የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ በዛሬው ዕለት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ወደ ውድድር ሲመለስ በቀዳሚነት የተደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ 1 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
በጨዋታው ቀዳሚ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ፍላጎቶች የታየበት ነበር ።
ነገር ግን በአጋማሹ ድሬደዋ ከተማም ሆነ ወላይታ ድቻ ኳሶችን በእግራቸው ስር ይዘው ለመቆየት ይቸገሩ የነበረ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች ያደረጓቸው ጥረቶችም የተጋጣሚ የኋላ ክፍልን በመፈተን ረገድ ደካማ ነበሩ ።
በጨዋታው የመጀመሪያው የግብ ዕድል በወላይታ ድቻ በኩል የተደረገ ሲሆን በ11ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ፍቅሩ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
- ማሰታውቂያ -
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ የጦና ንቦቹ ተሽለው የታዩ ሲሆን በተለይም በግራ መስመር አቅጣጫ ላይ ሰብረው ለመግባት ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ24ኛው ደቂቃ ላይም ወላይታ ድቻዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ። የቡድኑ የፊት አጥቂ ቢንያም ፍቅሩ ለአበባየሁ ሀጂሶ አቀብሎት በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት ከአበባየሁ የተሻገረለትን ኳስ በድሬዳዋ ከተማ መረብ ላይ አሳርፎታል ።
ከግቡ በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመድረስ ሲሞክሩ በወላይታ ድቻ በኩል የሚገኙ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል በማድረስ ተጨማሪ ግብ ለማከል ሲጥሩ ተስተውሏል ።
በ32ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች በጨዋታው የመጀመሪያ አደገኛ የግብ ዕድልን መፍጠር ችለዋል ።
ቻርለስ ሙሴጌ ከያሬድ ታደሰ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ሆኖ የደረሰውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ ተመልሶበታል ። የተመለሰውን ኳስ ኤልያስ አህመድ በድጋሚ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በ38ኛው ደቂቃ ላይም በአቤል አሰበ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ በተደረገ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ሙከራ በቢንያም ገነቱ ተመልሷል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በትዕግሥት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመግባት ጥረቶች በሚያደርጉበት ወቅት የሚነጠቋቸው ኳሶች በፈጣን ሽግግር ጫና እንዲፈጠርባቸው አድርጓል ።
በተደጋጋሚ በግራ መስመር ጫና ሲፈጥሩ የቆዩት የጦና ንቦቹ በ40ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በቀኝ መስመር በኩል ፀጋዬ ብርሀኑ ወደ ሳጥን ገብቶ ያገኘውን ኳስ ለአበባየሁ ሀጂሶ አቀብሎ አበባየሁ የመታው ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
በ42ኛው ደቂቃ ላይም ፀጋዬ ብርሀኑ ከግራ አቅጣጫ ከዮናታን ኤልያስ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጣሮ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ የግቡን ቋሚ ለትሞ ወጥቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ድሬዳዋ ከተማ ዘርዓይ ገብረስላሴ እና ተመስገን ደረሰን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማጠናከር ሞክረዋል ።
በተወሰነ መልኩም በተሻለ እንቅስቃሴ የጀመሩ ቢመስልም ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ደቂቃዎችን መጠበቅ ነበረባቸው ።
በ49ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዘርዓይ በረጅም የደረሰውን ኳስ ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ ጋር ተገናኝቶ በግንባር ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ መቶ ወጥቷል ።
በ61ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ወደ አቻ የመጣበትን ግብ አስቆጥሯል ። ተቀይሮ የገባው ተመስገን ደረሰ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቆመ ኳስ ያሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል ።
ከግቡ በኋላ የነበሩት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች በሁለቱም በኩል ሁለተኛውን ግብ ቀድመው ለማስቆጠር ፈጣን እንቅስቃሴ አድርገዋል ።
ነገር ግን የሶስተኛው የማጥቃት ዞን ላይ የነበራቸው እንቅስቃሴ ሁለቱንም ቡድኖች የግብ ዕድል ለመፍጠር ያስቻላቸው አልነበረም ።
በ86ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች ምናልባትም የሚቆጩበትን እና አሸናፊ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
አበባየሁ ሀጂሶ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ሲተፋው አግኝቶ ፤ ለግቡ እጅግ በቅርበት የነበረው ብስራት በቀለ ለአብነት ቢያቀብለውም አብነት የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወደ ውጪ ወጥቶል ።
በመጨረሻም ጨዋታው 1 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
በ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ህዳር 27 ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ እንዲሁም ህዳር 30 ቀን ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ።