በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታ ቀን 7 ሰዓት ላይ የተገናኙት ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ጨዋታቸዉን 1 አቻ በሆነ ዉጤት አጠናቀዋል።
በሁለተኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸዉ ግብ ሽንፈትን ያስተናገዱት ኢትዮ ኤሌትሪኮች የመጀመሪያ ነጥባቸዉን ለማሳካት ወሳኝ በነበረዉ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለዉ ተመልክተናል። በተቃራኒው የአሰልጣኝ ፀጋየ ኪዳነማርያሙ ወላይታ ድቻ በመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ ግብ ለማስቆጠር ሲጦሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም በጨዋታዉ መጀመሪያ የኢትዮ ኤሌትሪኮችን መሳሳት ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ የመስመር ተጫዋቹ ቃልኪዳን ዘላለም ሞክሮ የነበረዉ ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ሲሆን በድጋሚ በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በረከት ወልደዮሐንስ ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ችሏል።
በጨዋታው ኳሱን መቆጣጠር ቢችሉም ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ኤሌትሪኮች በተቃራኒው በ19 ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮባቸዋል በዚህም ጌቱ ሀይለማርያም ቃልኪዳን ዘላለም ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቃል ኪዳን አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ኤሌትሪኮች ግብ ካስተናገዱ በኋላ በቶሎ ወደ ጨዋታዉ ገብተዉ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የተገኘዉን ቅጣት ምት ፀጋ ደርቤ ሲያሻማዉ አማካዩ አብነት ደምሴ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ እረፍት ከመዉጣታቸዉ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ በመሆንም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ተሽለዉ የገቡት ዲቻዎች በተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉም ተስተውሏል። በዚህም በተለይ በ46ኛዉ ደቂቃ ላይ የፊት መስመር አጥቂዉ ስንታየሁ መንግስቱ ከርቀት አክርሮ ሞክሮ የነበረ ሲሆን ግብ ጠባቂዉ ተቆጣጥሮታል። በተጨማሪም ከደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ አጥቂው ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የበላይነታቸዉ ተቀዛቅዞ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸው ኤሌትሪኮች መልስ ለመስጠት አልፎ አልፎ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ያን ያህል ተሳክቶላቸዋል ለማለት አያስደፍርም።
አሁንም ማጥቃታቸዉን የቀጠሉት ዲቻወች በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ የቸገኘዉን ቅጣት ምት በእንድሪስ ሰይድ አማካኝነት ምክረዉ የነበረ ቢሆንም ኤሌትሪኮች እንደምንም አዉጥተዉታል። በቀሪ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ ሊያደርጋቸዉ የሚችለዉን ግብ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸዉ ቀርቶ ጨዋታዉ በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።
በቀጣይም ወላይታ ድቻ ከመድን ጋር ሲገናኙ በተመሳሳይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአራተኛዉ ሳምንት ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።