በይስሐቅ በላይ
ሀትሪክ፡-…ብሩኬ ከአሜሪካ እንኳን ወደ
ሀገርህ በሠላም መጣህ…?
- ማሰታውቂያ -
ብሩክ፡- …እንኳን ደህና ቆያችሁኝ…፤
ሀትሪክ፡- … ቆይ…ቆይ…ከዚያ በፊት…
ግን…አንድ የገረመኝን ነገር ልጠይቅህ…አንድ
ጊዜ መድን ስትጫወቱ የራስ ፀጉር ቅቤ…
ተቀብታችሁ… እንደነበር ሰምቼ ማመን
አልቻልኩም…፤እውነት ተቀብታችሁ ነበር…?
ብሩክ፡- …(በጣም ሳቅ)…ምነው…ግን…
ሰላምታው አይቀድምም…?…እውነት ነው……
ግን መድን እያለሁ ሣይሆን ከኢችንኮም
ከመድንም በፊት የነበረው ወህኒ ቤት (ማረሚያ
ቤት) ለሚባል የመጀመሪያ ክለቤ ስጫወት
የተፈጠረ ነው…(ሳቅ)…በወቅቱ ወህኒ ቤት
ስንጫወት አሰልጣኛችን ጋሼ አብርሃ ይባላሉ፤
ለጨዋታ ስንሄድ “…ወባ እንዳይዛችሁ፤ ቅቤ
ጥሩ ነው…” ተብለን… በሙሉ ተጨዋች
ይሄን ቅቤ አናት አናቱ ላይ ተቀብቶ…ቁጭ
…አለ…(ሳቅ)…በኋላ ላይ አንድ ተጨዋች
ዘግይቶ ይመጣል…፤…ተጨዋቹ ስለ ወባ
ስለተወራ ወባ የነደፈችው መስሎት ይሁን
በሌላ ብቻ አይታወቅም “…ራሴን አመመኝ…”
ይላል…ሁሉም…“…በቃ ወባ ሊሆን ይችላል…
ቅቤ ይቀባ” ይላሉ… ግን ቅቤውን ሁላችንም
ስለተቀባን ቅቤው ከየት ይምጣ…? …(በጣም
ሳቅ)…መጨረሻ ላይ… አማራጭ ሲጠፋ…
እኛ ከተቀባነው ቅቤ ከአናታችን ላይ እንደገና
እየተነቆነጠረ… ያ ተጨዋችም ተለቅልቆት
አረፈው…(በጣም ሳቅ)…እና እውነት ነው
ተቀብተናል ሳይሆን ተለቅልቀነዋል…(በጣም
ሳቅ)…።
ሀትሪክ፡- …የሚገርም ነው ለተጫዋች
ቅቤ…?ብሩኬ…ለማንኛውም…እንኳን…ደህና
መጣህ…?
ብሩክ፡-…እንኳን ደህና ቆያችሁኝ…፤…
ከረዥም ጊዜ በኋላ ስላአገኘኋችሁ እንግዳ
ስላደረጋችሁኝ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከልብም
አመሰግናለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …በእናንተ ዘመን የነበሩ
ተጨዋቾች ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋር በተያያዘ
ትታሙ ነበር…? በተለይ አንተ እንግሊዘኛ
እንደቁምጣ ቢያጥርህም በድፍረት በመናገር
ትታወቅ ነበር… ? ይሄን ታስታውሰዋለህ….?
ብሩክ፡- …በወቅቱ የክለቡ ብቸኛው
የእንግሊዘኛ አስተርጓሚ እኔ ነበርኩሣቅ)…፤…በመድንም በብ/ቡድንም አንድ ነጭ
ወይም እንግሊዘኛ ተናጋሪ ሲመጣ…ሁሉም
ተጨዋች… ብሩክን ጥሩልን ነበር የሚለው…
(በጣም ሣቅ)…፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ የአንተ እንግሊዘኛ
የተሰባበረ… ለአማርኛ የቀረበ ነበር የሚመስለው
ብለው ያሙሃል…? …(ሳቅ)…
ብሩክ፡- …ኧረ ስም አታጥፉ በላቸው…
(ሳቅ)…በወቅቱ ስንቱን ሀገር አሻግሬበታለሁ…
ስንቱን ከፍላጎቱ አገናኝቼያለሁ…(በጣም ሳቅ)…
ስንቱን ተጨዋች ከዳኛ ጋር በቋንቋ ችግር
ሲፋጠጥ ደርሼ የምገላግላቸው መፍትሔ
የምሰጣቸው እኔ ነበርኩ…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ከዚህ ከእንግሊዝኛ ጋር በተያያዘ
አንድ ጊዜ… ለብሔራዊ ቡድን ስትጫወቱ…
ተጨዋቹ ፋውል አልሠራም፤ አልመታውም”…
ለማለት ብለህ “…ሪፌሪ…ኖ…ከት…ኖ…ከት…”
ብለህ ዳኛውንም ተጨዋቾቹንም… አስቀሃቸዋል
አሉ…?…(ሳቅ)…
ብሩክ፡- …(በጣም ሳቅ) … ይሄ ነገር
ምን መሰለህ… አንተ በጥያቄህ እንዳነሳኸው…
ለብሔራዊ ቡድን ስጫወት ሣይሆን…
መድን እያለሁ የተፈጠረ ነው…፤… ሳቅ….
መድን ከሩዋንዳው ራዬን ክለብ ጋር ኪጋሊ
ላይ እንጫወታለን፡፡ …ያኔ ሩዋንዳ ቱትሲና
ሁቱ በሚባሉ ጎሣዎች በጣም በከፋ የእርስ
በእርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች፤ መጀመሪያ
ልንጫወትበት የነበረው ስታዲየም በእርስ በእርስ
ጦርነቱ በተፈናቀሉ በተጎዱ ዜጎች መሞላት ብቻ
ሣይሆን ደም በደም በመሆኑ ጨዋታው ወደ
ሌላ አነስተኛ ስታዲየም እንዲዛወር ተደረገ፡፡ ያ
ስታዲየም በወታደር ተከቧል… የስታዲየሙ
ብቻ ሣይሆን የሀገሪቱ ድባብ በጣም ያስፈራ
ነበር፤ ዳኛውም ነገሮች በጣም እንዳስፈሩት
ፊቱ ብቻ ሣይሆን ውሳኔውም ያስታውቅበታል፤
ውሳኔዎቹ ሁሉ ለእነሱ ነበር፡፡ በኋላ አንድ
ኳስ ላይ ዳንኤል (ማቻ) አንድ ተጨዋች ላይ
ፔናሊቲ ቦክስ ውስጥ አደገኛ ፋውል (ታክል)
ሠርቷል በሚል ፔናሊቲ (የፍፁም ቅጣት
ምት)ይሰጥብናል፤ በኋላ እኔም ሐሰንም
በላያም ሮጠን ዳኛውን ከበብነው… ግን ማን
ያውራው…(ሳቅ)…በላያም…ሐሰንም በአማርኛ
ቢያወሩት ሊግባቡ አልቻሉም…በኋላ እኔ
አይደለሁም የክለቡ የእንግሊዝኛ ሊቅ… (ሳቅ)…
በፍፁም አልመታውም፣ አልነካውም ለማለት ልኩት…በጣም…ሳቅ…ከዚያ ወዲያውኑ በላያ
መሃል ገባችና “…ኧረ…ብሩክ…ጉድ አደረከን…
እንደዚህ አይደለም የሚባለው ተሳስተሃል…”
ሲለኝ…እንዴ በላያ… ምን ማለትህ ነው…
ዳኛው ስለገባውና…ትክክል ስለሆንኩ እኮ
ነው…“…የስ…ከት…የስ…ከት…” …ያለው …
(በጣም ሳቅ)… ያልኩት ትዝ ይለኛል፡፡ …
የሚገርምህ… ፔናሊቲውም ገባ… በአጠቃላይ
3ለ0 በሆነ ውጤት…ተሸንፈን ወጣን…፡፡
ሀትሪክ፡- …በዕለቱ ጨዋታ… በተለይ
የሐሰን በሽር ከቁጥጥር ውጪ መሆን…
ብዙዎችን አስገርሞ ነበር… ትዝ ይልሃል…?
