*ሁለቱ የአካውነት ቁጥሮች
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000544405617
በንብ ባንክ ደግሞ 7000043195037
ነው ተብሏል
“ለብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ወርሃዊ ደመወዝ 1500 ለምክትሉ ደግሞ 1200 ይከፈለን ነበር. በዚህ ምን ታጠራቅማለህ…?”
ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው
ለአሠልጣኝ አስራት ኃይሌ ህክምና የተቋቋመው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ዛሬ በራስ ሆቴል አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ስራውን በይፋ ጀምሯል።
ኮሚቴው ወደ 13 አባላት ያሉትና በአሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የሚመራ ሲሆን ሁለት አካውንት በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በአቶ ጌታዘሩና አቶ ሰለሞን በቀለ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በንብ ባንክ መከፈቱ ተገልጿል በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000544405617 በንብ ባንክ ደግሞ 7000043195037 መሆኑን አውቆ ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረበው ኮሚቴው ህብረተሰቡ ከሁለቱ አካውንት ውጪ እንዳይጠቀም ጠይቋል።
- ማሰታውቂያ -
“እግርኳስ ሲጠራ በቀዳሚነት የሚጠራ ሰው ነው
በክለብም ሆነ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሀገሩን ያገለገለው ይኸው ባለሙያ አሁን ላይ ታሟል እሱን ለማዳን የምንችለውን እያደረግን ነው” ያለው ኮሚቴው “አሰልጣኝ አስራት በጭንቅላቱ ግራ የኋሏ ክፍል እጢ በመገኘቱ ግራ ጆሮው አይሰማም ቀኙ የሚሰማው በማዳመጫ እየታገዘ ነው ቶሎ ካልታከመ ለጤናው ስለሚያሰጋው ቶሎ ኦፕራሲዮን መደረግ አለበት በተለይ ተጨዋቾች አሰልጣኞኝ ቡድኖች የስፖርት ቤተሰቡ እንዲሁም የሰራባቸው ክለቦች በአስቸኳይ ድጋፍ አድርገው አሰልጣኝ አስራት ህክምናውን እንዲከታተል መደረግ አለበት ድጋፍ አድራጊ ወገኖቻችንም ይህን ታሳቢ አድርገው ድጋፋቸውን እንዲሰጡ እንጠይቃለን”ብሏል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እንደተናገሩት “ከመጀመሪያው ጀምሮ የኢትዮጵያን እግር ኳስ አገልግለናል በተጨዋችነት ክለቦቻችንና ብሄራዊ ቡድኑንም አገልግሏል የሱ ምክትል ሆኜ ሁለት የሴካፋ ዋንጫ አግኝተናል በወቅቱ ለብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ወርሃዊ ደመወዝ 1500 ለምክትሉ ደግሞ 1200 ይከፈለን ነበር. በዚህ ምን ታጠራቅማለህ…? ስለዚህ ነው የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ የጠየቅነው ህዘቡን አስጨፍሯል አስደስቷል የህዝቡን አንድነት አስጠብቋል
ያ ውለታው መመለስ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚቴው እንዳብራራው “አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ተደግፈው መጥተው ለእኛ ኮሚቴ እውቅና ሰጥተዋል እስካሁንም የገባው ብር ወደዚህ ኮሚቴ አካውንት እንደሚዞር ተስማምተናል ከኢትዮጵያ ውጪ የተከፈተው ጎፈንድሚ በልጁ የተከፈተ ነው በዚህ ላይ መረጃ እንለዋወጣለን የሀገር ውስጥ ግን በዚህ ኮሚቴ ስር ብቻ ይሆናል አሰልጣኝ አስራትን ለመርዳት የቃል የገቡ ወገኖች አሉ ቃል መግባትን ትርጉም የምንሰጠው በእኛ አካውንት ብሩ ሲገባ ነው” ሲል አስረድቷል።
ኮሚቴው በሰጠው በዚሁ መግለጫ “የአውሮፕላን የደረሰ መልስ ቲኬት ወጪ የህክምና ክትትልና ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር ለኦፕራሲዮኑ ብቻ ከ35 ሺህ ዶላር በላይ ተጠይቋል ቱርክ ህንድና ታይላንድ እየተሞከረ ነው ከጊዜ ከገንዘቡና ከጥሩ ህክምና አንፃር የትኛው የተሻለ ነው የሚለውን ቶሎ ወስነን ህክምናውን እንዲከታተል እናደርጋለን” በማለት ኮሚቴው መግለጫውን ሰጥቷል።
በራስ ሆቴል በነበረው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ተጨዋቾች ማህበር 2 ሺህ ዶላር ለመስጠት መወሰኑም ይፋ ሆኗል።