መቻል ፋሲል ከነማን በጠባብ ዉጤት አሸንፏል !
በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማን 2ለ1 ካሸነፉ በኋላ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ጨዋታ ምክንያት ሁለት ያህል የሊጉን ጨዋታዎች ማከናወን ያልቻሉት ፋሲሎች በተቃራኒው ከሶስት የሊግ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በማሸነፍ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን ተሸንፈዉ በሰንጠረዡ ከወገብ በታች ተቀምጠዉ ከነበሩት መቻሎች ጋር ያደረጉት ጨዋታ በመቻል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተመጣጣኝ ፍክክር የጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ እምብዛም ሙከራ ባይታይበትም ሁለቱም ክለቦች ወደ ሶስተኛዉ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ያደርጉት የነበረዉ እንቅስቃሴ በጥሩ ጎኑ ተጠቃሽ ነበር ማለት ይቻላል። ጨዋታዉ ገና በ3ኛዉ ደቂቃ ላይም ድንቅ ሙከራን አስመልክቶናል። በዚህም ከተከላካይ ክፍሉ የተሻገረለትን ኳስ አማካዩ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከርቀት አክሮሮ ወደ ግብ ቢሞክርም ለጥቂት ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታበታለች።
- ማሰታውቂያ -
በ24ኛዉ ደቂቃ ደግሞ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ከአለም ብርሐን የተገኘዉን ኳስ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ሲያሻማዉ ተከላካዮች በሚመልሱበት ሰዓት በአቅራቢያው ይገኝ የነበረዉ ታፈሰ ሰለሞን ኳሷን ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ዳግም እንደምንም አዉጥቷታል። በ32ኛዉ ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በኩል ወንድማገኝ ማርቆስ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት ሳሙኤል ሳሊሶ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በግብ ዘቡ ሚካኤል ሳማኬ አማካኝነት ግብ ከመሆን ከሽፋለች።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት መቻሎች በተደጋጋሚ ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል መድረስ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብን ለማዋሀድ ግን ያን ያህል ስል ነበሩ ማለት አይቻልም። በተመሳሳይ በጨዋታዉ እንደወትሮዉ በሀያልነታቸዉ ላይ ያልነበሩት ፋሲል ከነማዎች አልፎ አልፎ በረጃጅም እና በመስመር ላይ ኳሶች አንዳች ነገርን ለመፍጠር ቢጥሩም ያን ያህል ዉጤታማ ነበሩ ማለት አይቻልም። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑ ተሻሽለዉ የተመለሱት መከላከያዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብም ማግኘት ችለዋል። በዚህም በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባዉ እስራኤል መስፍን ከአማካዩ ከንዓን ማርክነህ የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥኑ ዉጭ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በድጋሚ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም መቻሎች መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የሚችሉበትን እድል አግኝተዉ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህም በ53ኛዉ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ በረከት ደስታ እየገፉ የአፄዎቹ የግብ ክልል ደርሶ ራሱ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወጥታለች።
በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ በማስገባት የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ተጭነዉ መጫወት የጀመሩት ፋሲሎች ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብን ግን ማዋሀድ ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም የአራተኛው ሳምንት የአራተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በመቻል የ1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።