ብሩክ፡- … (ሳቅ)… ኧረ የሀሰን በሽርን ነገር
አታንሳው… አሁንም ሳቅ…ሀሰንን እንደዛን ቀን
ሆኖ በጣም ተበሳጭቶ አይቼው አላውቅም፤…
በጣም ከመበሳጨቱ የተነሣ… ማልያውን
አውልቆ… ራቁቱን ሆኖ ወደ ዳኛው ሮጦ
ካልገደልኩት ሲል…ኧረ ሀሰን ምን ነካህ…? …
ትቀጣለህ…ሊያግዱህ ይችላሉ ስለው… “ባክህ
ተወኝ ማልያዬን ስላወለኩ የእነሱ ተጨዋች
ነው የምመስላቸው አይለዩኝም”…(ሳቅ) ብሎ
የዳኛውን ብስጭት አስረስቶን አስቆናል፡፡…
የሚገርምህ ጨዋታው ካለቀ በኋላም የሀሰን
ብስጭት አልበረደለትም ነበር… ላረጋጋው ብዬ
አይዞህ ሀሰን 3ለ0 ቢያሸንፉንም አዲስ አበባ ላይ
10ለ0 እናሸንፋቸዋለን ስለው… “…አንተ ደግሞ
በጣም ቀልደኛ ነህ… ባስኬት ቦል አደረከው
እንዴ…? ብሎ አስቆኛል፡፡ …የሚገርምህ አዲስ
አበባ ላይ የመልሱን ጨዋታ ስናደርግ እኛም
በተመሳሳይ 3ለ0 ብናሸንፋቸውም… ለሪጎሬ
ደርሰን… እነሱ በመለያ ምት አሸንፈው እኛ
ወደቅን…፡፡
ሀትሪክ፡- …ስለ ሀሰን በሽር ካነሣን
ሀሰን በክለቡ ከድንቅ ችሎታው በተጨማሪ
በጣም በዝምተኛነቱም ነው ተለይቶ
የሚታወቀው…፤…የሐሰን ድምፅ ለመጀመሪያ
ጊዜ በክለቡ የተሰማው… “…ፓስታው… ስጎ
አንሶታል…” ብሎ የተናገረ ጊዜ ነው እንጂ…
ከዚያ በፊት አንድም ቃል ተንፍሶ አያውቅም…
ሲባል ሰማሁ እውነት ነው… ?
ብሩክ፡- … (በጣም ሳቅ)… አይደለም…
ሀሰን ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ምን እንደሆነ
ልንገርህ…?…. (አሁንም ሳቅ)… ትሬይኒንግ
ላይ መሃል በገባ ሁሌ ስንጫወት… እኔና
በላያ ያለንበት ቡድን ሁልጌዜ ጭቅጭቅ
አይጠፋውም…፤…አንድ ነገር ሲፈጠር
ሁለታችንም በአባታችን ስም እየማልን
በጣም እንጨቃጨቃለን፤ እኔ “…እስጢፋኖስ
ይሙት…” ስል… እሱ ደግሞ… “…አስቻለው
ይሙት…” እያለ ለገላጋይ የሚያስቸግር
ጭቅጭቅ እንጨቃጨቃለን፤ አንድም ቀን
ተማምነን ወይም ተስማምተን አናውቅም…፡
፡ …ታዲያ አንድ ጊዜ እንዲሁ መሀል በገባ
ስንጫወት ሀሰንን ጠራሁትና… ና… እኛ ጋር
ግባ ስለው… “… አይ … አይ…. ይቅርብኝ…
የአስቻለውና የእስጢፋኖስ ፍርድ ቤት
አልገባም…” …(በጣም የማያቋርጥ ሣቅ)…
ብሎ የተናገረውን ነው የማስታውሰው፤ …
በጣም የሚገርምህ… ሀሰን… ከዝምተኝነቱ
አንፃር… በዚህ ደረጃ መናገሩ…ሁላችንንም
አስገርሞናል…፡፡
ሀትሪክ፡-…ሌላው…ከላይ እንዳነሳነው …
ሀሰን…በጣም ዝምተኛና የማይናገር ተጨዋች
ከመሆኑ አንፃር…ጋዜጠኛ ኢንተርቪው
የሚያደርገው… በአንተ አስተርጓሚነት ነው
ይባላል…. እውነት ነው…?
ብሩክ፡- …(በጣም ሳቅ)…የሚገርምህ እኮ…
እኔ እንግሊዘኛ ብቻ ሣይሆን አማርኛንም ወደ
አማርኛ በማስተርጎምም ነበር የምታወቀው…
(ሳቅ)…እንዳልከው… ሀሰን ዝምተኛ ስለሆነ…
ለኢንተርቪው ብዙም አይመችም ነበር…፤…
እንደምንም አግባብተነው ኢንተርቪው ከሰጠ…
ጋዜጠኛው በአንድ በኩል እኔና ተክሌ ከእሱ
አጠገብ ሆነን ነው የሚያነጋግሩት፡፡ …በጣም
የሚገርምህ ጋዜጠኛው ጥያቄ ይጠይቀዋል…
ሀሰን መልስ ሲሰጥ…ለአንድ ሰከንድም ቢሆን
ፊቱን ወደ ጋዜጠኛው አዙሮ አያየውም እኔን
እኔን እያየ ነው የሚመልሰው…(ሳቅ)… ከዚያ
እሱ የመለሰውን… እኔ ለጋዜጠኛው ጮክ
ብዬ እነግርለታለሁ… (ሳቅ)… በአጭሩ
አማርኛን ወደ አማርኛ ማስተርጎም ብቻ
ሣይሆን… የሀሰን በሽር ስፒከርም… በመሆን
አ ገ ል ግ ያ ለ ሁ …(ሳቅ)…
ሀትሪክ ፡-ብሩክ (ካንቶና) የሚለውን ስም
ያ ስ ተ ዋ ወ ቀ ው መድን ነው…የመድንን
ማልያ ለስንት አመት ለብሰህ
ተጫወትክ?
ብሩክ፡- የመድን ማልያን ለድፍን ስምንት አመት ለብሼ ተጫውቻለሁ፤ የእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ትልቁ ታሪክምበዋናነነት ያለው መድን ውስጥ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ መድን በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት
ጉልህ ሚና ያለው ክለብ ነው፤ በኢንተርናሽናል የውድደር
መድረክ ረዥም ጉዞ በመጓዝ ታሪክ የፃፈ በሀገር ውስጥም
ማራኪ በሆነው አጨዋወቱ “አርጀንቲናዊው መድን”
የሚል ስምም የተሰጠውም ክለብ ነው፡፡ ቡድኑ
በውጤት ብቻ አይደለም የሚታወቀው በድንቅ
የጨዋታ እንቅስቃሴውም ጭምር ነው፡፡ በየአመቱ
በደረጃ ከ1-3 ቢበዛ 4ኛ ድረስ ነበር የምወጣው፡፡ በክለቡ የ8 አመት ቆይታዬ የሊጉን ዋንጫ ባላነሣም እስከወጣሁበት
ጥልዬ እስካሰለጠነበት ጊዜ የጥሎ ማለፍ
ዋንጫዎችን አግኝቻለሁ፤በክለቡም የማይዘነጋ
ታሪክም አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-በወቅቱ የነበረው ስብስብ በጣም
ምርጥና አስፈሪ የሚባል ነበር እስቲ እሱን
አስታውሰኝ…?
ብሩክ፡- በወቅቱ የነበረው ስብስብ በጣም
ልዩ ነቡር፤ እናዳልከውም ምርጥም አስፈሪም
ነበር፡፡ ወደ ሶስትና አራት ዓመታት ኮከብ
ቡድን ነበር፤ ሀሰን በሽር ፣በላያ፣ ጉልማ፣
ተክሌ ከየትኛውም ቦታ የማስቆጠር አቅም
ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው፡፡ መሀል ላይ
ስትመጣ እንድሪያስ ሙሉ ሜዳ የማይበቃው
ሁልጊዜም ጭንቅላቱን እንጂ ፊዚካሉን አስርቶ
የማያውቅ ተጨዋች ነው፤ ቴዎድሮስ ቀነኒ
ልዩ ነው፣ ዘውዴ ክንፍ ላይ ተአምረኛ ነው፤
ተከላካይ ላይ ባሳዝን ተጨምሪ አማካይ ሆኖ
ነው የሚያገለግልህ ወልደ አማኑ ኤል፣ ፔሌ፣
ዳንኤል (ማቻ)፣ ዳንኤል አሰግዶም ብቻ ምርጥ ምርጥ
ልጆች የነበሩበት ነበር። የሚገርምህ
በጭቃ ጨዋታ እኔና
ዳንኤል (ማቻ) ፊታችንን
ሣይቀር ሸፍኖን ዳ ን ኤ ል
አሰግዶም ግን ካ ሶ ተ ኒ ው
( ካ ል ሲ ው ) ት ን ሽ እ ን ኳ ን
ጭ ቃ ሣ ይ ነ ካ ው
የ ሚ ወ ጣ ተጨዋች ነበር፡፡ በአጠቃላይ
ክስተት በሆኑ ተጨዋቹ የተገነባቡድን መሆኑ መድንን የተለየ አድርጎታል፡፡
ሀትሪክ፡- መድን ለተጨዋቾቹ ካለው
አሳቢነት በሌሎች ክለቦች በተለየ የቋንቋ
ትምህርት ሁሉ እንድትማሩ አድርጎ ነበር…. ?
