ሲዳማ ቡና በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን መቻልን 1 – 0 በማሸነፍ አስመዝግቧል ።
ሲዳማ ቡናዎች በ23ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ መድኅንን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በሙሉቀን አዲሱ ምትክ አበባየሁ ሀጂሶን ሲያሰልፉ በመቻል በኩል በሳምንቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
የ24ኛው ሳምንታት የመጨረሻ መርሀግብር የነበረው ይህ ጨዋታ ወድድድሩ በሀዋሳ መካሃድ ከጀመረበት ቀን አንስቶ በርካታ ደጋፊዎች ስታድየም ገብተው የተከታተሉት ጨዋታ ሆኗል ።
- ማሰታውቂያ -
በዚህም በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ፊት የተጫወቱት እና ውድድሩ ወደ ሀዋሳ ከመጣ በኋላ ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገቡት ሲዳማ ቡናዎች በጥሩ መነቃቃት ሆነው ጨዋታውን ጀምረዋል ። በመጀመሪያው አጋማሽም ከተጋጣሚያቸው መቻህ በተሻለ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠሩ ጥረቶችን አድርገዋል ።
በመቻል በኩል ኳስን ከኋላ መስርተው ለመውጣት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እምብዛም ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል ።
ወደ መቻል የግብ ክልል ቶለ ቶሎ ሲደርሱ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በ33ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ሲዳማ ቡና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ 1 – 0 ሲያሸንፍ የማሸነፊያ ግቦችን ያስቆጠረው ፊሊፕ አጄህ በዚህ ጨዋታም ስሙን በግብ አስቆጣሪነት ላይ አስመዝግቧል ።
ተጫዋቹ ግቡን በግንባር ገጭቶ ኳሱን አመቻችቶ ያቀበለው ደግሞ ይገዙ ቦጋለ ነው ።
ሲዳማ ቡናዎች ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላም መሪነታቸውን ከፍ ሊያደርግ የሚችል የግብ ሙከራ በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት አድርገው በግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ ግብ ከመሆን ድኗል ።
በአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይም ሲዳማ ቡናዎች ሌላ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ምንተስኖት አዳነ ኳሱን ከመስመር ላይ አውጥቶታል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ መቻሎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ የቻሉበት ነበር ።
የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን በአጋማሹ በተጋጣሚው ላይ ብልጫ ወስዶ ለመጫወት ቢችልም ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ደርሰው ጠንካራ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ቆይተዋል ።
በሲዳማ ቡና በኩል በተወሰደባቸው ብልጫ አብዛኛውን የአጋማሹን ክፍለ ጊዜ በሜዳቸው ላይ ሆነው ለማሳለፍ የተገደዱ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች የግብ አጋጣሚዎች ለመፍጠር ሞክረዋል ።
በመጨረሻም ሲዳማ ቡና በአጄህ ግብ 1 – 0 አሸንፏል ።
በ25ኛው ሳምንት ጨዋታዎችም በመጪው ግንቦት 14(ሰኞ) በ9:00 ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከነማ ሲጫወት በተከታዩ ቀን ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ መቻል ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማል ።