቾችን በመያዝ 35 ሜዳ እና በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምዳችን ስንሰራ ቆይተናል። በዚህ አጋጣሚ ሁለቱንም ሜዳ የፈቀዱልንና አካላት እናመሰግናለን አዲስ አበባ ስታዲየምን የፈቀዱልን የባህሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ደኤታ የሆኑትን አምባሳደር መስፍን ቸርነትን አመሰግናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
“ጥሩ ዝግጅት ብናደርግም ሙያዬ በሚፈቅደው ደረጃ ግን አይደለም ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጠይቄያለሁ
ሞሮኮ ከሰባት ቀን በፊት አስቀድመን ሄደን እንዘጋጅ ብዬ ነበር ሁለቱም አልሆነም ከአንድ ወንድ ቡድን ጋር ብቻ ነው የተጫወትነው የምንሄደውም ከሶስት ቀን በፊት ነው ….ፕላን ኤ ቢቀር ፕላን ቢ ብለን ተዘጋጅተን የመጨረሻውን ልምምድ አድርገን ዛሬ ወደ ሞሮኮ እናቀናለን ሞሮኮ ግን በ10 ቀን ውስጥ ከአልጄሪያና ቦትስዋና ጋር ተጫውታና ተዘጋጅታ ነው የምትገጥመን..” ያሉት አሰልጣኙ ” ያም ቢሆንም የምንሄደው ሰው ሜዳ ነው ይሄ ቡድን ደግሞ በሰው ሜዳም ቢሆን አሸንፎ መምጣት የሚችል መሆኑን አሳይቷል” ሲሉ አስረድተዋል።
ስለ አራት አመት ቆይታቸው የተናገሩት አሰልጣኝ ፍሬው “በቆይታዬ ከ31 ተጨዋቾች በላይ አምጥቻለሁ በሀሳብ የሚጫወት ቡድንም እንዲገነባ ትልቅ ስራ ሰርቻለሁ በናይጄሪያ ጨዋታ ከነበሩ 11 በጋና ጨዋታ ከነበሩ መሃል 7 ተጨዋቾች ተካተዋል በስራዬ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን የብዙ አመት ግልጋሎት የሚሰጡ ተጨዋቾችን በማፍራቴ የልማት ስራ እንደሰራሁና ሀገሬን የምጠቅምበት እድል እንደፈጠርኩ ይሰማኛል በዚህ ምክንያት በእራት አመት ቆይታዬ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል” ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል።
አሰልጣኙ ውላቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ሳይታደስ ዛሬ 20 ቀናት አልፏቸዋል በዚህ ዙሪያ ምን ምላሽ እንዳላቸው የተጠየቁት አሰልጣኙ “ውሌን ከጨረስኩ ወደ 16 ወይም 18 ቀናት አልፎኛል በኔ በኩል ማቅረብ ያለብኝን አቅርቤያለሁ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተጣራ 120 ሺህ ብር ደመወዝና የሁለት አመት ውል ፈቅዶልኝ ወጥቻለሁ ተፈጻሚ ሳይሆን ግን ወራቶች አልፎኛል በኔ በኩል ውል አልፈረምኩም ብዬ ትቼ ግን አልወጣም ሀገሬን፣ ተጨዋቾቼንና ሙያዬን አከብራለሁ የተቀጠርኩት ከ20 አመት በታች ቡድን እንደመሆኑ መገምገም ካለብኝ በዚህ ቡድን ውጤት ብቻ ነው ተቋሙም ሙያዬን ሀገሬን ተጨዋቾቼን አስቦ ኮንትራቴን እንደሚሰጠኝ እጠብቃለሁ አሁንም ሀገሬን አስቀድሜለሁ ለኔ ፊርማ ሁለተኛ ጉዳይ ነው በቀጣይ የማወጣቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ግን ይችላሉ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የስነ ምግብ ባለሙያው ድንገት ቡድኑን ትተው ስለመሄዳቸው የተጠየቁት አሰልጣኙ ” የስነምግብ ባለሙያው ማን እንዳመጣውም ለምን እንደቀረም አላውቅም ያመጣው ወገን ቢጠየቅ ይሻላል” ሲሉ አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህን የአሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል መግለጫ ተከትሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን ግን የአሰልጣኙን ሃሳብ አስተባብለዋል። ከስነ ምግብ ባለሙያው ጋር ተያይዞ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ባህሩ ” ቡድኑ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ሙሉ ድጋፍ እያደረግን ነው የስነ ምግብ ባለሙያው