ብሩክ፡- በወቅቱ የነበረው የመድን አመራር
ያላደረገው ነገር የለም፤ የሚገርምህ በወቅቱ
ለተጨዋቾች በካምፕ ውስጥ ዲሽ (ጨዋታ
ለመከታተል)ያስገባ የመጀመሪያው ክለብ ነው፡
፡ የካምፕ ህይወታችን እንዳያሰለቸን ከእግር
ኳስ ሜዳው በተጨማሪ የቅርጫትና የሜዳ
ቴኒስ ሜዳ የሰራ ክለብም ነው፡፡ አንተ ይሄን
ትላለህ ለእኔ በየቀኑ ስድሰት ብር በወር 180
ብር አካባቢ ተመድቦልኝ ሳሪስ ከሚገኝ ቪዲዮ
ቤት በየቀኑ የፊልም ካሴት እያመጣሁ ከኳስ
በኋላ ፊልም እያየን እንድንዝናና ይደረግ ነበር፡
፡ በዚህ ሳይበቃ አንድ ጊዜ እኔ ትምህርት
መማር እፈልጋለሁ አልኩና ኮሚቴውን ቋንቋ
ትምህርት ቤት ልግባ አልኳቸው፤ በጣም
ገረማቸው ኮሚቴው ለተጨዋቾች አሳቢ ስለሆኑ
አይደለም የቋንቋ ት/ቤት እስከ ዩኒቨርስቲ
ድረስ መማር ከፈለክ መድን ይከፍልሃል
ተመዝገብ አሉኝ፤ በእኔ ተነሳሽነት ሁሉም
የክለቡ ተጨዋቾች ቋንቋ እንዲማሩ ተደረገ፡፡
ያኔ የምንማረው መጀመሪያ ፒያሳ ነበር እሱ
ሲርቀን ስታዲየም አካባቢ ገባን፡፡ የሚገርምህ
ክለቡ የት/ቤት መክፈል ብቻ ሣይሆን ሰርቪስ
መድቦ ት/ቤት ያደርሱን ይመልሱን ነበር፡፡
ኮሚቴው ለተጨዋቹ የሚያስብ የተሻለ ህይወት
እንዲኖራቸው በጣም የሚተጋ ኮሚቴ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-… ግን ምን ዋጋ አለው በህዝብ
ስልክ የሴት ጓደኞቻችሁን ሳይቀር በመቅጠር
ከመማር ይልቅ ትፎርፉ ነበር በሚልም ትወቀሱ
ነበር….?
ብሩክ ፡-… ( ሳ ቅ )… ል ጅ ነ ት ፣ አ ለማ ወ ቅ
እንደነበረብን አልድም፤ ብዙውን ጊዜ ካምፕ
ስለምንውል ጓደኞቻችን፣ የሠፈር ልጆች
ይናፍቁን ስለነበር ልክ ሰርቪሱ ት/ቤት
እንዳወረደን ደብተራችንን ጀርባችን ውስጥ
ሽጉጠን በየአቅጣጫው እንበር ነበር፤ የሰርቪሱን
መምጫ ሰዓት ስለምናውቅ ልክ በሰዓቱ
ጀርባችን ውስጥ ያለውን ደብተር አውጥተን
እንደተማረ ሰው በሰርቪስ እንመለስ ነበር፡፡
አንድ ጊዜ ልማር ብዬ ክላስ ስገባ አስተማሪው
“ምነው ዛሬ መሄጃ የለህም እንዴ?… እንዴት
መጣህ?” ሁሉ ብሎኛል”፡ ክለቡ ብዙ ርቀት
ሄዷል ለፍቷል እኛ ግን ካለመብሰል ከልጅነት
በመነጨ ስህተት ስንፈፅም ነበር፡፡ አንተ የቋንቋ
ትምህርቱን ትላለህ ጨዋታ በሌለን ጊዜ ክለቡ
ገንዘብ ከፍሎ ስታዲየም አስገብቶን እኛ የገባን
መስለን በሌላ በር እንወጣ ነበር፡፡ ይሄ ያው
እንዳልኩህ ብስለት፣ አለማወቅ ያመጣው ችግር
ነው፤ ሲያልፍ ነው የሚሰማህና የሚቆጭህ፡፡
ሀትሪክ፡- መድንን ውጤታማ ያደረገው
ከስብስቡ በላይ በመከላከላችሁ ያለው ፍቅር
እንደሆነ አውቃለሁ…፤…እስቲ ይሄንን
ከአንደበትህ ልስማው…?
ብሩክ፡- …እሱ ፍፁም የተለየ ነው…፤
የሚገርምህ ቴዎድሮስ ቀነኒ ድፎ ዳቦ አስደፍቶ
ያመጣል… ክፍሉ ውስጥ ሻማ አብርተን ዳቦ
ይቆረሣል፣ ይዘመራል፣ ይፀለያል፣ የተጣላ
ይታረቃል፡፡ ከሰኞ እስከ ሰኞ ደግሞ ከካምፓችን
ፊት ለፊት ገብርኤል ቤተክርስቲያን አለ
የእስልምና እምነት ተከታዩ ሀሰን በሽር ሣይቀር
ገብርኤል ሄዶ ከእኛ ጋር ይማራል፣ ስብከት ሁሉ
ይሰማል፤እስከዚህ ነበር ፍቅራችን።በአካባቢው
ሰዎች በተለይ በእናቶች ስለምንወደድ እናቶች
ይፀልዩልናል፡፡ የሚገርምህ ነገር የአካባቢው
ሰው ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያውቁ የአካባቢው
ወጣቶች ጠላ ቤትና ምግብ ቤት ሣይቀር እየገቡ
ብሩክና በላያ ነን እያሉ ሳይከፍሉ በስማችን
እየበሉ እየጠጡ ስንት እዳ ውስጥ ከተውናል፤
የሚገርም ፍቅርና አንድነት ነው የነበረን፡፡ ያ
ይመስለኛል በሜዳ ላይም የጠቀመን፡፡
ሀትሪክ፡- ከተክሌ ጋር ተጣልታችሁ
“ፕሌኑ ይገለበጣል ታረቁ” በሚል ስለተፈጠረው
ነገርስ.. ታስታውሳለህ…?
ብሩክ፡- …(በጣም ሳቅ)… እኔና ተክሌ ወደ
መቀሌ ለጨዋታ ልንሄድ ስንል በሆነ ነገር ፀብ
ይፈጠራል፤ በፊት በጣም የምንዋደድ ሰዎች
ነበርን፡፡ የዚያን ቀን ሁለታችንም ጋ ትዕግስት
ይጠፋና እንጣላለን፤ ፀባችን ደግሞ እንዲህ
ቀላል መሰለህ…? እንደ በሬ በአናት (በቴስታ)
ነበር…፤…በቃ ግንባር ለግንባር ተለጣለጥን፡
፡ ከዚያ ለጨዋታ ልንሄድ ስንል እኔ አኩርፌ
አልሄድም አልኩኝ፤ ካምፑ ታመሰ፤ በስንት
መከራ ለምነውኝ ሃሳቤን ቀይሬ ሰርቪስ ውስጥ
ገባሁ፡፡ በፊት በሰርቪስ ስንሄድ ከተክሌ ጋር
አብረን ተቀምጠን ነበር የምንሄደው፡፡ የዚያን
ቀን እኔ ፊት ተክሌ መጨረሻ ተቀምጦ
ሰርቪሱ መሄድ ጀመረ፡፡ ያኔ ሹፌራችን ኃይሉ
(ጮራ) ነበር፡፡ እሱ እየረገጠ እየነዳው ሲሄድ
ቴዎድሮስ ቀነኒ ድንገት ተነሳችና… ሹፌሩን…
“…አንዴ አቁመው…፤..አንዴ አቁመው…”
ብሎ በመሃከላችን የነበረውን ዝምታ በጩኸት
ሰበረው፡፡ ሾፌሩ ምን ተፈጠረ ብሎ ሲያቆም
ቴድሮስ ቀነኒ በጣም እያለቀሰ “እናንተ
ተጣልታችሁ…እንዴት… ልንሄድ … ነው…?
…ፕሌኑን…ልታስገለብጡት…ልትጨርሱን…
ነው…?” ብሎ እዬዬ አለ…“በቃ ተነሱ ተቃቀፉ
ይቅርታ ተባባሉ…” አሉን ከተክሌ ጋር
ተቃቀፍን፣ ይቅርታ ተባብለን ልክ እንደበፊቱ
አብረን ተቀምጠን ሄደናል… (በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡-በዚህ ደረጃ የተወራለት ቡድን
ወርዶ ከክብሩና ከደረጃው ዝቅ ብሎ መጫወቱን
ስታይ… ምን ተሠማህ…?
