በሊጉ የአራተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀኝ ውሎ 10 ሰዓት ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለገጣፎ ለገዳዲን 3 ለ 0 ረቷል ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሶስተኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ ምንያህል ተሾመን እና ሄኖክ አየለን በሙሴ ከበላ እና አላዛር ሽመልስ ምትክ ያሰለፉ ሲሆን በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል በሳምንቱ በኢትዮጵያ መድኅን በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ አራት ለውጦችን በማድረግ በወንድወሰን ገረመው ፤ አቤል አየለ ፤ ዳዊት ቀለመወርቅ እና ተፈራ አንለይ ምትክ በሽር ደሊል ፤ አስናቀ ተስፋዬ ፤ ታምራት አየለ እና አማኑኤልን አረቦን አሰልፈዋል ።
ሁለቱን አዳጊ ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የተጀመረ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻለ በመንቀሳቀስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አስመልክቶናል ።
- ማሰታውቂያ -
በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል ደግሞ በተወሰደባቸው የጨዋታ ብልጫ መነሻ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በረጃጅም እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሂደቶች ጥቃት ለመሰንዘር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ 2ኛው ደቂቃ ላይ አብነት ደምሴ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ የለገጣፎ ለገዳዲው ግብ ጠባቂ በሽር ደሊል በቀላሉ ይዞታል ።
በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል ደግሞ በ10ኛው ደቂቃ ላይ በረጅም የተላከን ኳስ አማኑኤል አረቦ በቀጥታ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም በተመሳሳይ በቀላሉ በግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ተይዞበታል ።
በጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በማጥቃት ሂደት የተሻሉ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል ደጋግመው በመፈተን ገና በመጀመሪያ አጋማሽም ሶስት ያህል ግቦችን ለማስቆጠር ችለዋል ።
ቀዳሚው ግብ በ22ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረ ሲሆን ሄኖክ አየለ ከተስፋዬ በቀለ በረጅም የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ እየገፋ በመሄድ ቡድኑን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ፀጋ ደርቤ በሳጥን ውስጥ በመዝገቡ ቶላ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አየለ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ነገር ግን የግብ ዕድሎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአብነት ደምሴ የ30ኛ ደቂቃ ድንቅ ግብ መሪነታቸውን ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርገዋል ። ስንታየሁ ወለጬ በመዝገቡ ቶላ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት አማካዩ አብነት ደምሴ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮ አስደናቂ ግብ አስቆጥሯል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ ሁለት ደቂቃዎች በፊትም የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናው ቡድን ሶስተኛ ግቡን በምንያህል ተሾመ አማካኝነት አስቆጥሯል ። ፀጋ ደርቤ በራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ሲያሻግር በበረከት ተሰማ በግንባር ተገጭቶ ያገኘው የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ምንያህል ተሾመ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ለገጣፎ ለገዳዲዎች የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጠንከር ጠንከር ያሉ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል ።
በ51ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ በረከት ተሰማ ከቅጣት በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ዘሪሁን ታደለ አድኖታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው መሀመድ አበራ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ድንቅ የግቅ ሙከራ በአጋማሹ ምርጥ ብቃቱን ባሳየው ዘሪሁን ታደለ ግብ ከመሆን ድኗል ።
በሶስት ግብ ልዩነት በመምራት ላይ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ቀስ በቀስ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ኳሱን በእግራቸው ስር በማቆየት ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ሲጥሩ ተስተውሏል ።
ለገጣፎ ለገዳዲዎች በተለይም ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ የግብ ሙከራዎች ቢያንስ የግቡን መጠን ለመቀነስ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ፍሬያማ መሆን የቻለ አልነበረም ። በ70ኛው ደቂቃ በተፈራ አንለይ ያደረጉት የግብ ሙከራም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በ73ኛው ደቂቃ በምንያህል ተሾመ እንዲሁም 82ኛው ደቂቃ ላይ በሄኖክ አየለ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው በሽር ተይዘዋሎ ።
በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ የ3 ለ 0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በአምሰትኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ጥቅምት 14(ሰኞ) 10:00 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ከተማን ሲገጥም ጥቅምት 16(ረቡዕ) 7:00 ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ ባህርዳር ከተማን የሚጫወት ይሆናል ።