ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ

የክለቡ ዋና አሰልጣኝ፡- ማርት ኖይ                           index
የቡድን መሪ ፡- ታፈሰ በቀለ
አሰልጣኝ ፡- ፋሲልተካልኝ /ዘሪሁን ሸንገታ
የህክምና ባለሙያ ፡- ዘላለም አዱኛ
የበረኛ አሰልጣኝ ፡- አይሚ
Website: www.saintgeorgefc.com

ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ረዥም እድሜ ያለውና በውጤታማነቱ ቀዳሚ የሆነ ክለብ ነው፡፡ የተመሰረተው በ 1928 ዓ/ም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና፣ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ፣ በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግና በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በርካታ ዋንጫዎችን መሰብሰብ የቻለ ክለብ ነው፡፡

ምስረታ

እግር ኳስ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በውጪ ሀገር ኮሚኒቲዎች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ትክክለኛው ወቅትና ታሪኩ በመዝገብ ሰፍሮ ባይገኝም በ 1916 ዓ/ም እንደሆነ ይነገራል፡፡ እስከ 1928 ዓ/ም የነበሩ ቡድኖችም በውጭ ሀገር ዜጎች የተመሰረተ ነበር፡፡ ታህሳስ ወር 1928 ዓ/ም የመጀመሪያው የኢትዮጵያውያን ክለብ እውን ሆነ፡፡ የአራዳ አካባቢ ልጆች ከኪሳቸው ገንዘብ አዋጥተው ራሳቸውን ተጨዋቾች አድርገው ቅዱስ ጊዮርጊስን መሰረቱ፡፡ ኤየለ አትናሽና ጆርጅ ዱካስ ደግሞ አስተባባሪዎች ነበሩ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ስም ያላቸው ይድነቃቸው ተሰማ ክለቡ ከተመሰረተ ከሁለት ወር በኃላ እንደተቀላቀሉት የክለቡ መረጃ ያመለክታል፡፡ ጊዮርጊስ በተመሰረተበት አመት ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ ለነፃነት መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ በአምስቱ የጣልያን የወረራ ዘመናት “ቅ/ጊዮርጊስ” የሚለው ስያሜ በጣልያኖቹ ዘንድ ባለመወደዱ “ሊቶርዮ ውቤ ሰፈር አራዳ” በሚል ስያሜ እንዲጠራ ተደርጎ ነበር በወቅቱ በነበረው የወራሪዎቹ የዘረኝነት አስተሳሰብ ጥቁሮች ከነጮች ጋር እንዳይጫወቱ ይደረግ ስለነበር ቅ/ጊዮርጊስ ከሌሎች የኢትዮጵያውያን ቡድኖች ጋር እንጂ ከውጭ ሃይሎች ጋር አይጫወትም ነበር፡፡ በወቅቱ ከጊዮርጊስ በተጨማሪ የቀበና፣ የጉለሌ፣ የስድስት ኪሎና እንጦጦ በመባል የሚታወቁ የኢትዮጵያውያን ቡድኖች ነበሩ፡፡ ጊዮርጊስ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ጨዋታውን ሲያደርግ ሲመሰረት የነበረውን የነጭና ቡናማ ማልያ በመተው ሰማያዊ ማልያ በመልበስ አምስቱን የወራራ ዘመን አሳልፏል፡፡

ከ1933 ከድል በኃላ የነፃነት ዘመን ላይ ጊዮርጊስ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ከውጭ ዜጎች ጋርም መጫወት ጀመረ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመው የውጭ ሀገር ዜጎች ቡድን “አራራት” የተባለውን የአርመናውያን ቡድን ነበር፡፡ በውጤቱም ጊዮርጊስ 2 ለ0 ሲያሸንፍ የቡድኑ አምበል የነበረው ወጣቱ ይድነቃቸው ተሰማ አንዷን ጎል ከመረብ አሳርፏል፡፡ በ 1935 ዓ/ም በመድፈኛ ሜዳ ላይ ቅ/ጊዮርጊስ ፎርቲቲ ዮዳ ከተባለ የጣልያን ቡድን ጋር ተጫወተ፡፡ በውጤቱም ቅ/ጊዮርጊስ የ4ለ1 ድል ባለቤት ሆነ፡፡ በጣልያን ዘመን ወረራ ለጣልያውያን ጥላቻ አትርፈው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በጊዮርጊስ ድል ደስታቸው ወደር አጥቶ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