ብሩክ፡- መድን መውረድን ስሰማ በጣም
ነው የደነገጥኩት፤ ልክ እኔነቴን ያጣሁ ያህል
ነው የተሰማኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ፋትቦል የሚጠቅም
ስራ ከሠሩት ክለቦች መድን አንዱ ነበር፤
አልፓና መድን ናቸው በወቅቱ ታዳጊዎችን
ላይ ደፍሮ በማሳደግ በውጤትም በጨዋታም
የተሻለ ነገር የነበራቸው፤ በዚህ ደረጃ የነበረ
ቡድን ጭራሽ ወረደ ሲባል ያማል፡፡ በእኛም ጊዜ
የተለያዩ ተጨዋቾች አሰልጣኞች ተቀያይረዋል፡
፡ መድን ግን መድንነቱን ነው ይዞ የቀጠለው፡
፡ ከእኛ በኋላም መድንን የተለያዩ ጥሩ ጥሩ
አሰልጣኞች አሰልጥነውታል ግን ምንም ለውጥ
ሊመጣ አልቻለም፡ እኔ ለመደን መውረድ ከሜዳ
ላይ ጨዋታ በፊት ያለው ነገር ነው ችግሩ ብዬ
አስባለሁ፡፡
ራሱ ውስጡን አሣምኖ “እኔ የመድን ነኝ
የሚል ፕሪንስፕል ያለው ተጨዋች አለመገኘቱ
ይመስለኛል ችግሩ፡፡ ቡደኑ ወረደ እንጂ አይቼ
ብናገር ይበልጥ ደስ ይለኝ ነበር ፡፡
ሀትሪክ፡- … በአሁን ዘመን
ለአንድ ተጨዋች ከ250 ሺህ ብር በላይ ደሞዝ ይከፈላል፤
በእግር ኳስ ያገኘኸው የመጀመሪያ ትልቁ
ደሞዝህ ስንት ነበር…ታስታውሰዋለህ… ?
ብሩክ፡- …መድን
ከመግባቴ በፊት…ኢችንኮ እያለሁ
የ ማ ገ ኛ ት …ጫማ እንኳን…
ለመግዛት አቅም የ ሚ ያ ን ሳ ት …200… ብር ብቻ
ነበረች… (ሳቅ)…
ሀትሪክ ፡- …መድን ስትገባስ….?
ብሩክ፡- …መድን ስገባማ
የሚያስደነግጥ ብር ነበር በደሞዝ መልክ
የተስማማሁት… በወር 500 ብር፤…
ይሄ ብር በወቅቱ ጉድ አስብሏል…፤…
ምክንያቱም ምን መሰለህ… እኔ
መድን የገባሁት ከእነ አሰግድ፣ ፉአድ
አብድልቃድርና ካሳዬ አራጌ ጋር
ነበር፡፡ እነሱ ከትልልቅ ክለብ ነው
የመጡት፤ ካሳዬ ከኪራይ ቤቶችት
እነ አሰግድ ከጊዮርጊስ ስለመጡ
ለዚያ ተብሎ የክለቡ ትልቅ ክፍያ
500 ብር ደሞዝ ይከፈላቸው ተባለ፡
፡ እኔ እንደ እነሱ ስም ካለው
ትልቅ ክለብ ስላልመጣሁ በወቅቱ
የቡደኑ አሠልጣኝ የነበሩት ጋሽ
ሐጎስ(ነፍሳቸውን ይማረውና) “…
አንተስ ስንት ይከፈልህ…?” ሲሉኝ
…ኧረ ጋሼ እኔ አላውቅም…፤
…እርስዎ ይበቃሃል ያሉትን…”
ስላቸው “…አንተ እኔ የምልህን
ከሠማህ… ወደፊት ከእነሱ
በላይ ታገኛለህ…፤…ለአሁኑ
ግን… ከእነሱ እኩል 500
ብር ይከፈልሃል…” ሲሉኝ
…የሰማሁበትን ጆሮዬን
ተጠራጥሬ… ምን አሉኝ…?
…ለእኔ 500 ብር…?
ስላቸው… “…አዎን ከእነሱ
እኩል… 500 ብር…”
ሲሉኝ… በደስታ ከመስከሬ
የተነሣ… ሠፈሬ ኳስ ሜዳ
ነው፤ እኔ ግን በደስታ ሰክሬ
ሠፈሬን ትቼ ወደ አዋሬ
የነካሁበትን ጊዜ አልረሣውም…
(ያልተቋረጠ ሳቅ)… የእኛ ጊዜ ምን ያህል
የምስኪኖች ጊዜ እንደሆነ ይሄ ያሳይሃል…
(ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ከመድን ወጥተህ ኢት…
ቡና ገብተህ ነበር እስቲ አገባብህ እንዴት
እንደነበር መለስ ብለህ አጫውተኝ…?
ብሩክ፡- …ቡና የገባሁት የካሳዬ
ፋልስፍና በተጀመረበት 1994 አካባቢ ነው፤
ኩኩሻ ከቡና ወጥቶ መድን ሲገባ እኔን ከኋላ
ኳስ አይጠልዝም ያስጀምረናል ብለው እኔን
ደግሞ ከመድን ወደ ቡና ያዛውሩኛል፡፡ በወቅቱ
እኔ ብቻ ሣልሆን ለዚህ አጨዋወት ይጠቅማሉ
በሚል አንዋር ያሲን (ትልቁ) በለጠ ወዳጆም
መጥተው ነበር፡፡ የካሳዬ ፍልስፍና አዲስ
ስለነበረ በወቅቱ ብዙ ተወራ፤ ከባንክ ጋር በ8
ሰዓቱ ጠራራ ፀሐይ የመጀመሪያ ጨዋታ
አደረግን፡፡ እኛ እንጫወታለን እነሱ
እየወሰዱ ያገቡብናል፤መሃል
ላይ አንዋር፣ ቴዎድሮስ(ቦካንዴ) ከፊት አሰግድ
ገ/ኪዳን (ጋምብሬ) ከኋላ በለጠ እኔ አለን
ኳሱ በጣም ቀሎን ነበር
የምንጫወተው፤ ተመልካቹ ግን የእኛን
ተስፋ ሰጪ የሚያድግ ጨዋታ ሳይሆን
የሚገባብንን ግብ ነበር የሚቆጥረው፤ በዚህ
ተቃውሞ ቀረበብን፡፡ በመሃል የኩኩሻን
መመለስ በጣም የሚፈልግ ግሩፕ ነበር በተለያየ
መንገድ በሚዲያም ወቀሳ ይቀርብ ስለነበር እኔ
ላይ ተቃውሞ እየጠነከረ መጣ፡፡ ገና ወደ ሜዳ
ስገባ እኔን በመጥላት ሳይሆን ኩኩሻ እንዲመለስ
በመፈለግ “ኩኩሻ ይመለስ እያሉ” መጮህ
ጀመሩ፡፡ ይሄ ደግሞ እኔ አቅሜን አውጥቼበነፃነት እንዳልጫወት አደረገኝ፤ በእረፍት ወጣሁ፡
፡ ከዚያ የተወሰነ ጊዜ ትሬይኒንግ እየሠራሁ ቆየሁ፤
በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስላልቻልኩ ለመልቀቅ
ወሰንኩ፡፡ የተጨዋች የዝውውር ጊዜ ስለተጠናቀቀ
ወርጄ መጫወት ነበረብኝ፤ከእነ ሳሞሶን (ጆሮ) እና
ሲሳይ ጋር ሰሚት የተወሰነ ጊዜ ተጫወትኩና ወደ
ሙገር ሄድኩ በኋላ መድን ተመለስኩ፡፡ በጠቅላላ
በቡና የነበረኝ ጊዜ አጭር ነው፤ አመት እንኳን
አልሞላኝም፡፡
ሀትሪክ፡-በቡና በተለይ ምን የምታስታውሰው
ነገር አለ…?
ብሩክ፡- …ምን ትውስታ አለኝ ብለህ ነው፤..
የማስታውሰው እኔ ቡና እያለሁ ሰርቪሱ መገልበጡን
ነው የማስታውሰው… (በጣም ሳቅ)… እኔ ቡና ስገባ
ተገልብጦ አይደለም ተጋጭቶ የማያውቀው ሰርቪስ
ተገልብጦ አልቀን ነበር… (በጣም ሳቅ)… ይሄንን
አስታውሳለሁ… (አሁንም ሣቅ)…
ሀትሪክ፡- …የሰርቪሱ መገልበጥን ስታነሳ…
እኔም አንድ ነገር ትዝ አለኝ…(ሳቅ)…ከቡና
ወጥተህ ሙገርም ስትገባ በተመሳሳይ…የሙገርም
ሰርቪስም ተገልብጧል አይደል…?…በየሄድክበት
የሰርቪስ መገልበጡን የታዘቡ… እኛም ጋ መጥቶ
ሰርቪሳችንን ያስገለብጥብናል ብለው እስከመፍራት
ደርሰው ነበር ይባላል…?
ብሩክ፡- … (የማያበራ ረዥም ሳቅ)… አንተ
ጉደኛ ሰው… ነህ…? … ይሄንን ሁሉ ምስጢር
በውስጥህ ይዘህ ታስለፈልኛለህ…?(በጣም ሳቅ)…
ትንሽ አጋነንከው እንጂ ነገሩ ልክ ነህ…ግጥጥሞሹም
ይገርማል…፤…እንዳልከው ሙገርም ስገባ የክለቡ
ሰርቪስ ተገልብጦ በተሰበረው መስታወትና በቱቦ
ውስጥ ወጥተን ነው የተረፍነው፤ …በኋላ ምን
ብለው ተረቡኝ መሰለህ… (በጣም ሳቅ)…“ብሩክን
ማስፈረም ከባድ ነው… እሱ የገባበት ክለብ ሰርቪሱ
ይገለበጣል…ብለው አወሩብኝ፡፡ አንዳንዶቹ እናንተ
ጋር ልገባ ነው ስላቸው “…አረ ልታስጨርሰን…?˝
በማለት ሙድ እስከመያዝ ደርሰውብኝ ነበር፡፡ ነገሩ
መገጣጠሙ ዛሬም ድረስ ይገርመኛል፡፡ ችግሩ ግን
የእኔ አልነበረም የሾፌሮቹና ድንገተኛ አጋጣሚ
ነው… (ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …መድን እያለህ ከቡና ጋር
ስትጫወቱም ደጋፊው ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦብህ
ራስህን መቆጣጠር ሁሉ አቅቶህ ነበር…፤ ያን
አጋጣሚ መለስብለህ አስታውሰኝ እስቲ?
