THE BIG INTEVIEW WITH ABUBEKER NASIR
በይስሐቅ በላይ
- ማሰታውቂያ -
አሁን የኢትዮጵያ ቡናን 10 ቁጥር ማልያ ለብሶ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ
ለጊዜው እርሱት፤ ከዛሬ 8 አመት በፊት ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ሲያነሳ የት
ነበርክ? ብላችሁ ብትጠይቁት በምላሹ ገና ለጋ ታዳጊ መሆኑን ይገልፅላችኋል፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ ቡና ደምቆ እያበራ የሚገኘው አንፀባራቂው ኮከብ አቡበከር ናስር
ኢትዮጵያ ቡና በ2003 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ
ከፍ አድርጎ ሲያነሳ ይሄ ታዳጊ የሰፈር ልጅ እጁን ይዞት ስታዲየም ገብቶ ሽቦ ስር
ተቀምጦ ነው ታሪካዊውን ድል የኮመኮመው፡፡
ያለ ለጋ ሕፃንና ታዳጊ ዛሬ አድጎና ጎልምሶ ዛሬ ባለታሪክ ሆኖ በልጅነት አዕምሮ
የተቀረፀውን ድል በሱ ፊት አውራሪነት ለመድገም በቡናማዎቹ ማልያ ከፊት
ተሰልፏል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ግብ አዳኝ የነበሩት ተጨዋቾች ዮናስ
ተፈራ፣ ሙሉጌታ ወ/የስ ሚሊዮን በጋሻው፣ አቢ ሰይድ፣ ዮሴፍ ተስፋዬ፣
አሰግድ ተስፋዬ፣ ዮርዳኖስ አባይና ታፈሰ ተስፋዬን የመሳሰሉ ግብ አይምሬዎች
በክለቡ የፈፀሙት የማይረሳ ገድልን የማስቀጠል አደራን ገና በለጋ እድሜው
የተሸከመውን የወቅቱ ክስተት ወይም አንፀባራቂ ኮከብ (The Rising star)
የእድሜውን ለጋነት ሳይሆን በሜዳ ላይ ያለው ታላቅነት በማየት
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክሲኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ
(The Rise of Abubeker Nasir) በሚል ርዕስ በብርሃን ፍጥነት
እየተመነጠቀ ያለውን እድገቱን ሊያስቀኘን እንግዳ አድርጎ
አቅርቦታል፡፡
ራስ መኮንን ድልድይ ኢንሀስ ህንፃ 4ኛ ፎቅ በሚገኘው የሀትሪክ
ቢሮ ቀለል ባለ አለባበስ የተገኘው አቡበከር ለኢትዮጵያ ቡና
ቢ ቡድን ሳይጫወት አንዴም ልምምድ ሳይሰራ የዋናው ቡድን
የማሸነፍ ከፍተኛ ኃላፊነት የወደቀበት ከክለብም አልፎ ለአገር ትልቅ
ሥራ ይሰራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን፤ አድናቂዎቹ በቁልምጫ
“አቡኪ” እያሉ የሚጠሩት ዝምተኛው ገዳይ አቡበከር ናስር በሚዲያ
ታሪክ በተለይ ለሀትሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ቃለ ምልልስ “አሁን
ግቤን (Goal) እየመታሁነው፤ ህልሜን ግን ገና መኖር አልጀመርኩም”
በማለትም ይናገራል፡፡ አቡበከር በሀትሪክ ኤክሲኪዩቲቭ ኤዲተር ቢሮ
በነበረው ከአንድ ሰዓት የበለጠ ቆይታ በግል ህይወቱ፣ ስለ
ክለቡ፣ ስለ ህልሞቹ፣ ስለሚያስታውሳቸው የእግር
ኳስ ክስተቶች፣ የክለቡ ፔናሊቲና የቅጣት
ምት አንደኛ መቺ ስለመሆኑ ተጠይቆ የልጅ አዋቂ
መሆኑን የሚመሰክር ምላሽ ከዚህ በታች
ሰጥቷል፤
ሀትሪክ፡- የአባትህን ስም በተመለከተ ሚዲያውም ላይ ሰው ሲጠራህም
ግራ የመጋባት ነገር አለ፣ ልክ እንደ አበባው ቡታቆ (ቡጣቆ) በማለት
የማሳሳት ነገር አለ ይሄን በተመለከተ አባትህስ ምን ይላሉ…?
አቡበከር፡- እንዳልከው በተለይ በሚዲያ ሲዘገብ አቡበከር ናስር ከማለት
ይልቅ አቡበከር ነስሩ እየተባለ ሲጠራ የተሳሳተ ስሜት ብዙዎቹ ላይ
ፈጥሮ ሌሎቹም የአባቴን ስም ቀይረው እስከመጥራት ነው የደረሱት፤
በዚህም የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግጂያለሁ፡፡ አንተ ይሄን ትላለህ
እንጂ አንድ ጊዜ ግን በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቡና ስለማሸነፉ ሲዘገብ
እኔ ለቡና ግብ አስቆጥሬ ዘጋቢው ግን አቡበከር ናስር አስቆጠረ ከማለት
ይልቅ አቡበከር ሣኒ ብሎ ያውም ደጋግሞ አቀረበ፡፡ እቤት ለአባቴ ጎል
አገባሁ ብዬ ነግሬው ስለነበር ዘገባውን ሲሰማ “አንተ ትዋሻለህ እንዴ?
ሞክሼህ ያስቆጠረውን እንዴት እኔ ነኝ ያገባሁት ትለኛለህ?“ (ሣቅ)
ያለኝ አጋጣሚ ሁሉ አለ፡፡ አባቴ ስሙ በትክክል ባለመጥራቱ
ደስተኛ አያደርገውም፤ የሱ ልጅ የተጠራ ያህልም
አይሰማውም፡፡ ሰውም ለምዶ አቡበከር ናስር ሣይሆን
አቡበከር ነስሩ ማለትን ነው የሚያስቀድመው፡፡ ስለዚህ
ትክክለኛው የአባቴ መጠሪያ ናስር መሆኑን በዚህ
አጋጣሚ ብናገር ደስ ይለኛል፡
ሀትሪክ፡- በ2003 ኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚየር
ሊጉን ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነሣ
አንተ የት ነበርክ…?
አቡበከር፡- …የሚገርምህ በጣም ልጅ
ነበርኩ፤ አንድ የሰፈሬ ልጅ ይዞኝ ገብቶ
ይሄንን ታሪካዊ ድል የስታዲየሙ ሽቦ
ስር ሆኜ ተከታትያለሁ፡፡ የነበረው
ድባብ በጣም የሚገርም ነው፤ ደጋፊው
ድል እንደተራበና ያንን ቀን በጉጉት
ሲጠብቀው እንደነበር በልጅነት አዕምሮዬ
አይቼ ታዝቤያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ኢትዮጵያ ቡና ይሄንን ታሪካዊ ድል
ካሳካ ድፍን ስምንት አመታትን አስቆጥራል፤ይሄንን ታሪክ
በአንተ 10 ቁጥር ለባሽነት ስለማሳካት ምን ታስባለህ… ?
