“በደንብና በመመሪያ ስለሚሰራ የጥቅም ግጭት ይከሰታል ብዬ አልሰጋም”
አቶ ዳዊት ውብሸት
/የቅ/ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር የቦርድ አባል/
” እኛ በር ሆነን ሌሎች ቤቲንግ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እንዲመጡ ማገዝ አለብን””
ወ/ሮ ንጋት ሙሉጌታ
የዊነር ኢቲ ቤቲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ
ባለፉት ሁለት አመታት የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስና ዊነር ኢቲ. ስፖርት ቤቲንግ ለሶስት አመት የሚዘልቅ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረሙ ።
- ማሰታውቂያ -
ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው ስምምነት መሠረት ለቀጣዮቹ የላቀ የስትራቴጂ የአጋርነት ውል በመጀመሪያ አመት 25 ሚሊዮን ብር የሚከፈል ሲሆን ቀጣዮቹ ሁለት አመታት ላይ የዊነርን ስራ፣ የክለቡን ውጤትና የዋጋ ግሽበቱን ከግምት በማስገባት በሁለቱ ወገኖች የጋራ ስምምነት መሠረት የሚከፈል መሆኑ ታውቋል።
በዊነር ኢቲ ቤቲንግ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ንጋቷ ሙሉጌታ ” ዊነር አሸናፊነት ነው ቅዱስ ጊዮርጊስም የአሸናፊዎች ክለብ ነው ሁለቱም አሸናፊነትን ከፊት አስቀድመው የሚያደርጉት የሶስት አመት የጥምረት ጉዞለሁለቱም ወገኖች የላቀ ስኬትን የሚያጎናጽፍ እንደሚሆን እተማመናለሁ ስምምነቱም የአሸናፊዎች በመሆኑ ደስተኞች ነን
በ88 አመት የቅ/ጊዮርጊስ ታሪክ ውስጥ አሸናፊ ጉዞ ካደረገ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ ከሆነ ቡድን ጋር አብረን ለመስራት በመስማማታችን ተደስተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ በበኩላቸው ” የሁለቱ ወገኖች ስምምነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነው ማለት ይቻላል… የተቋሙ 25 ሚሊየን ብር መክፈል በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያንጸባረቀ ውል መሆኑን ያሳያል ይህም ስምምነቱንም ትልቅ ያደርገዋል በ88 አመት ታሪኩ የገጠመውን ችግር በሰከነ አመራር በትዕግስት የተወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ኩራት የኢትዮጵያ አርማ የተሰኘው” ሲሉ አስረድተዋል።
በስምምነቱም መሠረት ዊነር ከገንዘቡ ውጪ የክለቡን ሙሉ ትጥቅ ወጪ የሚሸፍን ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስም በኩል በዋና ቡድኑ ማሊያ ላይ አርማውን ያደርጋል የክለቡ መለማመጃ ልብስ ላይ ያደርጋል በጨዋታ ወቅት ማስታወቂያ ላይ ክለቡ በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች፣ ልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ የተለያዩ የክለቡ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ የዊነር አርማ ይደረጋል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቤቲንግ ተቋማት መብዛታቸው የጥቅም ግጭት ይፈጥራል የሚለውን ስጋት እንደማይቀበሉት ሁለቱ ተፈራራሚ ወገኖች ይፋ አድርገዋል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዊነር፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቤቲካ እንዲሁም ከፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሁሉ ስፖርት የተሰኙ የአቋማሪ ተቋማት የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት መፈጸማቸው የጥቅም ግጭት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ቢሰጋም አቶ ዳዊት ግን ስጋት ኤንደሌለባቸው አስረድተዋል። ” በደርቢው ጨዋታ ሶስት የአቋማሪ ተቋማት ቢኖሩም አወዳዳሪው አካል በሚያወጣው የውድድር ደንብና መመሪያ የማንም ጥቅም ሳይነካ እንስተናገዳለን ብዬ አስባለሁ። እንግሊዝ ውስጥ በርካታ ክለቦች የቤቲንግ አርማ አድርገው ነው የሚገቡት….
አፍሪካ ውስጥ ስንመጣ የታንዛኒያ ሊግ ተቀናቃኞች ሲምባና ያንግ አፍሪካ በተመሳሳይ የሚገቡት በቤቲንግ ነው ያን ያህልም መጋነን የለበትም በደንብና በመመሪያ ስለሚሰራ የጥቅም ግጭት ይከሰታል ብዬ አልሰጋም” ሲሉ የዊነር ኢቲ ቤቲንግ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ንጋት ሙሉጌታ በበኩላቸው “የቤቲንግ አቋማሪ ተቋማት ወደ እግርኳሱ መሳባቸውና መብዛታቸው ሊበረታታ ይገባል እንደውም እኛ በር ሆነን ሌሎች ቤቲንግ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እንዲመጡ ማገዝ አለብን የእኛ መብዛት ውድድሩ ላይ የሚፈጥረው ምንም አይነት የጥቅም ግጭት አይኖርም አወዳዳሪው አካል መላ እንደሚያበጅለት ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።