ብሩክ፡- …ነፈሱን ይማረውና አሰግድ ተስፋዬ
በጣም ጓደኛዬ ነው እንግባባለን…፤…በወቅቱ
ደግሞ ጨዋታችን ከእነሱ ጋር ነው፡፡ ከጨዋታው
በፊት ከእሱ ጋር ተደዋውለን ነበር፤ ሜዳ ላይ
ስንገባ ወጥሬ አላንቀሳቀስ አልኩት፡፡ ምክንያቱም
ጨዋታው ለሁለታችንም ወሳኝ ስለነበር አሰግድ
መያዝ ነበረበት፡፡ ምንም የመጫወቻ ስፔስ (ቦታ) እንዳያገኝ እላዩ ላይ ተለጠፍኩበት፡፡ ቦታ
ሲቀየር እኔም እየተከተልኩ እቀይራለሁ፡፡ ይሄን
የማደረገው ወድጄ አይደለም አሰግድ እንዳይዞር
ቦታ እንዳያገኝ ነው፡፡ አሰግድ ቦታ ካገኘና ከዞረ
አለቀልህ በቃ ያጠፋሃል፡፡ ብቻ አላንቀሳቅስ
አልኩት አሰግድ ያልጠበቀው ነገር ስለሆነበት
ነው መሰል በጣም ይናደድና ዞር ብሎ “ምን
ነካህ?” ይለኛል፤… ምን አልክ…? ምን ነካህ?
ነው ያለከው…? ትንሽ ለቀቅ አደረኩህ መሰል
ስለው ይበልጥ በጣም ይናደድና “…ኧረ በእህትና
ልጫወትበት፤ ሰው ሌላ ይመስለዋል…” ሲለኝ
ዝም ብለህ ተጫወት ስለው ራሱን መቆጣጠር
አቅቶት ፋውል ይሰራል… ወዲዲው ዳኛው
መጥቶ ቀይ ካርድ ይሰጠዋል፤ይወጣል፡፡ ከዚያ
በኋላ ሁሉም ነገር ይደበላለቃል፤ ደጋፊው
ያብዳል… የስድብ ናዳ ያወርድብኛል…እኔም
የእነሱን ስድብ መቋቋም አቅቶኝ በቀኝ ጥላ
ፎቅ በኩል ለመደባደብ ስሄድ ወላጅ አባቴ
መሃል ቁጭ ብሎ አየሁት…(በጣም ሳቅ)…
በጣም ደነገጥኩና… ሳልጣላ ወደ ውስጥ ገባሁ፡
፡ ወደ ካምፕ ለመሄድ ሰርቪስ ልንይዝ ስንል
ሰርቪሱ በቡና ደጋፊ ተወሯል… ይሰድቡናል…
ይጮሃሉ… በጣም ስሜታዊ ሆነዋል…
በመጨረሻ በፖሊስ በመከራ ተበትነው ወጣን…
ከዚህ በኋላ የሚገርምህ በነጋታው…
ሀትሪክ፡- …በነጋታው …ምን ተፈጠረ…
ደግሞ… ?
ብሩክ፡- …በነጋታው እኔና አሰግድ
ጓደኛማቾች ነን ብየሃለሁ… ሁሉም ነገር
ሜዳ ውስጥ አልቋል ብለን ነው የምናስበውና
ተቀጣጥረን ተገናኘን፡፡ አብረን እየሄድን
እያለን የቡና ደጋፊዎች አንድ ላይ ሲያዩን
አላመኑም፤በጣምም ተናደዱ፣ ጮሁብን በኃላ
ምን ቢሆን ጥሩ ነው እኔን ትተው አሰግድን
“…አንተ ትናንት እንደዛ አድርጎህ… እንዴት
ከዚህ ጋር ትሄዳለህ…?” …ብለው በእኔ ጦስ
እሱንም ሊመቱት የነበረው ጊዜ አይረሳኝም….
(በጣም ሳቅ)…፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን ደግሞ ስለ አሸናፊ
በጋሻው እናንሳ…፤ ቡና እያላችሁ ከታኬታ
(የመጫወቻ ጫማ) ጋር የተያያዘ አንድ ነገር
አለ… እሱን አጫውተኝ እስቲ…?
ብሩክ፡- … ባጣም ሳቅ…ምን ሆነ መሰለህ…
ያው በእኛ ጊዜ ካምፕ አለ እዛ ነው የምንውለው
የምናደረው፤ ለድብርት በሚል ካርታ ምናምን
እየተጫወትክ ነው የምታመሸው፤ ታዲያ
አንድ ጊዜ አሹ እጅ ያጥራትና ታኬታዋን
በ500 ብር ጆሮውን ትለውና በዚያ ብር
ካርታ ትጫወታለች…(ሳቅ)… በአምስት ደቂቃ
ውስጥ አንዴም ሳትበላ 500 ብሯን እምሽክ
ያደርጓታል፡፡ በዚህም በጣም ተናደደች አበደች
ራሱን ሁሉ መቆጣጠር አቃተው፡፡ ከዚያ ታኬታ
ሸጦ 500 ብሩን መበላቱን እንዳይታወቅበት
ሁሉም ተጨዋች በተሰበበትበጣም እየጮኸ “…
ታኬታ ያየ ሰው አለ…?…ወይኔ ታኬታዬ..
ታኬታዬ.. ጠፋ …ተባለሁ… እያለ ካምፑን
ቀውጢ አደረገው…(በጣም ሳቅ)…ሀሉም
ደንግጦ ምን ተፈጠረ? ሲሉት ታኬታውን ሸጦ
እንዳይጠየቅና ሌላ እንዲሰጠው የዘየደው ዘዴ
ዛሬም ድረስ ያስቀኛል አይረሳኝድ…፤…ያላባራ
ሳቅ…
ሀትሪክ፡- …ከሀገር ውስጥ የምታደንቀው
አሰልጣኝ ማነው?…ብልህ…መጀመሪያ
የምትጠራው ማንነው…?
ብሩክ፡- …ብዙ አሰልጣኞች
አሰልጥነውኛል…፤… ጋሽ ሐጎስን ብትወስድ
የሚገርሙ ትልቅ አሰልጣኝ ነበሩ፤ ወርቁ
ደርገባም ለስልጠና የተፈጠረ ሰው ነው፤
ለእነዚህና ላሰለጠኑኝ በሙሉ ትልቅ ክብር
ቢኖረኝም ለኢንስትራክተር ካሳሁን ተካና
ለአሠልጣኝ ገዛኸኝ ማንያዘዋል በጣም ትልቅ
ቦታ አለኝ፡፡ የእነዚህ አሰልጣኞች ተፅዕኖ በእኔ
እግር ኳስ ህይወት ውስጥ በጣም ከፍተኛ ነው፤
ጭንቅላቴ በጣም ስለሚቀበለው አሁን ባለው
የስልጠና ህይወቴም እየተጠቀምኩበት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …የጨዋታ ዘመንህ አንድ ምርጥ
ተጨዋች ጥራ ብልህስ ማንን ትላለህ…?
ብሩክ፡- አንድ መጥራት ከባድ ነው፤
ከዚህ ይልቅ የእኔን ምርጦች ብጠራ ይሻለኛል፡
፡ የችሎታውን ያህል ብዙ ያልተነገረለት
የኃይሌ ኳሴ ወንድም የላ ኳሴ እስከዛሬ የእሱን
አይነት ተጫዋች አይቻለሁ የማልለው ኤልያስ
ጁኸር፣ ካሳዬ አራጌ፣ አሰግድ ተስፋዬ (ነፍሱን
ይማረውና)፣ ተክሌ አንዋር ያሲን (ትልቁ)
በጣም ምርጦች ነበሩ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከባህር ማዶ ፍቅርህን ያለስስት
የምትሰጠው… የምታደንቀው አሰልጣኝ…. ?
ብሩክ፡-… ብዙ የተከታተልኩት… ድላቸ
ውን ያጣጣምኩት… የሰር አሌክስ ፈርጉሰንን
በመሆኑ ለእሳቸው የተለየ ቦታም ትልቅ
ክብርም አለኝ፡፡ አሁን ደግም አሰልጣኝ ፔፕ
ጋርዲዮላ ላይ የማየው በጣም ስለሚያስደስተኝ
ተፅዕኖውንም በግልፅ ስለማይ ለእሱም የተለየ
የአድናቆት ስሜት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከክለቦችስ…ማን በድንቅ
ጨዋታው አሸንፎሃል…?
