“ቡደናችንን ከለቀቁት አንጻር የሳሳ ይመስላል አትጠራጠሩ ድሉ ግን የኛ ነው”
” አምናና ካቻምና ገጥሞን እንደነበረው የፋይናንስ ክፍተት ዘንድሮ ግን አንቸገርም”
አቶ ዳዊት ውብሸት
/ የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር
የቦርድ አባል/
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በውድድር ሜዳ ያለባቸውን ፍልሚያ በድል እየተወጡ የተቋረጠውን ፕሪሚየር ሊግ እየመሩ ነው ከአምስት በላይ ኮከቦቻቸውን አሳልፈው ሰጥተው በወጣቶች ቢገቡም ጠንካራ ጉዞ እያደረጉ መገኘታቸው ደግሞ ግርምትን ፈጥሯል…. ከሜዳ ውጪ ከባድ ትግል የገጠማቸውና የተከሰተው የፋይናንስ ፍልሚያ መነጋገሪያ ያደረጋቸው ፈረሰኞቹ ከባዱን ጊዜ እያለፍነው ይላሉ….ነገ ጠዋት አራት ሰዓት በስካይ ላይት ሆቴል ዊነር ከተሰኘ የቤቲንግ ኩባንያ ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለመፈራረም ቀጠሮ የያዙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደዚያም ሆኖ የሊጉን ዋንጫ ለሶስተኛ ተከታታይ አመታት እንደሚያነሱ ይናገራሉ…ከሀትሪክ ድረገጹ ባልደረባ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረጉት የክለቡ የቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ሀትሪክ:- የፕሪሚየር ሊጉን ጅማሮ እንዴት ገመገማችችሁት…?
- ማሰታውቂያ -
ዳዊት:- ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ወደ ውድድር ገብቷል። በእስካሁኑ አምስት ጨዋታ አራቱን አሸንፎ አንዱን አቻ ወጥቶ በ13 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል..በዚህ ጅማሮ ደስተኞች ነን ቡድናችንም ጥሩ የሚባል ጉዞ እያደረገ ነው በሂደት ግን የተሻለ ለመሆን ጠንክረን እንሰራለን በዚህ ላይ ጉዳት ላይ ያሉት እነ ቢኒያም ዳግም ሲመለሱ የተቋረጠው ውድድር እስኪጀመር ድረስ የተሻለ ተቀናጅተን እንደምንመለስ ተስፋ አደርጋለሁ….ከዚያ በኋላ ያሉት ተከታታይ ውድድሮች ጠንከር ያሉ ስለሚሆኑ ጥሩ ተዘጋጅተን አሸናፊነታችንን እናስቀጥላለን ብዬ አስባለሁ።
ሀትሪክ:- ከሜዳ ውጪ ያለውስ ፈተና…?
ዳዊት:- እንደ መጀመሪያ ከቢጂአይ ጋር ያለንን ውል ለማደስ የሚያስፈልጉንን ሁሉ ፈጽመን በይፋ ለመፈራረም ከጫፍ ደርሰናል የሚቀረን የወረቀት ስራ ብቻ ነው በጥቂት ቀናት የምንፈራረም ይሆናል ዞሮ ዞሮ ግን ከቢጂ አይ ጋር ያለን ውል የሚፋታ ስላልሆነ ከማደስ ውጪ ሌላ አዲስ ነገር ይፈጠራል ብለን አንሰጋም…. ከጸሀይ ባንክ ጋርም የ5 ሚሊይን ብር ስምምነት ፈጽመን ወደ ስራ ገብተናል …ለኛ ትልቅ የሚባለውን አካዳሚያችንን በደንብ ገንብተን የመለማመጃ ሜዳውን ለማሰራት በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ሊሰጡን ተስማምተን እየጠበቅን ነው ያም ሆኖ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አሁኑኑ መስራት እንዳችል ቦታውን አጥሮ ለመጀመር በከተማ አስተዳደሩ የግንባታ ፍቃድ በመታገዱ አልቻልንም ባንኩ ደግሞ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሠረት ለጊዜው ብድር እየሰጡ አይደለም ሁለቱ ጉዳዮች ሲፈቱ በርግጠኝነት ወደ ስራ የምንገባ ይሆናል… በኛ በኩል ዲዛይኑን ሰርተን አስፈላጊውን ነገር ጨርሰን ተዘጋጅተናል ነገሮች እንዳለቁ ወደ ስራ እንገባለን…ያለው ሁኔታ ይሄ ነው…
ሀትሪክ:- ተጨማሪ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ልትፈራረሙ መሆኑ ይታወቃል..ሂደቱ ምን ይመስላል..?