አቡበከር፡- ትናንት በልጅነቴ ያየሁት ደል ዛሬም
ድረስ በአዕምርዬ አለ፤ ያንን በተጨዋችነት ዘመኔ ተሳክቶ
ማየት ትልቅ ምኞቴ ነው፡፡ ለዚህ ምርጥ ድጋፊ የሀገሪቱን
ትልቁን ዋንጫና ክብር ከመስጠት በላይ ሌላ ትልቅ ስጦታ
አለ ብዬ አላስብም፣ ከቡናም ይሄን ሳላሳካ መውጣትን
አልመኝም፡፡ ለደጋፊው እንኳን የሊጉን ዋንጫ ሰጥተነው
የሲቲ ካፑን ዋንጫ ስንወስድ እንዴት በደስታ እንደሰከረ
አይተናል፤ ይሄንን እውን ለማድረግ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር
ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ይሄን አሳክተን
ደጋፊውን ይበልጥ ጮቤ ማስረገጥ፣ የሀገሪቱ ክለቦች የበላይነት
ማጎናፀፉን ነው የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- …ታዲያ ይሄ ምኞትህ መቼ ወደ አውነትነት
ይቀየራል ብለህ ታስባለህ… ?
አቡበከር፡- …አሁን በፕሪሚየር ሊጉ አናት ላይ
ነን፤ እየመራን ነው፡፡ የምንመኘውን ለማግኘት ይሄን
እስከመጨረሻው አስጠብቀን መጓዝ ይኖርብናል፡፡ እነ
መስዑድ፣ ዳዊት እስጢፋኖስና ሌሎች የቀድሞ የክለቡ
ተጨዋቾች ይሄንን አሳክተው የራሳቸውን ታሪክ በደማቁ
አፅፈዋል፤ እኛም ይሄን ታሪክ መድገም እንፈልጋለን፡፡ ቡና
የሊጉን ዋንጫ እኔ የተጨዋችነት ዘመን ቢያነሣ ራሴን እንደ
አንድ እድለኛ ነው የምቆጥረው፤ በኢትዮጵያ ቡና ታሪኬን
በደማቁ ማፃፍ እፈልጋለሁ፡፡ ቡና ዋንጫ ሣያገኝ በግሌ 100 ጎል
ባገባ የግል ክብሮችን ባግበሰብስ ለእኔ ትርጉም አይሰጠኝም፤ከግል
ክብሬ ይልቅ የክለቤ ክብር ይበልጥብኛል፡፡ እኔ ባገባ ሌላው ቢያገባ
የሚለው አያሳስበኝም፡፡ አሳሳቢው ሻምፒዮናነት ነው፤ቡና ሻምፒዮን
ሲሆን ነው የቡና ቆይታዬ ሙሉ ወይም ደማቅ ነበር የምለው፡፡ ለስኬቱም
አቅሜ የሚችለውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና 10 ቁጥር ማልያን ነው የምትለብሰው፤
ይሄ ቁጥር ደግሞ በክለቡ ታሪክ ታላላቅ ስም ያላቸው፣ እግር ኳሱ
የማይዘነጋቸው ባለውለተኞች ለብሰውት አልፈዋል፡፡ 10 ቁጥር ማልያን
የለበስከው መርጠህ ነው…? በዚህ ታላቅ ክለብ ካለው ታሪክ አንፃር ይሄን
ከክለብህ ቁጥር መልበስ ምን ስሜት ይፈጥራል
አቡበከር፡-በነገራችን ላይ ለ10 ቁጥር የተለየ ፍቅር አለኝ፤ ቁጥሩን
እወደዋለሁ፣ ይመቸኛል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ቡናም ስመጣ መጀመሪያ መልበስ
የፈለኩትም ይሄንኑ 10 ቁጥር ቢሆንም ይሄንን በክለቡ በወርቃማ ቀለም
የተፃፈ ታሪክ ያላቸው ተጨዋቾች የለበሱትን ማልያ መልበስ በጣም
ከብዶኝ፣ አስፈርቶኝም ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርሃቴንም ጉጉቴንም የተረዳው
መሰዑድ መሀመድ 10 ቁጥሩን ማልያ እንድለብስ ገፋፍቶኝ አበረታታኝ፡
፡ ይሄው እስከዛሬ የክለቡ ታላላቅ ተጨዋቾች የለበሱትን 10 ቁጥር ማልያ
የግሌ በማድረግ ለብሼ እየተጫወትኩ ነው፡፡ የልጅነት የፍላጎቴን ቁጥር
በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ 10 ቁጥር ማልያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሼ
ወደ ሜዳ በገባሁበት ቀን ትዝ የሚለኝ መስዑድ መሀመድ እኔንና ሚኪያስን
ጠርቶን የመጀመሪያ ማስታወሻ ፎቶ አብረን መነሳታችን አስታውሳለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ዮናስ ተሾመ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ሚሊዮን በጋሻው፣ አቢ
ሠይድ፣ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ ጌታቸው ካሳ (ቡቡ)ና አሰግድ ተስፋዬን የመሳሰሉ
ታላላቅ አጥቂዎች ለክለቡ ተጫውተው አልፈዋል፤ ስለ እነዚህ ታላላቅ
ተጨዋቾች ታሪክ ታውቃለህ?
አቡበከር፡- በአፈ ታሪክ ደረጃ ሲነገር እሰማለሁ፤ ከዚያ በዘለለ
አንዳቸውም ሲጫወቱ የማየት እድሉ አልገጠመኝም፡፡ ምክንያቱም እነሱ
በተጨዋቱበት ዘመን እኔ አልተፈጠርኩም፡፡ ባልፈጠርም ግን የክለቡ ታሪክ
፣ ስማቸው በታሪክነት አብሮ ሲነሣ እሰማለሁ፡፡ እኔ ነፍስ አውቄ
ጨዋታ መከታተል ከጀመርኩ በኋላ ስለ ክለቡ አጥቂዎች ከተነሣ
ስለ ታፈሰ ተስፋዬ ብቻ ነው ትንሽ ትንሽ የማስታውሰው፡
፡ ያም ቢሆን ግን ከላይ ስማቸውን ያነሳሃቸውን ታላላቅ
ተጨዋቾች ከቡና አልፈው ለሀገር ትልቅ ውለታን ሰርተው
ያለፉ ስለመሆናቸው ከታሪክ ተረድቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-የእነዚህ ታላላቅ ተጨዋቾች የግብ
አግቢነት ኃላፊነት በዚህ በለጋ እድሜህ ተሸክመሃል
ማለት ይቻላል…፤ በዚህስ ምን ይሰማሃል…?