ቅ/ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ሻምፒዮና

የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው በ 1936 ዓ/ም ነበር ቅ/ጊዮርጊስን ጨምሮ አምስት ክለቦች በውድድሩ ተካፍለዋል፡፡ ብሪትሽ ሚሊተሪ፣ የጣልያኑ ፎርቲቲዩን፣ የግሪኩ ኦሎምፒያክስ እና የአርመኑ አራራት ከጊዮርጊስ በተጨማሪ የሻምፒዮኑ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የብርቲሽ ሚሊተሪ ቡድን ውድድሩን በሻምፒዮንነት ሲያጠናቅቅ ቅ/ጊዮርጊስ ሁለተኛ ደረጃን በማግኘቱ ከንጉስ ነገስት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ የግድግዳ ሰዓት ተሸልሟል፡፡

በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከ1937-1941 ባልታወቀ ምክንያት ውድድሩ ሣይካሄድ ቀርቷል በቀጣዮቹ 17 ዓመታት ውጤት ርቆት ነበር፡፡ በ 1958 ግን በአዲስ ትውልድና በአዲስ መንፈስ ወደ ውጤታማነተ ተመለሰ፡፡ በ 1958 ከረዥም ጊዜ በኃላ ሻምፒዮን ሆነ፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አመታትም የዋንጫ ባለቤት በመሆን ለሥስት ተከታታይ አመታት ሻምፒዮን በመሆን ዋንጫውን የግሉ አደረገ፡፡ ከኢትዮጵያ ሻምፒዮን በተጨማሪ በ 1965፣ በ 1966 እና 1967 የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን በመሆን ውጤታማ ዘመን አሳልፏል፡፡ በ 1967 ሁለት ዋንጫዎች በመውሰድ የጣምራ ድል ባለቤት ሆኗል፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ “አዲስ ቢራ”

በአፄ ሀይለስላሴ ዘመን ቅ/ጊዮርጊስ ተብሎ ይጠራ የነበረው የክለቡ ስያሜ በደርግ ስርአት ስሙን እንዲቀይር አስገደደው “አዲስ ቢራ ክለብ” ተብሎ ለመጠራት ተገደደ፡፡ በወቅቱ ህዝባዊ ድጋፍ እንደነበረው የሚነገር ቢሆንም የመንግሥት አመራሮች ደስተኛ ባለመሆናቸው በ 1970 ክለቡ እንዲፈርስ ሆነ፡፡ በወቅቱም የነበሩት የድል ዋንጫዎችና ቅርሶች መዘረፋቸው፣ ከውድድር መገለሉ፣ ከአቶ ህሩይ ተክለማሪያም የተበረከተለት መለስተኛ አውቶብስ መወሰዱን በክለቡ ድረገፅ የሰፈረው ታሪክ ያመለክታል፡፡ ይህንንም ጊዜ “የችግር ዘመን” ሲል ክለቡ ይጠራዋል፡፡
በ 1975 ዓ/ም የክለቡ ዳግም ውልደት እውን ሆነ፡፡ በአዲስ መልክ ተደራጀ ባርኖሮና ፖሊስ ሜዳ ተብለው በሚጠሩት ሜዳዎች ወርዶ በመጫወት ለሁለት አመት በሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርዶ ለመጫወት በቃ፡፡ በ 1977 ዓ/ም ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ለመመለስ በቃ፡፡ ክለቡ በ 1977 ዓ/ም ውጤታማ ዘመን አሳለፈ፡፡ ሰለሞን መኮንን ሉጆ ዳኛቸው ደምሴዳኙ ገላግለን፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ገ/መድህን ሀይሌ እና ሌሎችንም ወሳኝ ተጫዋቾች ያካተተው ቡድን የኢትዮጵያ ሻምፒዮናና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን በጣምራ አነሳ፡፡ ዳኛቸው ደምሴ በኮከብ ተጫዋችነት ሙሉጌታ ከበደ በኮከብ ግብ አግቢነት ተመረጡ፡፡ ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በ 1979 ዓ/ም እና በ 1979 ዓ/ም በተከታታይ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን በመሆን ሀትሪክ ሰራ፡፡ ዋንጫውንም የግሉ በማድረግ አስቀርቷል፤ ሙሉጌታን ከበደን በኮከብ ተጨዋችነትና ግብ አግቢነት አስመርጧል በ 1979 ዓ/ም ደግሞ የኮከብ ተጨዋችነቱን ሰለሞን ዩሀንስ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ጌቱ ከበደ አሸነፉ፡፡

