በአስረኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት ጨዋታቸውን ያደረጉት ወልቂጤ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና 2 አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል ።
ወልቂጤ ከተማ በዘጠነኛው ሳምንት ሰበታ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ በሀይሉ ተሻገርን እና ተስፋዬ ነጋሽን በዮናታን ፍስሀ እና ዳግም ንጉሴ ቀይረው የገቡ ሲሆን በሀድያ ሆሳዕና በኩል ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ እሸቱ ግርማን በ ቃልአብ እና ኡመድ ኡክሪ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ በተንቀሳቀሱበት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ግብ በመድረስ ከወልቂጤ ከተማ በአንፃራዊነት የተሻሉ ነበሩ ። በተለይም የሀድያ የመሀል ክፍል ጠንካራ ሆኖ መቅረብ እና ከፊት አጥቂዎች ጋር የነበራቸው መናበብ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር እንዲችሉ አድርጓቸዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በሀድያ ሆሳዕናው አማካይ ተስፋዬ አለባቸው የተደረገ ሲሆን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ተመልሷል ።
በ15ኛው ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ። ብርሀኑ በቀለ በቀኝ መስመር ላይ ከተስፋዬ አለባቸው የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ሶስት ተጫዋቾችን አልፎ ለፍቅረየሱስ ተክለብርሀን ያቀበለው ሲሆን ፍቅረየሱሰም ኳሱን ከመረብ አዋህዶታል ። ግቡ በተቆጠረበት አጋጣሚ ኳሱ መረቡን በጥሶ ወጥቶም ነበር ።
መልስ ለመስጠት ጥሩ ለመንቀሳቀስ የጣሩት ወልቂጤ ከተማዎቾ የአቻነቷን ግብ ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ማግኘት ችለዋል ። ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ውጪ በቀኝ አቅጣጫ ሆኖ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ያገኘው ጫላ ተሺታ በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል ። ከግቡ በኋላ ሀድያ ሆሳዕናዎች ቀደም ብሎ እንደነበረው ወደ ፊት በመሄድ እና ጫናዎችን በመፍጠር የሀድያ ሆሳዕናን የተከላካይ መስመር መፈትን ችለዋል ።
በ33ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ከተማው ሰይድ ሀብታሙ ኳስ ለማውጣት ሲሞክር የተሳሳተውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ ቢያገኘውም ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ያደረጉት ጥሩ የኳስ ቅበብል ለባዬ ገዛኸኝ ደርሶ አጥቂው በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎታል ። የመጀመሪያው አጋማሽ በሀድያ ሆሳዕና መሪነት ተጠናቀቀ ።
ቀዝቀዝ ብሎ በተጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ኳሱን ይዘው ለመጫወት ቢሞክሩም ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽሎ የመጣውን የወልቂጤ መከላከል በቀላሉ መስበር አልቻሉም ። ቀስ በቀስ በተለይም ከውሀ እረፍት በኋላ ወልቂጤ ከተማዎች የማጥቃት እንቅሰቃሴያቸውን በማጠናከር ቀደም ብሎ ከነበረው በተሻለ ወደ ፊት መድረስ ችለው ነበር ።
67ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከግራ መስመር የደረሰውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሱህ በግሩም ሁኔታ ኳሱን መልሶታል ። 73ኛ ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ከመሀል በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ለጌታነህ ከበደ ቢያቀብለውም የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ፈጥኖ የመታው ጌታነህ ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
89ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን በግራ መስመር ላይ በረጅም የደረሰውን ኳስ ወደ ወደ ግቡ ያቀበለው ኳስ የደረሰው ተቀይሮ የገባው አላዛር ዘውዱ የወልቂጤ ከተማን ሁለተኛ ግብ አስቆጠረ ። ጨዋታውም ፍፃሜውን 2 ለ 2 አድርጎ ሁለቱም ክለቦች አንድ አንድ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አድርጓቸዋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 16 ማድረስ የቻለ ሲሆን በደረጃው ላይ ግን ለውጥ አላሳየም በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 13 በማድረስ ደረጃውን ወደ 9ኛ አሻሽሏል ።