በቅርቡ ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀምበሪቾ ዱራሜ ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ የነበረዉ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በዛሬዉ ዕለት የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዉን ወልቂጤ ከተማ ለማሰልጠን መስማማቱ ተረጋግጧል።
ከ2003 ጀምሮ ወደ ስልጠናው ብቅ ያለዉ አሰልጣኙ ባለፉት አስራ አንድ አመታት በተለይ በታዳጊዎች ላይ በመስራት በስፋት ይታወቃል። ከደቡብ ክልል ፕሮጀክት አንስቶ በሀዋሳ ከተማ የሴቶች ቡድን ፣ በሀዋሳ ከተማ ወጣቶች ቡድን ፣ በከፍተኛ ሊጉ ላይ በደቡብ ፖሊስ ፣ በሀዋሳ ከተማ ዋናዉ ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ20 አመት በታች ታዳጊ ቡድን ላይ በአሰልጣኝነት መስራት የቻለዉ ተመስገን ዳና በዛሬው ዕለት ደግሞ ሰራተኞቹን ለአንድ አመት ለማሰልጠን መስማማቱ ተረጋግጧል።
አስቀድሞ የወልቂጤዉ አሰልጣኝ ጳዉሎስ ጌታቸዉ በፈረሰኞቹ ከደረሰባቸዉ የ4ለ0 ሽንፈት በኋላ በሰጡት አስተያየት በክለቡ የበላይ ሰዎች ደስተኛ አለመሆናቸዉን እንዲሁም የክለቡ አመራሮች እርሳቸዉ በስራ ገበታ ላይ እያሉ ክለቡ ከሌላ አሰልጣኝ ጋር ንግግር መጀመሩ ቅር እንዳሰኛቸው መግለፃቸው ይታወሳል።