ብሩክ፡- …ማንቸስተር ዩናይትድና
ባርሴሎና… ሁለቱም ነፍሶቼ ናቸው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ከተጨዋቾችስ… ልብህ ለማን
ያደላል…?
ብሩክ፡- …ውይ… ለእኔ የትልቁ ሮናልዶ
(ብራዚላዊውን) ያህል የሚሆንብኝ የለም…
እሱን በፍቅር እወደዋለሁ፤… በማድነቅ ደረጃ
ግን አሁን ካሉት የማደንቃቸው አይጠፋም…
በመውደድ ደረጃ ግን ትልቁ ሮናልዶን ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ከምታደንቃቸው ተጨዋቾች
ውስጥ አንዱ የላ ኳሴ (የኃይሌ ኳሴ ወንድምን)
አንስተሃል፤ እሱን በተመለከተ አንድ ጊዜ ቅጣት
ምት አግኝታችሁ በራስ መተማመኑን ብቃቱን
የሚያሳይ ነገር አድርጎ ነበር ሲሉ ሰማሁ…
እስቲ እሱን ነገር አስታውሰህ አጫውተኝ…?
ብሩክ፡- …(በጣም ሳቅ)…በጣም የሚገርም
ነገር ነው…ምን ሆነ መሰለህ…አንድ ጊዜ
ስንጫወት ከግብ ክልሉ 16.50 ራቅ ያለ ቦታ
ላይ ቅጣት ምት እናገኛለን… የላ ለመምታት
እየተዘጋጀ… እኛም ከአሁን አሁን መታው ብለን
ስንጠብቅ… ድንገት መምታቱን አቆመና… “…
እንዴ ምን እየሰራችሁ ነው….? ተቃቀፉ፣
ደስታችሁን ግለፁ እንጂ…”ሲለን…እንዴ ገና
ሳትመታው…? …በዚያ ላይ ሳታገባው…?…
ስንለው…“…ጊዜ አታቃጥሉ… ለምን ከወዲሁ
ደስታችሁን ተቃቅፋችሁ አትገልፁም…?…በሉ
ተቃቀፉ…”…ሲለን…እኛም ኳሷን ሣይመታው
ልክ ግቡ እንደገባ ዘለን ተቃቀፍን… ልክ
ተቃቅፈን… ደስታችንን ገልፀን ስንጨርስ…
ኳሱን መቶ አገባው… እንደገና… ደግሞ
ተቃቅፊን ደስታችንን ገልፀናል፡፡ የላ
የችሎታውን ያህል ብዙ ያልተወራለት በጣም
ትልቅ አቅም ያለው ተጨዋች ነበር፤ ምን ያህል
በራሱ እንደሚተማመንና እርግጠኛ እንደሆነ
ይሄ ራሱ ያሳይሃል፡፡
እኛ ብቅ ባልንበት ጊዜ ኃይሌ ከሰፈር
ወጥቷል፤ የላ ኳሴ ግን እነ አስፕሪላን
ከሚደባደቡበት እነ ዮሴፍ ተስፋዬን ከቡቲክ
ቤት አሊ ረዲ ገና ልጅ እያለ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል
እየተማረ ከት/ቤት እያስቀረ እኔንና ሳምሶን
(ጆሮ)ን እስማኤልንም ከክለብ አልፈን ሀገር
አንድንጠቅም ያደረገ ባለውለተኛ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-አንዴ የብ/ቡድን ተጨዋቾች
ጣሊያን ላይ ሲጠፉ አንደኛው ተጨዋች
የመድኑ አማካይ በላያ ነበር፤ በእሱ መጥፋት
ስቅስቅ ብለህ አልቅሰህ ነበር…አሉ…ያለቀስክበት
የተለየ ምክንያት ነበረህ… ?
ብሩክ፡- …(በጣም ሳቅ)…እውነት ነው…
ከበላያ ጋር በጣም ነበር የምንግባባው፤ ብዙም
ታሪክ ነበረን። ለብ/ቡድን ተመርጦ ከሌሎች
ተጨዋቾች ጋር ጣሊያን ላይ ይጠፋል…
የሚገርምህ እኔም ለብ/ቡድን ተመርጬ ጉልበቴ
ላይ ጉዳት ስለገጠመኝ ቀርቼ እንጂ ያኔ እሱ
ሲጠፋ እኔም እብሬው ልጠፋ እችል ነበር፡
፡ እንዳልከው በላያ ከሌሎች ተጨዋች ጋር
ሲጠፋ እኔ በጣም ነው ያለቀስኩት፤ልክ ግማሽ
አካሌን ያጣሁ ያህል ነው ሐዘን የተሰማኝ፡፡
የሚገርመው ግን ቤተሰቦቹ ልጆችን ውጭ ሀገር
ሄደልን አውሮፓ ገባልን ብለው ድግስ ደግሰው
ደስታ በደስታ ሆነው የእኔ ማልቀስ ነው፡፡ አሁን
በቅርቡ በላያን አግኝቼው ያኔ ምንም በማያገባኝ
ያለቀስኩት ቆጭቶኛል… (ሳቅ)… አሁን ካሰኝ
ብዬ አስቄዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …በጨዋታ ዘመንህ ለአንተ
አስቸጋሪውና ፈታኝ ተጨዋች ማን ነበር…?
ብሩክ፡- …ውይ…ውይ…ኤልያስ ጁኸር
ነዋ…? …ኤልያስ ሜዳ ላይ ተጨዋች ሣይሆን
አስማተኛ ነው የሚመስልህ…፤እሱን በቀላሉ
ማቆም ከባድ ነበር፡፡ እውነቴን ነው የምልህ
የኤልያስ ጁኸር አይነት አጥቂ እስከአሁን
አይቻለው ማለት አልችልም፡፡
ሀትሪክ፡- ኃይሌ ኳሴን በጣም ትፈራዋለህ
ይባላል፤ ወንድሙ የላ ኳሴ በጣም ጓደኛህ
ስለሆነ ይሆን…?
ብሩክ፡- …ኃይሌ ኳሴ አያስፈርም…፤…
የሚያስፈራው ፍቅሩ፣ ደግነቱ፣ ለሰው አሳቢነቱ
ነው፡፡ ኃይሌ የምትፈራው አይነት ሰው ሣይሆን
በመልካም ስብዕናው የምትወደው ሰው ነው፤
ኃይሌ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይ ለኳስ
ሜዳ ትልቅ ውለታን የከፈለ ከአካባቢው ብዙ
ተጨዋቾች እንዲፈልቁ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠረ
እኛንም ለዚህ ያበቃን፣ ያሳደገን ሰው ነው፡፡
ይሄን አይነቱን ሰው ከልብህ ትወደዋለህ እንጂ
አትፈራውም፡፡ ከፈራህም የሚያስፈራህ ደግነቱ
መልካም አሳቢነቱ ብቻ ነው፡፡ ኃይሌ ኳሴ ብቻ
አይደለም ቤተሰቡ በተለይ ወንድሙ የላ ኳሴ
በተለይ ለእኛ ትውልድ ትልቅ ውለታን የዋለ
ሁሌም በመልካም ሥራቸው ስናስታውሳቸው
የምንኖር ሰዎች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በእናንተ የጨዋት ዘመን ትልቁ
የፊርማ ገንዘብ ከ10 ሺዎች የሚዘል አልነበረም፤
አሁን አንድም ታዋቂው ተጨዋቾች በሚሊዮን
ቤት የሚከፈላቸው ጊዜ ላይ ደርሰዋል ከዚህ
አንፃር ምነው በዚህ ዘመን ኖሬ በተጫወትኩ
ብለህ ትመኛለህ…?
ብሩክ፡- …በፍፁም አልመኝም…!…
ምክንያቱም በነበርኩበት ዘመን በማገኘው
ገንዘብም ሆነ ባሳለፍኩት የጨዋታ ጊዜ በጣም
ደስተኛ ሆኜ ነው ያሳለፍኩት፤ አሁን
የሚከፈለው ገንዘብ በጣም ብዙ ነው
እንደሚባለው ሁሉ በወቅቱ ለእኛም
ሲከፈለን የነበረው ገንዘብ እንደዚህ ነበር
የሚባለው። በወቅቱ በምታገኘው ገንዘብ
ካወክበት እኮ ህይወትህን መለወጥም
ትችላለህ፤ ለምሣሌ አሊ ረዲን ብትወስድ
በወቅቱ ባገኘው ገንዘብ በአንድ የፊርማ
ብር እኮ ሚኒባስ ገዝቷል፡፡ ቤት ልግዛ
ብትል ከ50 ሺህ ወይም ከ100 ሺህ
ስለማይበልጥ በአንድም ባይሆን በሁለት
አመት መግዛት ትችላለህ፡፡ ከዚህ
አንፃር በእኛም ጊዜ የነበረው ክፍያ
በነበረበት ዘመን ሊለካ ብዙ ስለነበር
ዛሬ በሚከፈለው ገንዘብ ጎምዥቼም
ተመኝቼም አላውቅም፡፡ በዚያ ወይም
በዚህ ዘመን የሚያሰኝኝ ነገርም የለም፡
፡ ደግሞም እኮ እኛ ለገንዘብ አይደለም
ስንጫወት የነበረው መድን ስገባ ጋሽ
ሀጎስ ስንት ይከፈልህ ሲሉኝ እርስዎ
ደስ እንዳልዎት ነው ያልኩት፡፡ አሁን
ከሚሊዮን 10 ብር ከጎደለ ክርክር አለ ይባላል፡፡
እኛ ግን ከገንዘብ በላይ ኳሱን ነበር የምንወደው፡
፡ እንደውም እኔ ምነው በኖርኩ ብዬ ሳይሆን
የምመኘው ምነው ከዚህ በላይ ቢያድግላቸው
ነው የምለው፤ እኔም ሆንኩ የእኔ ትውልድ
በነበርንበት ዘመን በምናገኘው ነገር ተደስተን
ስላለፍን ባዶ ምኞት አንመኝም፡፡
ሀትሪክ፡- …በጨዋታ ዘመንህ በጣም
የምትቆጭበት… ማነው ባላደረኩት የምትለው
አለ….?