ዳዊት:- ዊነር የተሰኘው የቤቲንግ ኩባንያ ኢትዮጵያ ገብተዋል… ከእኛ ጋር ተስማምተው ውለታ ፈጽመዋል.. ስምምነቱ በማለቁ ማሊያችን ላይ ለጥፈን እየተጫወትን እንገኛለን በጨዋታ ጊዜ አንዳንድ ማስታወቂያቸውን እየሰሩ ነው በሶሻል ሚዲያም እያስተዋወቁ ይገኛሉ.. የዚህ አይነት ስምምነት ሲካሄድ ለህብረተሰቡ ለደጋፊዎቻችን መግለጽ ስለሚጠበቅ ስምምነቱ ሃሙስ ጠዋት 4 ሰአት በስካይ ላይት ሆቴል በሚካሄድ ስነስርዓት ይፋ ይደረጋል የዘገየውም በተባለበት ጊዜ ቦታ አለማግኘትና በራሳቸው ጊዜ ከውጪ የሚመጡ እንግዶች ጋር አለመገጣጠሙ ነው … በአጠቃላይ ሶስቱ ስፖንሰሮቻችን ሃይላንድ ውሃን ጨምሮ እነሱን ይዘን እየሰራን ቡድናችንን ወደ ላይ ከፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ለቀጣይ ደግሞ ሌላ እየተሞከረ ያለውን የስፖንሰርሺፕ ሙከራ ሲሳካ ደግሞ ይፋ የምናደርግ ይሆናል።
ሀትሪክ:- ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ ያነሳል የሚለው ሃሳብን ልብህ የምር ያምንበታል…?
ዳዊት:-/ ሳቅ/ እውነት ነው ቡደናችንን ከለቀቁት አንጻር የሳሳ ይመስላል አትጠራጠር ድሉ ግን የኛ ነው… በርግጥ ቡድኑ ቅንጅት ያስፈልገዋል አዲሶቹ ወጣቶች ታዳጊዎቹ ጥሩ ነገር እያሳዩን ነው ልምድ ያስፈልጋቸዋል በቀሪዎቹ ቀናቶች ታዳጊዎቹን እያበረታን እያጠነከርን እንሄዳለን አጥቂው ሞሰስ ጥሩ እየለመደ ነው ማስቆጠር መጀመሩም በራስ መተማመኑን ስለሚጨምርለት የተሻለ ይሆናል.. ይሁን እንጂ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የምጠራጠው ነገር የለም በአምስቱ ጨዋታዎችም አልተሸነፈም ከጊዜ አንጻር ካልሆነ በስተቀር ቡድናችን ምንም ችግር የለበትም።
ሀትሪክ:- የፋይናንስ ፈተናው ግን አላንገዳገዳችሁም..?
ዳዊት:- ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውት አልፎታል የአሁኑን ፈተና ለየት የሚያደርገው የፋይናንስ ፈተና መሆኑ ነው ከዚህ በፊት በፖለቲካው በአንዳንድ ከደጋፊ ጋር ያለ አለመግባባት የሚፈጥረው ረብሻ ይሆናል ፈተናው …. የአሁኑ ፈተና የጠበቀው ችግሩ የፋይናንስ ነው ፋይናንስ ደግሞ የደም ስር ነው እሱ ከሌለ ምንም መንቀሳቀስ ስለማይቻል ከባድ ፈተና ሆኗል ነገር ግን አሁንም ይህን ፈተና ባለፉት ሁለት አመታት በምንችለው አቅምና ትግል አልፈን ሻምፒዮንም ሆነናል አሁን ከሞላ ጎደል ችግሩን መቅረፍ በምንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። ምክንያቱም አሁን የመጡት ሁለቱ ስፖንሰሮችና ቢጂ አይ የሚሰጡንን
ጨምረን ቡድናችንን ማስተዳደር የሚቻልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን በምንፈልገው ደረጃ ባይበቃንም በጣም የሚያሰጋን ወይም የሚያስፈራን አይደለም የምናገግምበትን ስትራቴጂ ዘርግተናል..አሁን እየተነጋገርን ያለነው ስፖንሰር አለ እሱ ከተሳካ የተሻለ ጥሩ እንደምንሆን አምናለሁ ከዚህ በኋላ ግን ሜዳውን አካዳሚውን ሰርተን ለአገልግሎት ስናውለው ሌላ ገቢ ስለምናገኝ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ልንከፍት ያሰብናቸው አሉ ዝግ የነበረው “ፈረሰኞቹ” ይከፈታል ጨዋታዎቹ አዲስ አበባ ስታዲየም ከመጣ ገቢ ስለምናገኝ ፣ ከዲ ኤስ ቲቪ የምናገኘው አለ ከከተማው መስተዳደር ድጋፍ እንገጠቃለን እነኚህ ሁሉ ከመጡ ቀጣይ ጊዜያችን አሪፍ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ በአጠቃላይ ግን አምናና ካቻምና ገጥሞን እንደነበረው የፋይናንስ ክፍተት ዘንድሮ ግን አንቸገርም ።
ሀትሪክ:- እስቲ በከፍተኛ አመራር ደረጃ እየሰራህ ስላለህበት ፊያታ እናውራ…?
