በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሀያ አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት ጨዋታ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታቸዉን አንድ አቻ በሆነ ውጤት አገባደዋል።
ባሳለፍነዉ ሳምንት የ23ተኛዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር በመቻል ሽንፈት አስተናግዶ የነበረዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚገኘዉ ሀዋሳ ከተማ ባደረጉት የዕለቱ ጨዋታም ባለሜዳዉ ቡድን ሀዋሳ ከተማ በአብዝሀኛዉ የጨዋታ ደቂቃ በመከላከል ላይ ትኩረት ባደረገ የጨዋታ መንገድ በተለይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ከመርሐግብሩ አንዳች ነገር ለመፍጠር ሲሞክር ፤ በተቃራኒው የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳዉን የመሐል ላይ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና የፊት መስመር አጥቂዉን አጎሮ ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን ወደ ሳጥኑ በማድረስ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩም ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለበች ጨዋታም ጨዋታዉ የመጀመሪያ አጋማሽ አጋማሽ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል የመስመር አጥቂዉ እዮብ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረዉ እና በተመሳሳይ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ይሄዉ ተጫዋች የፈረሰኞቹ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦበት የነበረዉ አጋጣሚ በሀይቆቹ በኩል የተደረገ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በተቃራኒው የሀይቆቹን የተከላካይ መስመር ጥሰዉ ወደ ሶስተኛዉ የሜዳ ክፍል ለመሻገር ሲቸገሩ የነበሩት ፈረሰኞቹ በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ አጥቂዉ አጎሮ ከርቀት በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የግብ ዘቡ መሐመድ ሙንታሪ ያወጣበት አጋጣሚ በአጋማሹ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የተደረገች ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች ።
ከዕረፍት መልስ ወዲያውኑ ፈረሰኞቹ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም በ46ተኛዉ ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ የመስመር አጥቂዉ ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ በመግጨት ግብ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ከግብ ጠባቂዉ መሐመድ ሙንታሪ ጋር የተጋጨዉ ቸርነት ጉግሳ በዚያው ቅፅበት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል።
ገና በአጋማሹ መጀመሪያ ላይ ግብ ያስተናገዱት ሀይቆቹ በርከቱ ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ቀይረዉ በማስገባት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲያደርጉት የነበረዉ ጥረት ፍሬ አፍርቶ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ፍሪፕሞንግ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ተባረክ ሄፋሞ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ጫና ፈጥረዉ መጫወት የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ያሻማዉን የቅጣት ምት ኳስ የመስመር ተጫዋቹ ተገኑ ተሾመ በግንባሩ በመግጨት ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ መሐመድ ሙንታሪ እንደምንም ኳሷን ተቆጣጥሯታል። ዉጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ52 ነጥብ በመሪነት ስፍራዉ ላይ ሲቀመጥ ፤ በተቃራኒው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በ32 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።