ቅ/ጊዮርጊስ በኢትዮጰያ ፕሪሚየር ሊግ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 1990 ዓ/ም የኢተዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ ሲኬሄደ መካፈለ አልቻለም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የብሄራዊ ሊግ ተወዳዳሪ ነበርና። በቀጣየ አመት ሊጉን ሲቀላቅለ ሻምፒዮን ሆነ። በቀጣዩ አመትም ደገመ። በ 1993 መብራት ሀይለ ሻምፒዮን በመሆኑ ለሶሰተኛ ጊዜ ዋንጫ ለመውሰድ የነበረው ህልም ሳይሳካ ቀረ። በሚቀጥሉት ሁለት አመታትም በ 1994 እና 1995 በተከታታይ የዋንጫ ባለቤተ ሆነ። ሀዋሳ ከነማ የ1996 ሻምፒዮን መሆኑ አሁንም ሀትሪክ የመስራት ህልሙ እንዲጨናገፍ አደረገው። 1997 እና 1998 ለሶስተኛ ጊዜ የተከታታይ ድል ባለቤት ሆነ። 1999 ከጨክለቦቸ ከፈደሬሽኑ ጋር የተፈጠረው ውዝግብ ዋነኛ ተዋናይ የነበረው ጊዮርጊስ ራሳቸውን ከውደድሩ ካገለሉ ክለቦች አነዱ በመሆኑ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ሻምፒዮን የመሆን አላማው ለሶስተኛ ጊዜ ተጨናገፈ። በ 2000፤ 2001 እና 2002 ዋንጫውን በማንሳቱ ግን በስተመጨረሻው አላማውን እንዲያሳካ አስችሎታል። ክለቡ እስከ 2002 ከተዘጋጁት 13 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች ውስጥ ዘጠኙን በመውሰድ ፍፁም የበላይነቱን አሳይቷል::

የቅ/ጊዮርጊስ ስታድየም

ቅዱስ ጊዮርጊስ በስታድየም ዙርያ በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ አዲስ ምእራፍ ለመክፈት እንቅስቃሴ ከጀመረ ሰነባብቷል። ሲ ኤም ሲ አካባቢ ቦታ በተረከበው ቦታ ግነባታ ለማከናወን የሚያስችለውን ስምምነት ሲ.ጂ.ሲ.አይ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር በመጋቢት 2002 ተፈራርሟል።የስታድየም ግንባታው247 ሚሊየን ብር 18. ዶላር የሚፈጅ ሲሆን በተደረሰው ስምምነት መሰረትበሁለት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል።