አቡበከር፡- ስለ ክለቡና ስለ እነዚህ ታላላቅ
ተጨዋቾች ታሪክ ወደ ኋለ መለስ ብለህ ስታይና
ስትሰማ ትልቅ አደራ እንዳለብህ ይሰማሃል፤ እኔ ራሴን
በእነሱ ደረጃ የማስቀመጥ ድፍረቱ ባይኖረኝም እኔምየእነሱን ታሪክ በክለቡ ውስጥ በማስቀመጥ
ስሜ በታሪክ እንዲነሣ የምስስተው ነገር
አይኖርም፡፡
ሀትሪክ፡-በኢትዮጵያ ቡና ቶሎ
እንድትላመድ ነገሮችን ሁሉ ቀለል በማድረግ
ከጎንህ የነበረው ማነው?
አቡበከር፡- እውነት ለመናገር የሁሉም
ድጋፍ አልተለየኝም ብልም የመስዑድ
መሀመድ ግን ፍፁም የተለየ ነው፤ መስዑድ
በሜዳ ላይ ጨዋታ ብቻ ሣይሆን ከሜዳ
ውጪም ፍፁም የተለየ ስብዕና ያለው
ተጨዋች ነው፡፡ እንኳን ለእኛ ለታዳጊዎቹ
ይቅርና ከሲኒየር ተጨዋቾች ጎን በመሆን
በመምከርና በማገዝ የሚታወቅ ነው፡
፡ በኢትዮጵያ ቡና ቡና ቶሎ እንድንላመድ
የመስዑድ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ
ቡና ነገሮች የከበዱን ስንገባ ሣይሆን መስዑድ
ከቡና ሲወጣ ነው፡፡ የእሱን ጥቅምና ጉዳት
ያወቅነው አሱ ከወጣ በኋላ ነው፤ በቡና ቶሎ
እንድንላመድ የእሱ ሚና የተለየ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- …በልጅነትህ የማን ደጋፊ
ነበርክ…?…የመጫወት እድል ያገኘኸው…
ለተመኘኸው ቡድን ነው…?
አቡበከር፡- …በድጋፍ ደረጃ የኢትዮጵያ
ቡና ደጋፊ ነበርኩ…፤…ኢትዮጵያ ቡናን
እየደገፍኩ ነው ያደኩት ብቻ ሣይሆን ቡናን
ማየት ስለሚያስደስተኝ የቡናን ጨዋታ
ብቻ እየመረጥኩ ነበር የማየው…፤ እውነት
ለመናገር ግን… ኳስ ተጨዋች ለመሆን
ከመመኘት ውጪ… እዚህ ክለብ ገብቼ…
ብጫወት… በማለት… በልጅነት አዕምሮዬ…
መመኘቴን አላስታውስም…፡፡
ሀትሪክ፡- …ሮል ሞዴሌ ነው…
እያደነኩት… እሱን ለመሆን እየተመኘሁ ነው
ያድኩት… የምትለው ተጨዋች አለ…?
አቡበከር፡- …ከላይም ብዬሃለሁ…
ስታዲየም ከገባሁ… የቡናን ጨዋታ
ለማየት ብቻ ነው የምገባው…፤ ምክያቱም
የቡና ደጋፊ ስለነበርኩ፡፡ የሌሎቹን ክለቦች
ስላላየሁ ይሆናል እንጂ በሞዴልነት የሚታዩ
ተጨዋቾች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በወቅቱ ግን እኔ
ካየኋቸው ተጨዋቾች መስዑድ መሀመድና
ዳዊት እስጢፋኖስ ለእኔ የተለዩ ተጨዋቾች
ነበሩ ብቻ ሣይሆን በድንቅ ችሎታቸው
እቀናባቸው ነበር፤ ሁለቱን በጣም ነው
የማደንቃቸው፡፡
ሀትሪክ፡-ለኢትዮጵያ ቡና ለመጀመሪያ
ጊዜ ስለተጫወትክበት አጋጣሚ መለስ ብለህ
አስታውሰኝ እስቲ….?
አቡበከር፡- ለኢትዮጵያ ቡናከመጫወቴ
በፊት ለሐረር ሲቲ ነበር የምጫወተው በወቅቱ
የሐረር ሲቲ አልጣኞችን እስማኤል አቡበከር
ነበር እሱ በወቅቱ ከ17 አመት በታች ቡድን
አሰልጣኝ ለነበረው ለጥናፉ አለሙ ነገረው
ይምጣ ልየው አለኝ፡፡ ወዲያውኑ የብሔራዊ
ቡድን አካል አደረገኝ፡፡ ቡናዎች እዛ ሲጫወት
አይተው ወሰዱኝ አቶኢትዮጵያ ቡና በቢራ
ቲሴራ ነበር የምጫወተው፡፡ አንድም ቀን የ ቢ
ቡድን ልምምድ ሆነ ትሬይሪንግ ሣልሠራ ነው
ዋናው ቡድን የተጨወትኩት፡፡ አሁን አለህ
እድሉን ሰጥቶኝ ለምወደው ቡደንን በቋሚ
ተሰላፊነት መጫወት ችያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮ.ቡና የመጀመሪያ ጎልና
ስለተሰማው ስሜት?
አቡበከር፡- ለመጀመሪያ በቡና ማልያ
የተጫወትኩትና ጎል ያስቆጠርኩት ለአባይ
ግድብ ዋንጫ ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ውድድር
ላይ መሳተፌ የእግር ኳስ ታሪኬን ይበልጥ
የተለየ አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም አባይም
ኢትዮ ቡናም የራሣቸው ተልቅ ታሪክ
ያላቸው ናቸውና በዚህ ደረጃ ግምትበምሰጠው
ጨዋታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰለፌ
ብቻ ሣይሆን ግብም አስቆጥሬያለሁ፡፡ ግብ
ማስቆጠሬ ከመደሰት ይልቅ በጣም ነው
የደነገጥኩት፡፡ ልብ ብላችሁ አይታችሁኝ ከሆነ
የመጀመሪያ ግቤን አስቆጥሬ ምንም አይነት
የደስታ ስሜት አላሳየሁም፤ ምክንያቱም
ማግባቴን እንኳን አላመንኩም፡፡ በይበልጥ ግን
በጣም የተደሰትኩት አዳማ ላይ ሁለት ጎል
አግብቼ ዋንጫ እንድናነሳ ምክንያት በሆኑት
ግቦቼ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጨዋታውም
ላስቆጠርኳቸው ግቦች የተለየ ቦታ አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ዋናው ቡድን ገብተህ
ከታላላቅ ተጨዋቾች ጎን ስትሰለፍ የነበረህ
ስሜትስ… ?
