ለበርካታ አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ዳኞች ታሪክ ሀገር በመወከል ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈችው ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴን በይፋ ተቀላቅላለች።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከፊፋ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የኤሊት የጨዋታ አመራሮች ኤም. ኤ ኮርስ ዛሬ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደተደረገው ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ በኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ በሚመራው የዳኞች ኮሚቴ ብቸኛዋ ሴት የኮሚቴ አባል መሆኗ ይፋ ተደርጓል።
ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ አባል ሆና በተቀላቀለችው ኮሚቴ ውስጥ ከኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ ውጪ ኮሚሽነር ልዑልሰገድ በጋሻው ፣ኮሚሽነር ሰላሙ በቀለ ፣ ኮሚሽነር በላቸው ይታየውና ኮሚሽነር አዲሱ ነጋሽ እንዳሉበት ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጥቅምት 21 – 25/2016 ለኢንተርናሽናልና ኤሊት የጨዋታ አመራሮች እንዲሁም ለስምንት ሲኒየርና ጀማሪ ኢትዮጵያዊያን ኢንስትራክተሮች የተሰጠውን ስልጠና ያሳተፈው ስልጠና ሞሪሺየሳዊው ቴክኒካል ኢንስትራክተር ሊም ቾንግና ጂቡቲያዊው የአካል ብቃት ኢንስትራክተር መሐመድ ሁሴን መስጠታቸው ታውቋል።
ዛሬ በተጠናቀቀውና በጁፒተር ሆቴል በተካሄደው የስልጠናው መዝጊያ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሚሽነር ሸረፋ ድሌቾ መገኘታቸው ታውቋል።