አስፈላጊነትም ሳይታለም የተፈታ ነው ስናመጣቸውም ከአሰልጣኙ ጋር ቁጭ ብለን ተነጋግረንበት መመሪያያ ተሰጥቶ ነው ወደ ስራ የገቡት … ከምግብ አቅርቦቱ ጋር ተያይዞ የተጨዋቾቹ አቀባበል ጋር ክፍተት ስለነበርና አሰልጣኙም የምጠብቀውን ድጋፍ አላደረጉልኝም ብለው ነግረውን ቡድኑን ተለይተው እንደወጡ እናውቃለን ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከኮንትራቱ ጋር ተያይዞ ዋና ስራ አስፈጻሚው በሰጡት ምላሽ ” ነሀሴ 30/2015 በአሰልጣኙ ውል ዙሪያ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ቁጭ ብሎ ከተነጋገረ በኋላ ለሉሲዎቹ ሃላፊነት የሁለት አመት ኮንትራትና 120ሺህ የተጣራ ደመወዝ እንዲሰጣቸው ይወስናል ስራ አስፈጻሚው የወሰነውንና ያስቀመጠውን አካሄድ በመንተራስ ለአሰልጣኙ ለሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን የማሳለፍ ግዴታ ያለው የሁለት አመት ውልና የ120 ሺህ ብር የተጣራ ደመወዝ የተካተተበት ውል ቀርቦላቸው አልፈልግም አልፈርምም በማለታቸው ሳንስማማ ቀርተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
” አሰልጣኙ አለመስማማታቸውን በማየት ፌዴሬሽኑም ታህሳስ 8/2016 ድረስ ባለው በ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የሃላፊነት ውል እንዲቀጥሉ ይደረጋል.. ከዚያም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ድጋሚ ይቀመጥና በ20 አመት በታች ቡድን ሃላፊነታቸው ለተጨማሪ አንድ አመት ኮንትራታቸው ታድሶ በ70 ሺህ ብር ደመወዝ እንዲቀጥሉ ይወስናል ይህን ለማስፈጸም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ዳኛቸው ንግሩና እኔ አሰልጣኙን እንድናናግር ተወሰነ ” ያሉት አቶ ባህሩ ” አሰልጣኙን ጠርተን በውሉ ዙሪያ ስናወራ የአንድ አመቱን ውል አልቀበልም” ሲሉ መልሰዋል። በጉዳዩ ዙሪያ ከፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በኮንትራቴ ዙሪያ ከሞሮኮ ጨዋታ መልስ በድጋሚ እናወራለን እስከዚያ ድረስ በውሌ ዙሪያ ምንም አላወራም ብለው መውጣታቸውን ነው የምናውቀው ” ሲሉ አስረድተዋል። አቶ ባህሩ እንደሚሉት የአሰልጣኙ ውል ተጠናቆ ባይታደስም በነባሩ የ50ሺህ ብር ደመወዝ ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነ ነው የምናውቀው ” ሲሉም አብራርተዋል።
አሰልጣኙ ያቀረቡት ሁለት ኢንተርናሽናል የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ይዘጋጅልኝ ጥያቄ ለምን ተግባራዊ አልተደረገም የተባሉት አቶ ባህሩ ” የአሰልጣኙ የሁለት ኢንተርናሽናል የአቋም መለኪያ ጨዋታ ጥያቄን ተከትሎ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። በተለይ የኬንያና የቡሩንዲ አቻዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ሙከራ አድርገን አልተሳካም በተለይ የዕድሜ ብሄራዊ ቡድኖችን ለአቋም መለኪያ ማግኘት ከሌሎቹ በላይ ይከብዳል በእኛ በኩል የምንችለውን ሞክረናል ግን አልተሳካም በቀጣይ የምንችለውንና የተለመደውን ድጋፍ ማድረጋችን ይቀጥላል” ሲሉ ለአሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል አስተያየት ምላሽ ሰጥተዋል።
በላቲን አሜሪካዋ ሀገር ኮሎምቢያ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የ180 ደቂቃ ፍልሚያ የቀረው ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል የምሳ ግብዣና ደማቅ አሸኛኘት የተደረገለት ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ ከሞሮኮ አቻቸው ጋር ላለባቸው ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ ሞሮኮ አቅንተዋል።