ቅ/ጊዮርጊስ በአህጉር አቀፍ ውድድሮች

ቅ/ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ በውጤታማነቱ የሚጠቀስ በመሆኑ ለበርካታ ጊዜ በኢንተርናሽናል ውድድር መሳተፍ የሚያስችለው ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በዚህም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች በተሻለ ሁኔታ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ በአህጉር አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው እ.ኤ.አ በ 1967 1959 ነበር፡፡
በወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን ክለቦች ዋንጫ ተብሎ ይጠራ በነበረውና በአሁኑ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲሆን በታሪኩ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበበት ውድድር ነበር፡፡ በመጀመሪያው ዙር የኡጋንዳው ቢቲማስቲክ ማሱን ራሱን ከውድድሩ በማግለሉ ጊዮርጊስ በቀጥታ አለፈ፡፡ በሁለተኛው ዙር የግብፅን ኦሎምፒክ አሌክሳንዴርያን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው አለፉ ለፍፃሜ ለማለፍ ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ኢንግልበርት የአሁኑ ቲ.ፒ ማዜምቤ ጋር ተገናኝቶ 4ለ3 በሆነ ድምር ውጤት ተሸንፎአል፡፡ አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 ቢያሸንፍም ኪንሻሳ ላይ 3ለ1 በመሸነፉ ነው ለፍፃሜ የማለፍ እድሉ ያልተሳካው፡፡ አሸናፊው ኢንግልበርት በፍፃሜ ጨዋታውም በማሸነፍ የአመቱ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በቀጣይ አመታት 1968 እና 1969 በመጀመሪያው ዙር ተሰናበተ በ 1972 በሁለተኛው ዙር ማለፍ አልቻለም፡፡ በ 1976 በመጀመሪያ በ 1986 በሁለተኛው ዙር ከውድድሩ ወጣ፡፡ በ 1991 1983 በኢትዮጵያ በነበረው የመንግስት ለውጥና አለመረጋጋት ምክንያት ራሱን ከውድድረ አገለለ፡፡ በ 1992 እና በ 1993 ቅድመ ማጣሪያ በነበረባቸው ውድድሮች አልተሳካለትምና ወደ አንደኛ ዙር እንኳን አልደረሰም፡፡ ከዚህ አመት በኃላ የወድድሩ ፎርማትና ስያሜ ተለወጠ፡፡
ከ1997 ጀምሮ ይህ ውድድር የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በሚል ስያሜ ተተካ፡፡ በመጀመሪያው ውድድር በመጀመሪያው ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ፡፡ ከግብፁ ታዋቂ ክለብ ዛማሊክ ጋር የተገናኘ ሲሆን ግብፅ ላይ 2ለ0 ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይቶ 3ለ1 በሆነ ድምር ውጤት ተበልጦ ነበር ማለፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ ያልተቻለው፡፡
ቀጣይ ተሳትፎውን ያገኘው በ 2000 ነበር በቅድመ ማጣሪያው የኡጋንዳውን ቪላ ካምፓላን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት ረትቶ አለፈ፡፡ከሜዳው ውጪ ካምፓላ ላይ ሁለት አቻ ተለያይቶ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ 3ለ0 አሸንፎ ነበር ውጤታማ የሆነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር በቪታሎ ቡሩንዲ በመሸነፉ ጉዞው አልረዘመም፡፡ ከሜዳው ውጭ 2ለ2 አቻ ቢለያይም በሜዳው 2ለ1 መሸነፉ ነበር ከውድድሩ ላለመዝለቁ ምክንያት የሆነው፡፡ በቀጣዩ አመት 2001 ከኬንያ ተስካር ጋር የተገናኘ ሲሆን አዲስ አበባ ላይ 1ለ1 ኬንያ ላይ ደግሞ ያለግብ አቻ ተለያዩ፡፡ ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ህግ መሰረት ተስካር አላፊ ጊዮርጊስ ወዳቂ ሆኑ፡፡