ብሩክ፡- …ካለመብሰል… ከልጅነት
በመነጨ… ለትናንሽ ደስታዎች ብለን
ትሬይኒንግ ወይም ጌም እያለ ሳያመን አመመኝ
የምንለው ነገር ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው በጣም
ይቆጨኛል…፡፡… ሰውን ሣይሆን ራሴን
እንዳታለልኩም ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ በዚህ
አጋጣሚ ራሴንና ፈጣሪዬን ይቅርታ ብጠይቅ
ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …በአሁን ሰዓት እግር ኳሱ
በዘር በአካባቢ በመከፋፈል የስፖርታዊ ጨዋነት
ችግር ትልቅ አደጋ ሆኗል…፤… በዚህ ላይ ምን
ትላለህ…?
ብሩክ፡- …ስለዚህ ነገር አሜሪካም
እያለሁ… እዚህም ከመጣሁ በኋላም… ሰምቼ
በጣም አዝኛለሁ፤ በጣም በፍጥነት እልባት
ማግኘትና ከስፖርቱ አካባቢ መጥፋት ያለበት
ጉዳይ ነው፡፡ በተጨዋቾችም በተመልካቾች
ጭንቅላት ላይ በዚህ ዙሪያ በጣም ብዙና
ተከታታይ ሥራ ሊሠራ ይገባል፤ በዚህ በሰለጠነ
ዘመን ዳኛ በአደባባይ ሲደበደብ ማየት ያማል፡
፡ የዲሲፒሊን ጉዳይ በጣም ትኩረት ሊሰጠው
ይገባል፡፡ በእኛ ጊዜ እንኳን ዳኛ ድብደባ ከሆቴል
ወጣችሁ ተብሎ For life (እድሜ ልክ) ከኳሱ
እንታገዳለን፤ አሁን ግን ዳኛ የመታ ሶስት
ጨዋታ ተቀጥቶ ተመልሶ ይገባል፡፡ በእኛ ጊዜ
ቅጣቱ ይሄ ቢሆን እኔ በየቀኑ ዳኛ ስደበድብ
ነበር የምውለው ከሚወስነው ውሳኔ የተነሣ፡፡
ግን ጭንቅላታችን ላይ ስለተሠራ የፈለገ ቢወስን
በፀጋ ተቀብለን ነበር የምንወጣው፡፡ ዲሲፒሊን
ለእግር ኳሱ በጣም አስፈላጊው ነው፡፡ ከኤርትራ
ጋር ልንጫወት ስንል መጨረሻ ላይ እግዜር
ይስጣቸው አስቀሩት እንጂ በሆቴል ተይዘን
ቢራ ይዞ የተገኘ ተጨዋች እድሜ ልክ ይቀጣል
የሚለው ላይ ፈርመን ነበር የተያዝነው፡
፡ ስለዚህ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በጣም
ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን በዘር
በጎሣ ተሰነጣጥቆ ሠላማዊውን የእግር ኳስ
መንደር የጦር አውድማ ማድረግ አለመሰልጠን
ነው ለእኔ፡፡
ሀትሪክ፡- በአሁን ሰዓት በተለያዩ የሀገራችን
ክለቦች ፕሮፌሽናል በሚል በሚመጡ የውጪ
ተጨዋቾች እግር ኳሱ ተወሯል…፤… ይሄንን
እንዴት ትለዋለህ…?
ብሩክ፡- …አንደኛው ከሌሎች ነገሮች
በተጨማሪ የሀገሪቱን እግር ኳስ እየገደለ ያለው
ይሄ ነው…፤ …የተሻለ ችሎታ የሌላቸው
ትምህርት ወይም ምሣሌ የማይሆኑ የውጪ
ሀገር ተጨዋቾች ክለቦችን ወረው ማየቴ
በጣም አስደንግጦኛል፡፡ እንዴ…!… ምን
ማለትህ ነው…?… አሁን እኮ… በሀገሪቱ በረኛ
የሚባል እየጠፋ ነው…፤…ሁሉም ክለቦች
ማለት በሚቻል መልኩ በውጪ ዜጋ በረኞች
ተጥለቅልቀዋል…፤… አጥቂዎችን ብታይም
ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው፡፡ ድሮ በእኛ ጊዜ
ፖሊስ (ኦሜድላን) ብትወስድ ብቻውን ከ10
በላይ በረኞችን ነው ለእግር ኳሱ ያበረከተው፤…
ፊቱሼ፣ አሊ፣ ቢኒያም… እያልክ ትዘረዝራለህ፡
፡ አሁን ግን በረኛ እንደ ብርቅዪ እንሰሳ
እየጠፋ ነው፡፡ ብዙም ጥቅም ለሌላቸው
ተጨዋቾች… በሌለ ዶላር የምናወጣው ገንዘብ
ብዙ ታዳጊዎችን ያፈራ ነበር፤… አሁን ይሄን
መንገድ በመከተላችን የሀገሪቱን በረኞች
እያጠፋን የዚህ ችግርም ብ/ቡድኑ ላይ እያረፈ
በ ውጤት ደረጃ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ከዚህ ሌላ
ተተኪዎች እንዳይፈሩም በር እየዘጋን ነው፡፡
ስለዚህ ይሄ ቢታሰብበት። በጣም የሚገርመህ
እኮ ለዋንጫ ወይም በአፍሪካ መድረክ የሚሣተፉ
ክለቦችስ ይሁኑ ላለመውረድ የሚጫወት፣ ታች
ዲቪዚዮን ያለ ቡድን ከውጪ በመጣ ተጨዋች
ሲወረር ማየት ለእኔ አደጋው ከባድ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ እግር ኳስ
የሚጠቅሙ ተጨዋቾችን በማፍራት ደማቅ
አሻራቸውን ካሳረፉ ሜዳዎች አንደኛው ኳስ
ሜዳ ነው ብል አልተሳሳትኩም…፤… ኳስ ሜዳ
የበርካታ ተጨዋቾች መገኛ የመሆንዋ ምስጢር
ምንድነው ትላለህ…?
ብሩክ፡- …የዛሬን አያድርገውና ኳስ ሜዳ
ራሱን የቻለ ታላንት ኤሪያ ነው፤በእኛ ጊዜ
አንድ አይደለም አምስት ሜዳ ነው የነበረው፤
ዛሬ ግን አንድም ጠፍቶ ት/ቤት ተሰርቶበታል።
የሚገርምህ የእኔና የሰይፈ ውብሸት
(ፕሮም) ቤት ፊት ለፊት ነው… ትሬይኒንግ
የምንሰራውም ለየብቻ ነው፤ የዚህ ቅያስና
የዚያኛው ቅያስ በሚል ተከፋፍለን ቡድን
መስራታችንን ስታይ ምን ያህል ብዛት ያላቸው
ተጨዋቾች እንዳሉ በዚህ ታውቃለህ፤ ጠዋት
ለጨዋታ የወጣን ማታ ነው የምንመለሰው፡
፡ ህይወትህ መሠረት ያደረገው እዛው ሜዳ
ውስጥ ነው፡፡ መጀመሪያ እነ ኤፍሬም ግዛቸው
ጃምቦ ወጡ ከዚያ የእነ ኃይሌ ኳሴ ዘመን ቀጠለ
እኔ ሣምሶን (ጆሮ)፣ አሊ ረዲ፣ እያለ ይሄድና
እነ ቴዲ (ባሪያው)፣ካሊድ፣ ኡመር ቀጥሎ
ደግሞ እነ ብርሃኑ (ፋዲጋ) ቢኒየም ግስላ እያለ
ይወርዳል፡፡ አየኸው የትውልድ ቅብብሎሹን…?
ኳስ ሜዳ ለብሔራዊ ቡድንና ለታላላቅ ክለቦች
በርካታ ተጨዋቾች በማፍራት ትልቅ ታሪክ
ያለው ሜዳ ነው፡፡ ኳስ ሜዳ ስትወለድ ከኳስ
ጋር ነው፡፡
ሀትሪክ፡-በርካታ ተጨዋቾችን የሚያፈራው
የኳስ ሜዳ ማህፀን አሁን የነጠፈ ይመስላል…?