አቡበከር፡- በጣም ስታደንቃቸው በተለየ
አይን ስታያቸው ከነበሩ ተጨዋቾች ጋር አብረህ
ተሰልፈህ የምትጫወትበት እድል ስታገኝ
የተለየ ስሜት ነው የሚሰማህ፤ዝም ብለህ
አስበው ከእነ መስዑድ እልያስና ከመሳሰሉት
ጋር አብሮ መጫወት የማታምነው ነገር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን በኢትዮጵያ ቡና 45ሺ
ብር ወርሃዊ ደሞዝ ታገኛለህ በእግር ኳስ
ለመጀመሪያ ጊዜ በደሞዝ መልክ የተከፈለህ
ስንት ነው…? ታስታውሰዋለህ…?
አቡበከር፡- አዎን አስታውሰዋለሁ፤
በእግር ኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ በደሞዝ መልክ
ያገኘሁት ሐረር ሲቲ ስጫወት የተከፈለኝ
300 ብር ነው፤ የወላጆቼን ልፋት ስለማውቅ
ገንዘቧን እንዳገኘሁ ሮጬ የሰጠኋት ለአናቴ
ነው፡፡ እኔ ሁሌም ለቤተሰቦቼ ቅድሚያ
መስጠት ነው የምፈልገው፤ እናቴም በሰጠኋት
ገንዘብ መርቃኛለች፤የእሷ ምርቃትም ነው
ለዚህ ያደረሰኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የባንክ ቤት ደጃፍስ ለመጀመሪያ
ጊዜ የረገጥከው መቼ ነው…?…በስንት
ብርስ… ቡክ ከፈትክ…?
አቡበከር፡- …አሁን ስንት ደረስክ…?
ብለህ እንዳትጠይቀኝ እንጂ… በ1500 ብር
ነው የባንክ ቡክ የከፈትኩት፤… የሚገርምህ
ግን የባንክ አካውንት የከፈትኩት ተጨዋች
ሆኜ አይደለም…
ሀትሪክ፡-… ታዲያ…?
አቡበከር፡- …ወደ እግር ኳስ ጎራ ብዬ…
ደሞዝ ማግኘት ሣልጀምር… ሠፈር ውሰጥ
እያለሁ ነው…፡
ሀትሪክ፡- …ማለት ሥራ ነበረህ…
በልጅነትህ…?
አቡበከር፡- …ሠፈር ውስጥ… በልጅነቴ
ሣይክል አከራይ ነበር… ሣይክል በማከራየት
ከማገኘው ገንዘብ ለቤተሰቦቼ እየሰጠሁ…
የምትተርፈኝን ገንዘብ… አጠራቅሜ ነው…
በ1500 ብር… የቡክ አካውንት… የከፈትኩት፡
፡
ሀትሪክ፡- …ስለ ብስክሌት ማከራየት
ስታነሣ… እንደውም አንድ የሰማሁት ነገር
ትዝ አለኝ…፤ …ብስክሌት የገዛኸው…
ከመሬት ባገኘኸው ገንዘብ ነው… የሚል ነገር
ሰምቼ ነበር… ትክክል ነኝ… ?
አቡበከር፡-…ማነው ሹክ…ያለህ….?…
አዎን ትክክል ነው… ከመሬት 1600 ብር
ድንገት አገኘሁ…፤…በአንድ ሺህ ብሩ
ወዲያውኑ ብስክሌት ገዛሁና ማከራየትና
ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩ…(ሳቅ)…የሚገርምህ
በዚያች በአንድ ሺህ ብር የገዛሃት ብስክሌት
ወልዳ ኳስ መጫወት እስከምጀምር ድረስ ወደ
ስድስት ብስክሌት ድረስ አድገውልኝ ነበር፡
፡ ወደ ኳስ ስገባ ትኩረቴን ይነጥቀኛል ብዬ
ሁሉንም ቸብችቤ ጨርስኳቸው፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን በክንፍና በመሃል
አጥቂነት ሚና ስትጫወት ነው የምትታየው፤
ራስህን ከእነዚህ ቦታዎች ውጪ ባለ የጨዋታ
ሚና አይተኸው ታውቃለህ…?
አቡበከር፡- እኔ ከ17 አመት በታች
ቡድን ውስጥ በአማካይ ቦታ ነበር ስጫወት
የነበረው፤ የመጀመሪያ ቦታዬዬም ይሄ ነበር፤
ወደ ቡና ስመጣ ነው አጥቂ የሆንኩት፤
በአብዛኛው በክንፍና በአጥቂነት ቦታ ላይ
ነው እየተጫወትኩ ፣ በዚህም ደስተኛ ሆኜ
ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ በየትኛው ቦታ
ብትጫወት ይበልጥ ይቀልሃል ካልከኝ ግን
10 ቁጥር ላይ ተደራቢ ላይ ስጫወት በጣም
ይመቸኛል፤ የተሻለ መንቀሳቀስም እችላለሁ፤
ጎል ለማግባትም በጣም ቅርብ እሆናለሁ፤
ኳስም እንደ ልብ እነካለሁ፡፡ ይህ የግል
አስተያየቴን ነው የምሰጥህ፤ ከዚህ ውጪ ግን
አሰልጣኝ ባዘዘኝ ቦታ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ባለፈው ከቅዱስ ጊዮርጊስ
ጋር በተደረገው የሀገሪቱ ትልቅ ደርቢ ላይ
ተሳትፈሃል፤ የመጀመሪያ የደርቢ ጨዋታን
በበርካታ ደጋፊ ፊት ማድረግ ለእንደ አንተ
አይነቱ ታዳጊ ተጨዋች ምን አይነት የተለየ
ስሜት አለው…. ?
አቡበከር፡-ምናባልት በቋሚ ተሰላፊነት
ስጫወት የአሁኑ የመጀመሪያ የደርቢ
ጨዋታዬ ነው እንጂ ከዚህ በፊት ግን በደርቢ
ጨዋታ ለተወሰነ ደቂቃም ቢሆን ገብቼ ስሜቱን
ሞክሬው ነበር፡፡ አሁን ግን በመጀመሪያ ቋሚ
ተሰላፊነት ስለገባሁ የተለየ ስሜት ነው
የተሰማኝ፤ ገና ስለ ፕሪምዬርየረ ሊጉ ጨዋታ
ስለመጫወት ሳሰብ ስመኘውና ስፈልገው
የነበረ የደርቢ ጨዋታ በመሆኑ በጣም ነው
የተደሰትኩት፡፡ ገና ጨዋታው ሳይጀመር
እያሟሟቅን ሳለ የደጋፊው ሀኔታ ትኩረቴን
እንደሳበው የተረዳው እያሱ ይመክረኝ ነበር፡
፡ “የስታዲየሙ ድባብ ሊገርምህ ይችላል ግን
ይህ ሁኔታ ትኩረትህን እንዳይሰርቅህ፤ ሙሉ
ትኩረትህን በጨዋታው ላይ አድርግ” ብሎ
ሲመክርኝ ነበር፡፡ በእርግጥ ድባቡ ስቦኛል
ሜዳ ውስጥ ስገባ ግን ሁሉንም ረስቼዋለሁ፡
፡ እውነት ለመናገር የደርቢ ጨዋታ ድባብ
ስሜቱ ልዩ ነው፤ በዚህ አይነት ድባብ ውስጥ
መጫወት ትልቅ አድል ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙዎች ግን ሀትሪክ ጋዜጣን
ጨምሮ የቅድስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ
ቡና ጨዋታ የሀገሪቱ ትልቅ ደርቢ ተብሎ
ቢጠራም ስሙን የሚመጥን ደርቢ አይደለም
በሚል ቅሬታ እናቀርባለን፤ አንተስ በዚህ ላይ
ምን አይነት ስሜት ነው ያለህ… ?