በ 2003 ለአራተኛ ጊዜ የመሳተፍ እድል ባገኘበት ወቅትም ቅድመ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለም፡፡ ኡጋንዳ ላይ 1ለ0 ቢያሸንፍም አላለፈም፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ አዲስ አበባ ላይ 3ለ1 ተሸንፎ ነበርና፡፡ በቀጣይም ውድድር 2004 ላይ ደግሞ በሱዳኑ አልሂላል አምደርማን ተሸንፎ በመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳውና ደጋፊው ፊት አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 ተሸንፎ ስለነበር ካርቱም ላይ አንድ አቻ መለያየቱ ሊያሳልፈው አልቻለም በእነዚህ ሁለት አመታት ከሜዳው ውጭ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም በሜዳው አለመጠቀሙ ጎድቶታል፡፡
በ 2006 አወዛጋቢ የውድድር ዘመን ያሳለፈበት ነው በመጀመሪያው ዙር ከግብፅ ኢንፒ ENPPI ጋር ነበር የተገናኘው፡፡ ይህ ክለብ በወቅቱ በአረብ ሻምፒዮንስ ሊግ ለፍፃሜ የበቃ ስለነበር ጨዋታው ጠንካራ ይሆናል የሚል ግምት አድሮ ነበር፡፡ ይሁንና ከሜዳው ውጭ 0ለ0 በመለያየት በሜዳው ደግሞ 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ፡፡
በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የጋናውን ኸርትስ ኦፍ ኦክል 4ለ0 አሸነፈ፡፡ ይህ በኢንተርናሽናል ውድድር ታሪኩ ታላቅ ድል ስለነበር በቀጣይ ተስፋ ተጣለበት፡፡ በመልሱ ጨዋታ ግን ያልተጠበቁ ክስተቶችን አስተናገደ፡፡ ከሆቴል ጀምሮ የደረሰበት እንግልት እስከ ሜዳ ዘለቀ፡፡ የእለቱ ዳኛ አወዛጋቢ ውሳኔዎችንአሳለፉ፡፡ ባለሜዳዎቹ 2ለ0 መሩ የፍፁም ቅጣት ምትም አገኙ በዚህ ወቅት በደሉን መቋቋም ያልቻሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የኦህንጃን ስታድየምን ሜዳን ጨዋታው ሳይጠናቀቅ አቋርጠው ወጡ የውድድሩ አስተዳዳሪ ፊፋ ውሳኔም ወደ ጋናው ክለብ ተጋዘ፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ ወድቆ ኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲያልፍ ተደረገ፡፡
በተከታዩ አመት 2007 የመጀመሪያውን ቁጭት ይዘው አዲስ አበባ ላይ የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤቶል ዲ ኮንጎን ያስተናገዱት ጊዮርጊሶች 1ለ0 አሸነፉ፡፡ በመልሱ ጨዋታ 2ለ0 መሸነፋቸው ግን ህልማቸውን አጨናገፈባቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ቡድኖች ላይ ገብተው ኤቶልን ከመግጠማቸው በፊት ከሱፐር ኤስከም ጋር ተደልድለው ነበር፡፡ ይሁንና የማላዊው ክለብ ራሱን በማግለሉ በቀጥታ አለፉ፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት አመታትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ፊፋ ሀገሪቱን ከማንኛውም ኢንተርናሽናል ውድድር ማገዱ ክለቦቻችንንም ይመለከታልና ቅ/ጊዮርጊስም መሳተፍ በነበረበት 2009 ሣይሳተፍ ቀረ፡፡ የተፈጠረው ችግር ተቀርፎ እገዳው መነሳቱ በ 2010 ወደ ውድድር እንዲመለስ አስቻለው የተደለደለውም ከሱዳኑ ኤልሜሪክ ጋር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ ሜሪኮች መምራት ችለው ነበር መሐመድ ናስር በጭንቅላት በመግጨት ያስቆጠራት ግብ ግን ባለሜዳውን ነጥብ አጋራች፡፡ የመልሱ ጨዋታ በኤልሜሪክ ስታዲየም ሲደረግ አዳነ ግርማ ቅ/ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል፡፡ ማሪኮች ሥስት ግቦችን በማስቆጠራቸው ጊዮርጊስን ጥለው ማለፍ ቻሉ እንጂ ይህ ጨዋታ በጋዜጠኛ መሰለ መንግስቱ አማካኝነት በሬድዮ በቀጥታ ተላልፏል፡፡በዚሁ አመት በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የመስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለፍፃሜ መድረስ ችሏል ። በዚህመ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ክለብ ሆኗል። ምንም እንኳን ዋንጫውን ለመውሰድ የነበረው ህልም በሩዋንዳው ኤ ፒ አር በመሸነፉ ቢጨናገፈም።