— የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እሁድ ይካሄዳል..
41 ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ የፊታችን እሁድ በጃንሜዳ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጉርድሾላ በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በሰጡት መግለጫ ውድድሩ በቀጥታ ሀገራቸውን በኢንተርናሽናል የአገርአቋራጭ ውድድር እንዲካፈሉ የሚያደረግ በመሆኑ በአትሌቶች በጉጉት የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።
- ማሰታውቂያ -
የጃንሜዳው ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሶስት ዋና አላማዎች ሲኖሩት የመጀመሪያው በዚህ አመት መጋቢት 30 /2024 በሰርቪያ ቤልግሬድ ለሚካሄደው የአለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ውድድርና
የካቲት 25/ 2024 ደግሞ በቱኒዚያ ቱኒዝ በሚካሄደውና ከአመታት በኋላ ለሚካሄደው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን መምረጥ ሁለተኛው የክልል አትሌቶች ልምድ የሚያገኙበትና ሶስተኛው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱ ነው ተብሏል።
ውድድሩ በኣምስት ካታጎሪ ማለትም በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች፣ በ10ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች፣ በ8ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ 6 ኪሎ ሜትር የሚካሄድ ሲሆን ከ1-5 የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ሲያልፉ 6ኛ የወጡት ደግሞ በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚታይ መሆኑ ታውቋል። በአምስቱ ካታጎሪ ከ1-6 የወጡ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት የሚሸለም ሲሆን ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ ለውድድሩ 3.5 ሚሊዮን ብር በጅቶ 840 ሺህ ብሩን ለሽልማት መመደቡ ታውቋል።
በውድድሩ 660 ወንዶች 320 ሴት አትሌቶች በአጠቃላይ 980 ተወዳዳሪዎች እንንደሚካፈሉ ይፋ ተደርጓል።
የፌዴሬሽኑ አመራሮች በዚህ መግለጫቸው 5 ሀገራትን ጋብዘው ሶስቱ ማለትም ኬንያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን እንደሚካፈሉ ሲያረጋገጡ ኤርትራና ኡጋንዳ ምላሽ አለመስጠታቸውን አስረድተዋል። ይህን ውድድር
ኢቢሲ በቀጥታ ስርጭት እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮ.ቴሌኮም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር 3 አመት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት መፈጸሙን አመራሮቹ አስታውቀዋል። ፌዴሬሽነ ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር ረጅም ጊዜ የወሰደ አጋርነት እንዳለው የገለጹት አመራሮቹ ለቀጣዮቹ 3 አመት የሚቆይ ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር መፈራረማቸውን ገልጸው ለስምምነቱ ተቋሙን አመስግነዋል።
በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው ጋዜጣዊ መግለጫው የሰጡት አቶ ዮሀንስ እንግዳ የፌዴሬሽኑ
ጽ/ቤት ሃላፊ ፣ አቶ አስፋው ዳኜ የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር እና አቶ አሰፋ በቀለ የፋሲሊቲና የአትሌቶች አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው።