የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ሲደረግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን 2 – 1 በማሸነፍ ከተከታዩ ባህርዳር ከተማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል ።
በጨዋታው በሁለቱም ክለቦች በኩል በ21ኛው ሳምንት በነበራቸው ጨዋታ ላይ በተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሳያደርጉበት በዚህኛው ጨዋታም ተጠቅመዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው የጨዋታ ሂደት ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢታይም ወደ ግብ ቀርቦ የግብ ዕድሎች ከመፈጠር አንፃር ፈረሰኞቹ የተሻለ ጊዜን ማሳለፍ ችለው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመሀል ላይ ብልጫ ለመውሰድ ጥረቶችን ያደረጉበትም ነበር ። በፈረሰኞቹ በኩል በተለይም በመስመሮች በኩል በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በነበረ የመጀመሪያ የግብ ዕድል እስማኤል ኦሮ አጎሮ ከቢንያም በላይ የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ከደቂቃዎች በኋላ ከቢንያም በላይ እግር የተነሳውን የማዕዘን ምት ሄኖክ አዱኛ አግኝቶ ወደ ግቦ መሞከር ቢችልም የሄኖክ ሙከራ ጠንካራ አለመሆኑን ተከትሎ ጀማል ጣሰው በቀላሉ ይዞታል ።
ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ፊት ለመድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ውጤታማ አልነበሩም ።
በአጋማሹ የመጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ሳሙኤል አስፈሪ ከቀኝ መሰመር አሻግሮ አቤል ነጋሽ በግንባር ለመጠቀም የሞከረው ኳስ ከመከነበት አጋጣሚ ውጪ ወደ ሳጥን ለመግባት ተቸግረዋል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ መቀዛቀዞች የታዩበት ነበር ።
በተጀመረ በመጀመሪያ ደቂቃ ላይም አቤል ነጋሽ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከጌታነህ ከበደ የደረሰውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ወደ ፊት የመድረስ ጥረቶች ቢኖሩም ለግብ የቀረቡ የግብ ሙከራዎች ከማድረግ አንፃር ጠንካራ እንቅስቃሴ አልታየም ነበር ።
ጨዋታው 62ኛ ደቂቃ ሲደርስ ግን ኳስ እና መረብ ተገናኝተዋል ። አቤል ያለው ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ በተቃራኒ አቅጣጫ የነበረው ረመዳን ዩሱፍ በቀጥታ ወደ በመምታት ከመረብ አሳርፏል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አስማኤል ኦሮ አጎሮ የግብ መጠኑን 21 ያደረሰበትን ግብ አስቆጥሯል ።
በሁለት ደቂቃ ልዩነቶች ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት ፈረሰኞቹ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ኳሱን ይዘው በመጫወት የጨዋታውን ፍሰት ለመቆጣጠር ሲጥሩ ተስተውሏል ።
በነዚህ ደቂቃዎች ላይ ጫን ብለው በመጫወት በሚነጠቁ ኳሶች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የጣሩት ወልቂጤ ከተማዎች ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመጓዝ ተገደዋል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ82ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር ሳሙኤል ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ለቡድን አጋሮቹ በተገቢው መልኩ ሳያደርስ የቀረው ኳስ እና ከደቂቃ በኋላ ኦሮ አጎሮ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ሞክሮ የወጣበት ኳስ ምናልባትም የፈረሰኞቹን መሪነት ከፍ ማድረግ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ ።
በ89ኛው ደቂቃ ላይም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ የመሀል ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ጌታነህ ከበደ አግኝቶ ከመረብ አሳርፎታል ።
በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 – 1 በሆነ ውጤት ወልቂጤ ከተማን ረቷል ።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 3(ሐሙስ) ከ9:00 ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ መቻልን ሲገጥም በዕለቱ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ከገጣፎ ለገዳዲ ይጫወታል ።