የ2015 ዓ/ም የሴቶች የከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ እና የመጨረሻዉ ዙር ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተማ እየተካሄዱ የቆዩ ሲሆን በትላንትናዉ እለት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፍፃሜዉን አግኝቷል።
ከዋንጫው ጨዋታ በማስቀደም ከጠዋቱ 3:00 ሰአት ጀምሮ ለደረጃ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ የተጫወቱ ሲሆን ጨዋታዉን ሀምበሪቾ ዱራሜ 3-2 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ የ2015 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ዉድድርን የሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
ከሱ በማስከተል አስቀድሞ የ2015 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ዉድድር ሻምፒዮን መሆኑን ባረጋገጠዉ በሲዳማ ቡና እና በፋሲል ከነማ መካከል የመዝጊያ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ጨዋታዉ በሲዳማ ቡና 3-1 በሆነ ዉጤት ተጠናቆ ሲዳማ ቡና የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ መሆን ችሏል።እንዲሁም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የ2015 ዓ/ም የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ዉድድርን በሶስተኝነት ደረጃ በማጠናቀቅ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
የ2015 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሴቶች የከፍተኛ ሊግ የዉድድር ዘመንን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚዋ ማህሌት ምትኩ በ19 ጎል ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ስታጠናቅቅ የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ቡድን ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸረፋ ደሊቾ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ብዙዓየሁ ጀምበሩ ፣ የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃጎ አገኘዉ ፣ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ ፣ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ፣ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አቡሽ አሰፋ ፣ የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ በክብር እንግድነት በመገኘት ለአሸናፊ ቡድኖች የዋንጫ እና የሜዳልያ ሽልማት እንዲሁም ለተለያዩ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል።ከዋንጫው ስነስርዓት በኋላ የሻምፒዮኖቹ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አቡሽ አሰፋ እና የሴቶቹ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አቶ ፍፁም በርሄ አስተያየታቸዉን ለሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ ተሰጥተዋል ።
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ የሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ ፍፁም በርሄ “ቡድናችን ከተመሰረተ ገና ሁለት አመቱ ብቻ ቢሆንም በአጭር ግዜ ቆይታዉ ሻምፒዮን ሊሆን የቻለዉ በመጀመሪያ ደረጃ በፈጣሪ እገዛ ሲሆን ከእሱ በማስከተል ሁላችንም ተስማምተን እና ተናበን እንዲሁም ጠንክረን መስራት በመቻላችን ለዚህ ስኬት ልንበቃ ችለናል በማለት አስተያየቱን የሰጠ ሲሆን እንዲሁም በቀጣይነተም በፕሪሚየር ሊጉ ዉስጥ አዳዲስ እና ጠንካራ ልጆችን በክለባችን ዉስጥ ጨምረን ይሄን ጠንካራነታችንን ለመድገም እንሞክራለን በማለት የክለቡ የቦርድ አመራሮች ፣ ስራ አስኪያጁ ፣ የደጋፊ ማህበሩ ፣ ደጋፊዎችን ፣ የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፣ የኮቺንግ ስታፉ እንዲሁም የክለባችንን ተጫዋቾችን ማመስገን እፈልጋለሁ ብሎ አስተያየቱን ቋጭቷል”
ከእሱ በማስከተል የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አቡሽ አሰፋ “የ2015 ዓ/ም የዉድድር ዘመንን ስንጀምር ሻምፒዮን ለመሆን አቅደን ነበር ያን ደግሞ አሳክተናል በቀጣይ በፕሪሚየር ሊጉ ዉስጥ በዚህ አሸናፊነታችን ለመቀጠል ከሌሎች ክለቦች ወደ ስብስባችን የምንጨምራቸዉ ልጆች አሉ ያለ ሲሆን ይሄ የሴቶቹ ቡድን እንደ አንድ ሆኖ በመቀጠሉ ሻምፒዮን ሊሆን ችሏል ያለ ሲሆን የክለቡ ማኔጅመን በሚያስፈልገዉ ነገር በሙሉ ከጎናቸዉ እንደነበረ ገልፆልን ለዚህ ስኬት የኮቺንግ ስታፉ ሚና ትልቅ መሆኑን በመግለፅ አመስግኗቸዉ ቆይታችንን አጠናቀናል”