ዳዊት:- ፊያታ ማለት የአለም አቀፍ የጭነት ማስተላለፍና የመርከብ አሶሴሽን ሲሆን 46 ሺህ አባላት ያሉት ግዙፍ ተቋም ነው ከነኚህ 40ሺዎቹ ካምፓኒዎች 6 ሺህ የግል አባላት ናቸው ስራው አለም ላይ ያለውን የሎጀስቲክስ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ደንብ የሚያወጣ ስርአቶችን የሚያስዝ የነበረውን ክፍተት እየሞላ የአለምን የሎጀስቲክ ፍሰት የሚያሳልጥ ትልቅ ተቋም ነው ይህን ትልቅ ተቋም የተቀላቀልኩት ከኢትዮጵያ የጭነት ማስተላለፍና የመርከብ አገልግሎትን በም/ል ፕሬዝዳንትነት እያገለገልኩ ነው ይህን ተቋምና ኢትዮጵያን ወክዬ ተወዳድሬ በማሸነፍ ባለፉት ሁለት አመታት የአለም አቀፍ የጭነት ማስተላለፍና የመርከብ አሶሴሽን የቦርድ አባልና በስሩ የሚገኘው የአየር ጭነት ኢንስቲትዩት ሊቀመንበር በመሆን ሳገለግል ቆይቻለሁ በቅርቡ ደግሞ ብራስልስ ቤልጂየም በነበረው ጉባኤ ላይ እንደገና ለመጪው ሁለት አመት እንዳገለግል ተመርጫለሁ
ሀትሪክ :- ብቸኛ አፍሪካዊ ነህ..? ወይስ ሌሎች አሉ..?
ዳዊት :- በእስካሁኑ የ50 አመት የተቋሙ ታሪክ ውስጥ ባለኝ መረጃ በዚህ ደረጃ የመራ አፍሪካዊ የለም .. ብቸኛ ጥቁር እኔ ነኝ በዚህም ደስተኛ ነኝ ባለፉት ሁለት አመታት ጥሩ ስራ ሰርተናል ሰርተን ያልጨረስናቸውን ወደ ፍጻሜ እንዳመጣ ደግሞ እድሉን ስላገኘሁ ደስ ብሎኛል ይሄ እንደ ማህበርም እንደሀገርም ትልቅ ስኬት ነው ከእግዚአብሄር ጋር ወደተሻለ ከፍታ እንደምጓዝ ርግጠኛ ነኝ
ሀትሪክ :- የመጨረሻ …ለፈረሰኞቹ ደጋፊዎች የምትለው ነገር ካለ…?
ዳዊት :- የእስካሁኑን ውጣ ውረድ ችለዋል የገባንበትን ችግር አውቀው ሲያግዙን ሲረዱን ቆይተዋል ..በምንም የማንለውጣቸውን ደጋፊዎቻችንን አመሰግናለሁ… በቀጣይም ቡድናችን ላይ መንገራገጭ ቢያዩ እንኳን በትእግስት በተለመደ ፍቅራቸው እያገዙ እንዲቆዩ ጥሪ አደርጋለሁ ለሶስት ተከታታይ አመታት የዋንጫ ስኬት እየተጓዝን በመሆኑ ድጋፋቸው እንዳይለይ አደራ እላለሁ.. አሁን ሀገሪቷ ውስጥ ባለው ሁኔታ ከቦታ ቦታ መዘዋወር ባይችሉ እንኳን ቤታቸውም ተቀምጠውም ቢሆን የስታዲየሙን ቲኬት በመግዛትና ክለባቸውን በመደገፍ ቡድኑን አባላቱን እያበረታቱ ወደ ድል እንድንጎዝ ጥሪ አደርጋለሁ ይህ እንደሚሆን ምንም አልጠራጠርም በደጋፊዎቻችን ሙሉ እምነት አለን።