አቡበከር፡- …ያው የሀገሪቱ ትልቅ
ደርቢ ተብሎ መጠራት ካለበት በታሪክም፣
በውጤትም፣ የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤትና
ሁለቱም የአንድ ከተማ ኃያል ክለቦች
ከመሆናቸው አንፃር የሁለቱን ጨዋታ የሀገሪቱ
ትልቁ ደርቢ ብለህ ነው የምትጠራው፡፡
ከደጋፊው የሚያምር ድባብ ውጪ በሜዳ ላይ
የሚታየው ነገር ስሙን የማይመጥን የደርቢ
ጨዋታ ነው በሚለው እኔም እስማማለሁ፤
ግን የጨዋታው መድከም ወይም ስሙን
ያለመመጠን ችግሩ የደርቢው ሣይሆን
የሀገሪቱ እግር ኳስ አጠቃላይ ችግር ውሰጥ
መውደቅ ነፀብራቅ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡
፡ የሀገሪቱ እግር ኳስ ደክሞ ከደርቢው የተለየ
ነገር መጠበቅ የዋህነት ነው፤እኔ እንደውም
ስጋቴ እግር ኳሱ ላይ ብዙ ካልሰራን አይደለም
ደርቢው ሌውም ሊጠፋ ይችላል፡፡
ሀትሪክ፡-ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ህልምህ
ምንድነው…?
አቡበከር፡-ከቡና ጋር በጣም ብዙና
ትልቅ ህልም አለኝ፤ እኔ ኢትዮጵያ ቡናን
የሚያክል ታላቅ ክለብ እንዲሁም ለሀ-
17 ብ/ቡድን በመጫወት ግቤን (ጎሌን)
ለማሳካት ሞክሬያለሁ እንጂ ህልሜን መኖር
ጀምሬያለሁ ብዬ ስለማላስብ ከክለቡ ጋር
ለማሳካት የምፈልጋቸው ህልሞች አሉኝ፡፡
ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ከኢትዮጵያ ቡና
ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሣት ከእኛ በፊት
የዚህ ታሪክ ባለቤት ከሆኑት ተጨዋቼች
ጋር ታሪክ መጋራትንና ማፃፍን እፈለጋለሁ፤
ከዚህ ከፍ ያለው ህልሜ ደግሞ ከኢትዮጵያ
ቡና ጋር ሀገር ወክለን በኢንተርናሽናል
የውድድር መድረክ መካፈልና ክለቡንም
ሀገሬንም የሚያስጠራ፣ የሚያኮራ ውጤት
የማስመዝገብ ትልቅ ህልም ነው ያለኝ፡፡ ይሄ
ሁሉ የሚያምር ደጋፊ በሀገር ውስጥ ብቻ
ተገድቦ መቀመጥ አይገባውም፡፡ ትልቅ ክለብ
ነው በአህጉሪቱ ትልቁ የክለቦች ውድድር ላይ
ከታላላቅ የአፍሪካ ክለቦች ጋር መወዳደርና
መታየት ያለበት ክለብ ነው፡፡ ይህ አለመሆኑ
ይቆጨኛል፡፡ እነ መከላከያ፣ እነ ጅማ አባጅፋር
እተሳተፉ ቡናን የሚያክል ክለብ ከዚህ ውጪ
መሆኑ ለእኔ ያስቆጨኛል፡፡ ይህንን ታሪክ
የመቀየር ሕልም አለኝ፡፡ ይሄንን ደግም አሁን
ባለው ትውልድ ተሳክቶ የምናይ ህልሜም
ወደ እውነትነት የሚቀየር ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …እንደ ሀገርስ…ምን
ታልማለህ…?
አቡበከር፡- …በክለብ ጥሩ ሣትሆን…
ከክለብህ ጋር ጥሩ ስራ ሳትሠራ ሀገር
የመወከል እድል የሚሰጥህ የለም፤ በኢትዮጵያ
ቡና የተሻለ ነገር ማድረግ ከቻልኩ ሀገሬን
በብቃት የማገልግልበት እድልም ይፈጠራል፡
፡ የብ/ቡድንን ማልያ የመልበስ እድል አግኝቼ
የምጫወት ከሆነ የእግር ኳሱን ታሪክ ከሌሎች
ጓደኞቼ ጋር ለመቀየር፣እግር ኳሱ አንገቱን
ቀጥ እንዲያደርግ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ?
ሀትሪክ፡- …ስለ ግል ህይወትህ እናውራ
እስቲ… ገና ልጅ እንደሆንክ ባወቅም በእድሜህ
አቻ የሆነች የፍቅር ጓደኛ አታጣም ብዬ ባስብ
ተሳስቼ ይሆን…?
አቡበከር፡- …በጣም ተሳስተሃል…(በጣም
ሳቅ)…የፍቅር ጓደኛ የለኝም፡ አሁን የፍቅር
ጓኛዬ ሙያዬ ነው፡፡ በዚህ እድሜዬ መቅደም
ያበትም ይሄ ነው፡፡ ወደፊት አላህ ሲፈቅድ
እድሤዬ ለዚህ ሲበቃ የምናየው የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡-በትልክ ክለብ ውስጥ
የምትጫወት ስም ያለህ ተጨዋች ከመሆንህ
አንፃር “እናደንቅሃለን እንወድሃለን”
በሚል? ሽፋን የፍቅር ጥያቄ ጋጋታስ
አላጋጠመህም…?
