ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ያለባቸው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አባላት ነገ ወደ አክራ ይጓዛለሉ።
የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ሃ/ገብርኤል ስለ ቡድኑ የአክራ ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ዛሬ በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በሰጡት መግለጫ “በዚህ አምስት ቀን ውስጥ የመጣው ዝናብ ሜዳዎችን ማጨቅየቱ በምንፈልገው ደረጃ ልምምድ እንዳንሰራ አድርጎናል ነገር ግን ምንም ውጤት ይምጣ ጭቃውን ሰበብ አናደርገውም ያም ሆኖ በቅ/ጊዮርጊስ ሜዳና በ35 ሜዳ ጥሩ የሚባል ልምምድ አድርገን ወደ ጋና ለመጓዝ ተዘጋጅተናል”ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኙ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን “በአበበ ቢቂላ ጨዋታ ተጨዋቾቼ በመጀመሪያ 45 ደቂቃ የተወሰነ የመደናገጥ የመሳሳት ነገር ታይቶባቸዋል ባልተለመደ መንገድ ከለመዱት በላይ በርካታ ደጋፊ ሜዳ በመግባቱና ያን ስሜት ያለመዱት በመሆኑ ጫና ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ይሄን መሠል አካሄድ ግን መስተካከል አለበት እንደ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ይህን ማስተካከል አለባቸው አበበ ቢቂላ የነበሰው ደጋፊ ለሰጠንም ድጋፍ አመሰግናለሁ” ሲሉ መልሰዋል።
” 3ለ0 ተሸንፈናል ይሄም ግን የማይለወጥ ውጤት አይደለም በዘመናዊ እግርኳስ ሲፈጠር የነበረውን ውጤት የመገልበጥ ሂደት ለተጨዋቾቼ አስረድቻለሁ ሊቨርፑል ከባየር ሙኒክ ጋር በሜዳው 0ለ0 ከተለያየ በኋላ በባየር ሙኒክ ሜዳ 3ለ1 ረትቶ አልፏል እኛም ይህን አሳይተን አበረታተናቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
3ለ0 ከተሸነፉ በኋላ አሰልጣኝ ፍሬው እኛም አልወደቅንም እነሱም አላለፉም በሚል ስለሰጡት መግለጫ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “አሁንም እደግመዋለሁ እኛም አልወደቅንም እነሱም አላለፉም
ስለ እግርኳስ ህግ የማያውቁ ወይም እግርኳስን ያልተረዱ ሰዎች በዚህ አባባል ሲገረሙ አይቻለሁ ግን እውነት ነው ውጤት የማይገለበጥ ቢሆን ለምን ወደ ጋና እንሄዳለን”ሲሉ ተናግረዋል
“በየትኛውም ሀገር ለ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ሲባል ዋናው የሴቶች ሊግ ተቋርጦ አያውቅም.. በተጨማሪ የዕድሜ ጉዳይ በተመለከተ ከዋናውም ብሄራዊ ቡድን ማቆም ያለባቸው ተጨዋቾች እንደገና ከ20 አመት በታች ቡድኑ ውስጥ የተካተቱ አሉ ይሄን እንዴት ታየዋለህ..?” በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አሰልጣኝ ፍሬው በሰጡት ምላሽ “እኔ የላብራቶሪ ሰራተኛ አይደለሁም ስለ ዕድሜም አያገባኝም ሙያው ካለህ በቀጣይ አብረን እንመረምራለን ሊጉ ለውድድሩ ሲባል ተዘጋ የምትለው ለአፍሪካ ዋንጫ ሲባል የወንዶቹ ፕሪሚየር ሊጉ ተቋርጦ የለም ምነው ለሴቶቹ ሲባል ቅር አላችሁ? እንደ ሀገር ሊጉ መቋረጡ አይገርምም ቅድሚያ ለሀገር እንጂ ለተቋም ወይም ለግለሰብ አይደለም” ሲሉ ቁጣ አዘል ምላሽ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ ” በአበበ ቢቂላው ጨዋታ ሰባት ያለቁ ኳሶችን ስተናል ዕድል መፍጠራችን ራሱ ለውጡን ያሳያል በቀጣይ በአክራ ባለን የመልስ ጨዋታ እኔም ሆንኩ ሌሎች ጫና ሳያደርግባቸው የተቻለውን ውጤት ለማምጣት ይጥራሉ ” በማለት ስለተጨዋቾቻቸው ምላሽ ሰጥተዋል። ረድኤት አስረሳኸኝን በመልሱ ጨዋታ እንደማያገኟት የገለጹት አሰልጣኝ ፍሬው የሌሎቹን ተጨዋቾች ጤንነት በተመለከተ ከቡድኑ የህክምና ባለሙያዎች የሚመጣውን ውሳኔ እየጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የደረሰባቸውን የ3ለ0 ሽንፈት የመገልበጥ ከባድ ሃላፊነት ይዘው ይቻላል በሚል ጽኑዕ አቋም እሁድ አክራ ላይ ለሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ ነገ ወደ ጋና ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።