በሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ከፍተኛ ቅጣት የተላለፈባቸው የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ አሳውቋል።
በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አንድ ይግባኝ ጠያቂ ውሳኔው በደረሰው ሶስት ቀናት ውስጥ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ማሳወቅ የሚጠበቅበት ሲሆን በሰባት ቀን ውስጥ ደግሞ ይግባኙን ማስገባት አለበት የሚል በመሆኑ አሰልጣኝ ገብረ መድህን እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ ይግባኝ እንደሚጠይቅ በመግለጽ በህጉ መሠረት ሶስት ቀናት ሳይሞላው ደብዳቤ ማስገባቱ ታውቋል።
አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኢትዮጵያ መድን በሲዳማ ቡና 1ለ0 በተሸነፈበት ጨዋታ በመሃል ዳኛው በአምላክ ተሰማ በቀይካርድ የተባረረ ሲሆን የጨዋታውን
መጠናቀቅ ተከትሎ በሚዲያ 14 ለ11 ሆነን እንዴት እናሸንፋለን በማለት ዳኞቹን የተቸበትን መግለጫ የሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ መርምሮ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት አሰልጣኙን ባዩት ቀይካርድ 3 ጨዋታና 10 ሺህ ብር ሲቀጣ ከጨዋታው በኋላ ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ የጨዋታ አመራሮች አሰራርን ያለ አግባብ የተቸና ስሜታቸውን የጎዳ አስተያየት መስጠታቸው ሪፖርት በመቅረቡ 3 ወር ከአሰልጣኝነት አግዶ የተጨማሪ የ10 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ግን ውሳኔውን በመቃወም ይግባኛቸውን እንደሚያስገቡ ለፌዴሬሽኑ ባስገቡት ደብዳቤ አረጋግጠዋል… “በመጀመሪያ ቢጫ ካርድ የተመዘዘብኝ ለሲዳማ ቡና ቅጣት ምት የተሰጠበት ቦታ ልክ አይደለም በማለቴ ሲሆን ቀይካርዱ ደግሞ አርቢትር በአምላክ ተሰማ ዝምበል ሲለኝ እኔንም ተጨዋቾቼን አታስፈራራን እንጂ ብዬ በመጠየቄ ያያሁት ካርድ ነው ከዚያ ውጪ አስፀያፊና የዳኞቹን ክብር የሚነካ ነገር አልተናገርኩም”በሚል ውሳኔውን እንደማይቀበሉት መናገራቸው ታውቋል።
አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ይግባኝን ተንተርሶ የፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚሰጠው ብይን የሚጠበቅ ሆኗል።