አቡበከር፡-ብዙዎች ስሜንና ሜዳ ላይ
ያለውን በማየት ብቻ በተለያ መንገድ
ሃሳባቸውን ለመግለፅ የሞከሩበት ሁኔታ
የለም ብዬ አልክድህም፤ በቴሌግራም፣
በተለያየ መንገድ ስልኬን አግኝተው ሜዳ
ላይ ብቻ ባዩኝ ግን በማይውቁት የውጪ
ባህሪዬ ይጠይቁኛል፡፡ ለምን ጠየቁኝ አልልም
መብታቸው ነው፤ ለጥያቄያቸው ግን ፍፁም
ትህትናና አክብሮት የተሞላበት ምላሽ
እሰጣችኋለሁ፡፡ ለጊዜው ትኩረቴ ኢትዮጵያ
ቡናንና ሀገሬን ማገልገል ላይ ነው ስለዚህ
ነገር አሁን አላስብም፤ እላቸዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ፌስቡክ ላይ እንዴት ነህ…?
ምን ያህል ተከታታይ አለህ?
አቡበከር፡- አካውንት አለኝ፤ መረጃ አልፎ
አልፎ ለማየት ካለሆነ በስተቀር ፌስ ቡክ ላይ
ተጥጄ የምውል አይነት ሰው አይደለሁም፡፡
ሀትሪክ፡- …በምን ዘና በማለት… ትርፍ
ጊዜህን ታሳልፋለህ… ?
አቡበከር፡- …ብዙም በመዝናናት
የማሳልፍ ሰው አይደለሁም…፤…ከጨዋታ
በፊትም ከጨዋታ በኋላም ከግቢ የመውጣት
ልምድ የለኝም፡፡ ከካምፕ ውጪ ሌላ ቦታ
አልሄድም፤ሄድኩ ከተባለ ወደ ቤተሰቦቼ ጋር
አልያም ከሰፈሬ ልጆች ጋር ነው የማሳልፈው፡
፡
ሀትሪክ፡-ከሀገር ውጪ የምታደንቀው
አሰልጣኝ ማን ነው ብልህ መልስህ
ምንድነው…?
አቡበከር፡- በፊት በፊት አርሴን ቬንገርን
ነበር፤ እሳቸው ከወጡ በኋላ ወደ ጋርዲዮላ
አደላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከተጨዋቾችስ…?
አቡበከር፡- …ሮናልዲንሆ ጎቾና ሊዮኔል
ሜሲ
ሀትሪክ፡- …ከብ/ቡድንስ… ?
አቡበከር፡- …ያው ብራዚልን ነዋ… (ሳቅ)
ሀትሪክ፡- …ሮናልዲንሆን
እንደምታደንቀው ተናግረሃል…፤ አዲስ አበባ
በመጣ ጊዜ በቅርበት ያገኘህበት አጋጣሚ
አለህ….?
አቡበከር፡- …ከ17 አመት በታች ቡድን
ጋር በተጫወትኩበት እለት አንድ ቡድን
ውስጥ ሆነን አብረን ተጫውተናል፡፡ በጣም
ከማደንቀው ተጨዋች ጋር አብሬ አንድ ቡድን
ውስጥ በመጫወቴ፣ ኳስ በመቀባበሌ ልዩ የሆነ
የደስታ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ሮናልዲንሆ
ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሣይሆን በመላው
አለም ትልቅ ስምና ክብር ያለው ተጨዋች
ነው፤እንደ እሱ አይነት ጥበበኛ ተጨዋች
አለማችን ከእሱ በኋለ ያየች አይመስለኝም፤
ምትሀተኛ ተጨዋች ነው፡፡
ሀትሪክ፡-አንዳንድ ተጨዋቾች ጨዋታ
ይመርጣሉ፤ የሚከብድህ ጨዋታ አለ…? …
ከጨዋታ ጨዋታስ የምታበላልጠው አለ…?
አቡበከር፡- …እኔ ጨዋታን ትልቅ
ወይም ትንሽ (ቀላል) ብዬ አላበላልጥም፤
ሁሉም ጨዋታ ለእኔ እኩል ነው፤ እንደውም
እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ትላልቅ የሚባሉ
ጨዋታዎችን መጫወትን ነው የምመርጠው፡
፡ የሚከብደኝም የሚቀለኝም ጨዋታ የለም
ባጭሩ፡፡
ሀትሪክ፡- …አጠገብህ አብሮህ… ማን
ሲጫወትስ… ጨዋታው የበለጠ ይቀልሃል…?
አቡበከር፡- …በፊት… በፊት… መስዑድና
ኤልያስን የመሰሉ አማካዮች ስታገኝ ሁሉም
ነገር ይቀልሃል፤ ምክንያቱም ከእነሱ እግር
ስር የሚወጣው ኳስ አንተ ጋር ሲደርስ
ጣጣውን ጨርሶ ነው፡፡ አሁን ካሉት ውስጥ
ሚድፊልድ ላይ (አማን) አማኑኤል ጨዋታ
በጣም ያቀልለሃል፤ፈጥኖ ምን እንደምትፈልግ
ይረዳሃል፡፡
ሀትሪክ፡- …አላነቃንቅ ብሎ
የሚያስቸግርህ… የአንተ ምርጡ… ተከላካይስ
ማነው…?
አቡበከር፡- …ባለፈው በደርቢው ጨዋታ
ትንሹ ብንጋጭም… ለእኔ የሀገሪቱ ምርጥ
ተከላካይ… የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ
ነው፤ አስቼ ለአጥቂዎች ፈተና የሆነ ኳስን
በደንብ የሚችል ተከላካይ ነው፤ ለእሱ የተለየ
አድናቆትም ክብርም አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ሁሌም የምታስታውሰው
ከአእምሮህ የማይጠፋ የተለየ ቦታ የምትሰጠው
ጨወታስ አለ…?
አቡበከር፡- …ከፋሲል ከነማ ጋር
ላደረግነው ጨወታ የተለየ ቦታ እሰጣለሁ፤
ሁሌም በመልካምነቱ ሳነሣው ነው የምኖረው።
ፋሲል ላይ ያደረግነው ይሄ የሊጉ ጨዋታ
በጣም እልህ አስጨራሽ፣ አሸናፊውን ለመለየት
እንኳን ያስቸገረ ጨዋታ ነበር፡፡ በጨዋታው
እኛ 1ለ0 ከመመራት ተነስተን ማሸነፋችን
ብቻ ሣይሆን ፋሲሎች ሲያገቡ እኛም እያገባን
በጣም ደስ የሚል ፉፉክር እያደረግን
ነበር፡፡ እኔ በእለቱ ተቀይሬ ነበር የገባሀት፤
ተቀይሬ ገብቼ የማሸነፊያዋን ጎል በማስቆጠር
ጣፋጭ ድል ይዘን የተመለስንበትን ጨዋታ
በሌላ የተለየ ታሪክ ካልተቀየረ በስተቀር
ሳስታውሰው ነው የምኖረው፡፡
ሀትሪክ፡-ኢትዮጵያ ውስጥ በግራ ክንፍ
ተጨዋችነት የምታደንቀውስ… ?
