የሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ በሆነዉ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀሪ የ22ተኛ ሳምንት ጨዋታ በሮዱዋ ደርቢ ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ከተማን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በውጤት ደረጃ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ በነበረዉ የዕለቱ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና በጥሩ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና በቀኝ በኩል ባዘነበለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ እና ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲልኩም ተስተውሏል።
በዚህም ቨ16ተኛዉ ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ በሲዳማ የቀኝ ማጥቃት በኩል የተገኘዉን ኳስ ፍሬዉ ሰለሞን ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥታለች። በ19ነኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ከተመሳሳይ ቦታ የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ ፍሬዉ ወደ ሳጥን አሻምቶ ደስታ ደሙ በጭንቅላቱ ኳሷን ወደ ግብ ልኮ የነበረ ቢሆንም በተመሳሳይ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታበታለች።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በመጠኑም ቢሆን ብልጫ የተወሰደባቸዉ እና አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃቱ አደጋ ሊፈጥሩ ሲጥሩ የነበሩት ሀይቆቹ 24ተኛዉ ደቂቃ ላይ ጥሩ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም በጥሩ ሩጫ ከኤፍሬም አሻሞ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ ወደ ሲዳማ ግብ ክልል መድሀኔ ብርሀኔ የላካትን ኳስ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በቀላሉ ተቆጣጥሯታል። በተቃራኒዉ በ29ነኛዉ ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ይገዙ እንዲሁም ዳንኤል ዕድላቸዉን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
አሁንም የበላይነታቸዉን አጠናክረዉ የቀጠሉት ሲዳማዎች በ36ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ የሲዳማ ቡናዉ የመሐል ሜዳ ሞተር ፍሬዉ ሰለሞን ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በአቤኔዘር ተተክቶ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።
የመጀመሪያዉ አጋማሸ ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ አሊ ሱለይማን ኳሷን በፍጥነት እየገፋ በግራ በኩል ለሚገኘዉ ኤፍሬም አሻሞ አቀብሎት ተጫዋቹ በቀጥታ ስጥን ውስጥ ከገባ በኋላ ለአጥቂዉ ሙጅብ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ መክብብ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሶን መልሷታል።
በተጨማሪም የመጀመሪያ አጋማሽ ተገባዶ በጭማሪ ሰዓትም አቤል እንዳለ ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ቢችል ሳይሳካ ቀርቶ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ብልጫቸዉን ያስቀጠሉት ሲዳማዎች ከአንድ ሁለት ድንቅ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በኋላ በ63ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከሲዳማ ቡና የቀኝ ማጥቃት በኩል እንዳለ ከበደ ያሻማዉን ኳስ አጥቂዉ ፍሊፕ አጃህ በግንባሩ በመግጨት ግብ ማሰልጠኛ ማስቆጠር ችሏል።
በሲዳማ ቡና የተወሰደባቸውን ብልጫ መቋቋም ያልቻሉትን እና የኋላ የኋላ ግብ ያስተናገዱት ሀይቆቹ በመስመር አጥቂዉ አሊ ሱለይማን እና አጥቂዉ ሙጅብ ቃሲም እንዲሁም ኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ዕቅዳቸዉ ሰምሮ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጫናቸዉን አሁንም አጠናክረዉ የቀጠሉት ሲዳማዎች በግቡ ባለቤት ፍሊፕ አጃህ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል። ዉጤቱን ተከትሎም ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 24 ከፍ አድርጎ አስራ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፤ በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማ በ31 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።