በዚህ ላይ ምን ትላለህ…?
ብሩክ፡- …አንዴ ምን ሆነህ ነው… ለምን
አይየነጥፍም…?… በእኛ ጊዜ ከአንድም አምስት
የነበረው ሜዳ ዛሬ አንድም የለም ጭራሽ
ሜዳው ላይ ት/ቤት ተሰርቶበታል፤ት/ቤት
መሠራቱ ላይ ችግር ባይኖርብኝም ለአካባቢው
ወጣቶችም መታሰብ ነበረበት፡፡ በሜዳው ላይ ት/
ቤት በመሠራቱ የትውልድ የቅብብሎሽ ሰንሰለት
መበጠሱን ነው የምታየው፡፡ እንደውም ት/ቤት
መሠራቱን አስመልክቶ ሳምሶን (ጆሮ) ምን
እንዳለ ታውቃለህ? ት/ቤቱ እስከ አሁን ሁለት
ነርስ ብቻ ነው ያወጣው.. ሳቅ… ብሎ እኛንም
አስቆናል፡፡ ያ ተጨዋች እንደጉድ የሚያ መርት
ሜዳ አሁን በተጨዋች ድርቅ ሲጠቃ ስታይ
ታዝናለህ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ አንስተህ
ኳስ ሜዳን መዝለል አይቻልም፡፡ የሚገርምህ
ከኳስ ሜዳ ሌላ የብዙ ተጨዋች መፍለቂያ
የሆነው አሸዋ ሜዳም በሚያሳዝን ሁኔታ
የአሮጌ መኪናዎች ማከማቻ ሆኗል፡፡ በየሠፈሩ
ያለን ሜዳ ማጥፋት ትውልድ የማጥፋት ያህል
ነው፡፡ እዚያ ሲቦርቁ የሚውሉ የነገ ታዳጊዎች
ላይም ሱሰኛ ሆኑ ብሎም መፍረድ ነው፡፡ አንድ
መንደር ወይም ት/ቤት ስትሠራ ለትውልዱም
ማሰብ አለብህ፤ ስራ የምትሠራው ትውልድ
እየገደልክ መሆን የለበትም፡፡ በስፖርት የዳበረ
ያደገ ትውልድ ሲኖርህ ነው ሀገርም ምርታማ
የምትሆነው፤ስፖርት የማይሠራ ከሆነ ለበሽታ
የቀረበ ወይም በሽተኛና በሱስ የተጠቃ ዜጋን ነው
የምታፈራው፡፡ ምናልባት የመሬት ዋጋ ውድነት
ወይም ገንዘቡ ሊያሳሳን ይችላል፤ በየሠፈሩ
ያለን ሜዳ እየነጠክ ትውልድ የምታጠፋ ከሆነ
አገር እየገደልክ እንደሆነ ሊገባህ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-በአሜሪካ በተጫዋችነትም
በአሰልጣኝነትም እያሳለፍክ እንደሆነ
በአንተ አሠልጣኝነት የሚመራው ቡድንም
በኢትዮጵያዊያን ውድድር ላይ ሻምፒዮን
መሆኑን ሰምቻለሁ…በስልጠናው በፕሮፌሽናል
ደረጃ የመግፋት ሃሳቡ የለህም….?
ብሩክ፡- …እንዳልከው በተጫዋችነትና
በአልጣኝነት እያሳለፍኩ ነው፤ በኢትዮጵያዊያን
ውድድር ከአንድም ሶስት ጊዜ ሻምፒዮን
ሆኛለሁ፡፡ የከተማ የውስጥ ውድድር ዋንጫ
እንዲሁም የ5ሺህ ዶላር ሽልማትን በተደጋጋሚ
አግኝቻለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር አሰልጣኝ የመሆን
ፍላጎቴ ከፍተኛ ነው፤ ወደ አሜሪካ ስሄድም
ቤት የመስራት ምኞትን ይዤ አይደለም፡፡ኮች
መሆንንም አልሜ ነው፡፡ እነ ኃይሌ ኳሴ ኬነዲደ
መንገሻም ሁሌም ይጎቱቱኛል፤ እኔም ብቃቱ
እንዳለኝ ነው የማምነው፡፡ ችግሩ በደንብ ሥራዬ
ብለህ ለመያዝ በአሜሪካ የሥራው ሁኔታ
ብዙም አይመችኝም፡፡ እንደ ሀገር ቤት የእናት
የወንድም ቤት የምትለው ነገር የለም፡፡ በቀጣይ
ሁለት አመት ግን ሙሉ በሙሉ አገባለሁ ብዬ
አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ምኞት ብቻ … ወይስ ስልጠና
ወስድሃል….?
ብሩክ፡- …የተወሰነ አዎን ወስጃለሁ፤ ግን
ከዚህም በላይ እግዚአብሔር የሰጠኝ ስልጠና
አለ፡፡ ይሄን ስልህ ስልጠና አያስፈልግም
እያልኩ አይደለም፡፡ ትላልቅ ቡድኖች
የአውሮፓ ጨዋታን ቁጭ ብዬ ብተነትንልህ
ያን ጊዜ ይገባሃል፡፡ ስለ ቡድኑ አጨዋወት ስለ
አሰልጣኞቹ ፍልስፍና ከጨዋታው ተነስቼ ማን
በውጤትም በጨዋታም ይበልጣል የሚለውን
ባስቀምጥልህ ውስጤ ያለውን ነገር በቀላሉ
ትረዳለህ፡፡ እኔ ጣሊያንኛ አልችልም፤የጣሊያን
ክለቦች የሚያደርጉትን ጨዋታ ብተነትንልህና
ባለሙያዎች የሰጡትን ትንተና አስተርጉመህ
ብትሰማው በቀላሉ ስለ እውቀቴ ትረዳለህ፡
፡ ብዙዎችን ጋዜጠኞችን ስታይ ከውስጣቸው
ሣይሆን ፈረንሣይኛውን ወይም እንግሊዝኛውን
ተርጉመው ያንን ሸምድደው እንደ ራሣቸው
አድርገው ነው የሚያቀርቡት፤ የእኔ ግን ከበዙ
አሰልጣኞች ያገኘሁት ነው፡፡ ሁልጊዜም ቡድኔን
በተመለከተ ከአሰልጣኞች በላይ ተጨዋቾቹን
የማነሳሳው እኔ ነበርኩ ያ በጣም ጠቅሞኛል፡
፡ ወደ ስልጠናው ብገባ ይሳካልኛል የሚለው
እምነቴ የጠነከረ የሆነው ከዚህ የመነጨ ነው፡
፡ ከካሳዬ አራጌ ጋር ብዙ ጊዜ እናወራለን፤
ሁለታችንም ቡድን ይዘን እንደ ሞውሪንሆና
ጋርዲዮላ በታክቲክ ብንተናነቅ ሠላማዊ ጦርነት
ብንከፍት እለዋለሁ፡፡ እሱ በቅርቡ ይሄን
የሚያሳካው ይመስለኛል፤ እኔ ግን እንዳልኩህ
በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ከእግዚአብሔር
ጋር…፡፡
ሀትሪክ፡- …በእኔ በኩል ጨረስኩ አንተ
ቀረ የምትለው ወይም ማመስገን የምትፈልገው
ካለ…እድሉን ልሰጥህና አመሰግኜህ እንለያይ…?
ብሩክ፡- …ብሩክ የሚለው ስም በእግር
ኳሱ ጎልቶ እንዲወጣ የለፉትን፣ የደከሙትን
በአጠቃላይ አመሰግናለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ
በተለይ ኃይሌ ኳሴ፣ ብርሃኑ ተርፋስን በጣም
ነው የማመሰግነው፤የአክስቴ ልጅ የሆነው
ብርሃኑ በወቅቱ ታዋቂና ዝነኝ ደጋፊ የሆኑትን
መረተ አላምረውንና አያሌውን ያስተዋወቀኝ
እሱ ነው፤ እነሱና እንዲሁም ለእሸቱ ዳኜ
ላቅ ያለ ምስጋናም አለኝ፡፡ ከሁሉም በላይ
የከበረ ምስጋና ማቅረብ የምፈልገው ለየላ
ኳሴ ነው፡፡ የላ በፍፁም ልቤ ውስጥ ያለ
የማይረሣ ባለውለተኛዬ ነው፡፡ ሁሌም ሌሌት
ሌሊት ከእኛ ቀድሞ እየተነሣ ጣሪያችን ላይ
ድንጋይ እየወረወረ በመቀስቀስ የእግር ኳስ
ሀሁን ያስተማረን ትልቅ ባለውለተኛችን
ስለሆነ እሱንም በጣም ማመስገን እወዳለሁ፡
፡ የላ የችሎታውን የመልካምነቱን ያህል
ያልተወራለት ግን ለብዙዎቻችን ውለታን የዋለ
ስለሆነ እሱን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡
፡በተረፈ ሀትሪኮችን አስታውሳችሁ እንግዳ
ስላደረጋችሁኝ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