አቡበከር፡-ሚኪያስና ጋዲሳን ነው፡
፡ ሁለቱም በዚህ ቦታ በጣም ጥሩ ናቸው፡፡
ጋዲሳ አሁን አሁን ትንሽ ቀዝቀዝ አለ እንጂ
ሃዋሳ በነበረበት ጊዜ በቦታው በጣም ጥሩ ነበር
የሚንቀሳቀሰው፡፡
ሀትሪክ፡-ከሚኪያስ ጋር በአንድ ክለብ
ከመጫወታችሁ ውጪ አብሮ አደጎች ናችሁ፤
ለእሱም የተለየ ቦታ እንዳለህ ተናግረሃል በዚህ አጋጣሚ ሚኪያስ በሀ-17 ግብፅ ላይ
ስላስቆጠራት ምርጥ ግብ እስኪ አንድ ነገር
በል…?
አቡበከር፡- ከሚኪ ጋር እንዳልከው
ነው አብሮ አደግ ፤ የአንድ ሰፈር ልጆችም
ነን፡፡ አሁንም አብረን እየተጫወትን
ነው፤ለችሎታው የተለየ ክብርም አለኝ፡፡
እንዳልከው ሚኪያስ ግብፅ ላይ ያስቆጠራት
ኳስ አጋነንክ ካላልከኝ በስተቀር ኢትዮጵያ
ውስጥ እንደዚህ አይነት ግብ ተቆጥሮ
አላየሁም፤ አውሮፓ እግር ኳስ ላይ ካልሆነ
በስተቀር። በእለቱ ጨዋታውን ሲያሳተላልፍ
የነበረው ኮሜንታተርም በጣም አድንቆት
ነበር፤ ሚኪያስ ያለው ብቃት ልዩ ነው፡፡
በተለይ ሰው እየቀነሱ ማለፍ ላይ ኢትዮጵያ
ውስጥ ብቃት ካላቸው አንዱ ነው፤ በዚህ
እድሜው እንዲህ ከሆነ ከፍ ሲል ምን
ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የክለባችሁ የቅጣት ምትና
የፍፁም ቅጣት ምት አንደኛ መቺ ማነው…?
አቡበከር፡- …እውነት ለመናገር አንደኛ
መቺ እኔ ነኝ…፤…አሰልጣኞችንም ይሄንን
በግልፅ ተናግሯል፡፡ “በግራም ይሁን በቀኝ
እሱ ይምታ እንዳትደርሱበትም” ብሏል፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄንን ያለ ምክንያት
አይደለም ያነሳሁልህ፤ባለፈው ጨዋታ ላይ
ቅጣት ምት ለመምታት ስትሻሙና በተለይ
አንተ ካልመታሁ ብለህ መጨቃጨቅህ
በርካታ ደጋፊዎችን ቅር ማሰኘቱን ልብ
ብለሃል… ?
አቡበከር፡- …በዚህ ነገር እኔም በጣም
አዝኛለሁ፤በድቻ ጨዋታ እለት ከምንትአብይ
ጋር ፀብ ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ነበር፤እኔ
ልምታ…እኔ ልምታ… ከሚል… ይህ
ሁኔታ ደጋፊዎቻችንን እንዳላስደሰተም
ተረድቻለሁ፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ “ገና
በዚህ እድሜው ይጨቃጨቃል?፤ ገና
ሳያድግ ከአሁኑ እስከመጠላት ደረሰ?” ሁሉ
ተብያለሁ፡፡ እኔ ግን በወቅቱ ያንን ያደረኩት
ጨቅጫቃ ስለሆንኩ ሳይሆን በአሰልጣኜ
የተመደብኩ አንደኛ መቺ ስለሆንኩ መሆኑ
እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ደጋፊውን
በዚህ መልኩ ማሳዘንም እኔንም በሌላ
መልኩ እንዲረዳኝ አልፈልግም፡፡ አኔ ልምታ
በሚል መጨቃጨቃችንም ለክለቡ አንድ
ነገር ለማድረግ ካለን ጉጉት ተደርጎ ቢወስድ
ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ የቡድኑ የፊት አጥቂ
ሆነህ፤ አብዛኛዎቹ ጎሎችህም በፍፁም ቅጣት
ምት (ፒናሊቲ) የተገኙ ናቸው፡፡ ፔናሊቲ
ማስቆጠር በራሱ አንድ ኳሊቲ ቢሆንም
መቼ ነው በጨዋታ ግቦች ስታመርት ክለቡን
በዚህ ውጤታማ ስታደርግ የምትታየው… ?
አቡበከር፡- …እንዳልከው ነው… በፍፁም
ቅጣት ምት እያገባሁ ነው፤ ከእኔ የሚጠበቀው
ይሄ ብቻ ባለመሆኑ በጨወታም ማስቆጠር
ይጠበቅብኛል፡፡ ደጋፊዎች አካባቢም ይሄ
ነገር ሲነሣ እሰማለሁ፤ ለዚህ ጥያቄ ወይም
ቅሬታ መልስ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ፡
፡ ደጋፊውን ከፔናሊቲ ውጪ በማግባት
ማሳመንና ይሄ ጥያቄ አንዲቀረፍ ማድረግ
ቀጣይ ስራዬ ነው የሚሆነው…፤አኔም ራሴን
ብትጠይቀኝ በፔናሊቲ ብቻ በማገባቸው ጎሎች
ብዙም ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ከቲሙ ጋር
ብዙ ግቦችን በተለይ በጨዋታ ማስቆጠር
እፈለጋለሁ፤ ከቲሙ ጓደኞቼ ጋር ይሄንን
አሳካለሁ፤ ምክንያቱም እነሱ የሚሰጡኝን
ኳሶች ነው ወደ ጎልነት የምቀይረው፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ደዲዬ ጎሜዝ ለአንተ
የተለየ ቦታ እንዳለው ይነገራል፡፡ በክለቡ
እንደትሰለፉ የተለየ ድጋፍ ተደርጎልሃል…?
አቡበከር፡- እኔ ቡና መሰለፍ የጀመርኩት
በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ጊዜ ነው፤ በአባይ ግድብ
ዋንጫ ላይ ተሰለፍኩ አገባሁ፤ በፕሪሚየር
ሊጉም ሲዲማ ላይ ከሲዲማ ቡና ጋር
ተጫውተን 3ለ1 ስናሸንፍም እንዲሁ አገባሁ፡፡
በ2ዐ1ዐ አሰልጣኝ በመቀያየሩ ብዙም የጨዋታ
እድል አላገኘሁም፤ ዲዲዬ ጎሜዝ ሲመጣም
መጀመሪያ ላይ የተጨዋቾችን ብቃት እያየ
ስለነበር የመሰለፍ እድሉም አልነበረኝም፡
፡ ከዚያ በኋላ ነው እድሉን ሰጥቶኝ ቤስት
ውስጥ መሰለፍ የጀመርኩት። ዲዲዬ በጣም
ትልቅ አሰልጣኝ ነው፤ በተለይ በታዳጊዎች
ላይ ትልቅ እምነት ያለው አሰልጣኝ ነው፡
ሀትሪክ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ
ደጋፊዎች በክለቡ አጨዋወት ላይ ቅሬታ
ያሰማሉ፤ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ ኢትዮጵያ
ቡናን ለውጦታል ትላለህ…?
አቡበከር፡- አሠልጣኝ ዲዲዬ አምና ጥሩ
ነገር ሰርቷል፣ ሲቲ ካፑን አግኝቷል፡፡ ዘንድሮ
ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉን የሚመራ ቡድን ነው
ይዞ እየተጓዘ ያለው፡፡ አሁን በውጤቱ በኩል
ጥሩ ብንሆንም ደጋፊው “የለመድነው ጨዋታ
የለም” በማለት ቅሬታ ሲያሰሙ ይደመጣል፡
፡ በእርግጥ ይሄ ስሜት ተጨዋቾችም ጋ
አለ፤ ደስተኛ ያለመሆን ነገር አለ፡፡ ደጋፊው
ያየውን ነገር ነው የሚናገረው፤ ጨዋታ
አስፈላጊ እንደሆነ አልክድም፤ ውጤት ግን
ከባድ ነገር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ከባዱን
ነገር ይዘናል ጨዋታው በቀጣይ ቀስ እያለ
ይመጣል፡፡ ምናልባት አሁን አንድና ሁለት
ጨወታዎች ጥሩ ስላልሆንን ጨዋታ ጠፋ
ብለን ባንደመድም መልካም ነው፤ ምክንያቱም
ጥሩ ኳስ የሚጫወት ቡድን እንዳለ ሲቲ ካፑ
ላይ አሣይተናል፡፡ ያንን ነገር ነው ማስቀጠል
ያለብን፡፡ አሁን በቡድናችን ብዙዎቹ ሲኒየሮች
የሉም፡፡ በቀጣይ ቡና የሚታወቅበትን ጨዋታ
ከውጤት ጋር አጠናክረን የምንቀጥል ነው
የሚሆነው፡፡ በነገራችን ላይ አሠልጣኞችንም
ኳስ እንድንጫወት ነው የሚነግረን፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን በሀገሪቱ ትልቅ ክለብ
ውሰጥ በመጫወት ወደ የዝናን ጣርያ
ለመንካት እየተቃረብክ ነው፤ አሁን ያገኘኸውን
ስም ያህል በኑሮህስ ተለውጠሃል… ?
አቡበከር፡-አንድ የማልክደው ነገር
ኢትዮጵያ ቡና መጫወቴ ለእኔም ለቤተሰቤም
ትልቅ ክብርን ይዞልን መጥቷል፤ ትናንት
ቦታ የማይሰጡን ሰዎች ዛሬ የተለየ ቦታ
ሰጥተውናል፡፡ ከዚህ ውጪ በሀብት ደረጃ
እንደዚህ ነው የምለው ነገር የለም፤ ምክንያቱም
ነገሮችን ገና አንድ ብዬ ነው የጀመርኩት፡፡ያም
ቢሆን ግን ከትናንት ዛሬ ለእኔም ለቤተሰቦቼም
በጣም የተሻለ ነው፤ እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ
እንኳን ሀብት በሀብት ልንሆን የራሳችን
መኖሪያ ቤት እንኳን የለንም፡፡ ግን ይሄ ታሪክ
ሆኖ መለወጡ አይቀርም፤ ደግሞ ሀብት
ማለት ለእኔ ዋናውና ትልቁ በጤና መኖርን
ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙ ተጨዋቾች ትንሽ ሲታወቁ
ሮጠው መኪና ላይ ነው፤ አንተስ በዚህ
በኩል…?…መኪና… ገዝተሃል…
አቡበከር፡- …እስከአሁን አልገዛሁም፤…
ምክንያቱም ከመኪና ከግል ቅንጦቴ በፊት
ቤተሰቤን ነው ማስቀደም የምፈልገው…።
እኔ የቤተሰቦቼ እዳ ነኝ፤ ለፍተውብኛል፤
ደክመውብኛል፡፡ የእነሱን እዳ ሳልከፍል
ወደ መኪና መሮጥን አዕምሮዬ
አያስበውም፤ለፍተው ያሳደጉኝን ቤተሰቼን
ካስሰትኩኝ በኋላ ነው ስለ ግል ደስታዬ ማሰብ
የምጀምረው፤ ለእኔ ከቁሳቁስ በላይ ትርጉም
ያለው ነገር ይሄ ነው፤ ቤተሰቦቼን ስረዳ ነው
ፈጣሪ ከጎኔ የሚሆነው፤ የበለጠም የሚረዳኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ስለፕሮፌሽናል ተጨዋችነትስ…
አዕምሮህ አስቦ ያውቃል…?
አቡበከር፡- …የአንድ ተጨዋች ረዥሙ
ህልሙ ይሄ ይመስለኛል፤ እኔ ገና በሀገር
ውስጥ ብዙ የምሰራቸው ሥራዎች እንዳሉ
ባምንም ወደፊትም ቢሆን ፕሮፌሽናል
ስለመሆን አስባለሁ፤ አሁን እንደውም
አንዳንዶች የጨዋታ ህይወትህን የሚገልፅ
ቪደዮ አሰባስብ ብለውኝ ከክለባችንም ይሁን
ከተለያየ ቦታ እየጠየኩ ነው፡፡ እንደ ሰው
ታስባለህ አላህ ነው የሚያሳካው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ መናገርም
ማመስገን የምትፈልገውም ካለ?
አቡበከር፡- በመጀመሪያ አላህን በመቀጠል
ሁሉን ላደረጉልኝ፣ ለለፉልኝ፣ ሰው እንድሆን
ሣይሰለቹ ለደገፉኝ ቤተሰቦቼ እናትና አባቴን
እህትና ወንድሞቼን ከልብ አመሰግናለሁ፡
፡ በመቀጠል የሰፈር ልጆችን ስም መጥራት
ቢቸግረኝም ሁሉም አሁን ድረስ አጠገቤ
ናቸውና አነሱም አመሰግናለሁ ፡፡ በመጨረሻ
እስካአሁን የስልጠና አሻራቸውን ያሳረፉቡኝን
አሠልጣኞች በሙሉ ማክበርና ማመስገን
ነው የምፈልገው። ሰፈር ውስጥ ብዙ
አልሰለጠንኩም፤ የተወሰነም ቢሆን ደረጀ
(ሊቴ)፣ በይበልጥ ዳዊት ቀለመወርቅ (እባቡ)
ኳስ እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ ያሳየኝ
ሙሉጌታ ወልዴ አሁንም ድረስ አጠገቤ ያሉ
ሰዎች ናቸውና ለእነሱም ምስጋና አቀርባለሁ፡፡