በሊጉ የ24ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን መርሀግብር ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኅን ድሬዳዋ ከተማን 3 – 0 አሸንፏል ።
በጨዋታው በኢትዮጵያ መድኅን በኩል በ23ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ፀጋሰው ድማሙ ፣ አብዱልከሪም መሀመድን እና ተካልኝ ደጀኔን በያሬድ ካሳዬ ፣ ቻላቸው መንበሩ እና ቴዎድሮስ በቀለ ተክተው ገብተዋል ። በድሬዳዋ ከተማ በኩል በሳምንቱ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ አንድ ቅያሪዎ በማድረግ በጋዲሳ መብራቴ ምትክ ሙኸዲን ሙሳን አሰልፈዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ መድኅኖች ብለጫ ወስደው መጫወት የቻሉበት የተሻለ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩበት ግቦችንም ማስቆጠር የቻሉበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በአንፃሩ በድሬዳዋ ከተማ በኩል በተወሰደባቸው ብልጫ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ የተገደዱ ሲሆን እግራቸው ስር የሚገቡ ኳሶችን በረጅም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለማድረስ ቢጥሩም ስኬታማ ጊዜን አላሰለፉም ።
በአጋማሹ ቀዳሚ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ሲመዘገብ ሀቢብ ከማል ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ ተመልሷል ።
ከዚህኛው ሙከራ ዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ኢትዮጵያ መድኅኖች መሪ የሆነበት ግብ አስቆጥረዋል ። ወገኔ ገዛኸኝ ከባሲሩ ኡመር የደረሰውን ኳስ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ሆኖ በመቀበል ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
እንደ አጀማመሩ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ የቀጠለው ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይም ሌላ ግብ ሲያስተናግድ ኢትዮጵያ መድኅን እና ወገኔ ገዛኸኝ በግቡ ላይ ስማቸዉን አስፍረዋል ።
የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ ቀለል አድርጎ ወደ ግብ የመታው ኳስ በዳንኤል ተሾመ መረብ ላይ በድጋሚ አርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በኢትዮጵያ መድኅን የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በጨዋታው የሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ድሬዳዋ ከተማዎች ጥሩ መነቃቃትን በማሳየት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን አድርገዋል ። ነገር ግን ለግብ የቀረበ እና ኡቡበከር ኑሪን የፈተነ የግብ ሙከራ በማድረግ ረገድ ደክመው ታይተዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ምክንያት በተረጋጋ መንፍስ ጨዋታውን በማድረግ ላይ የነበሩት ኢትዮጵያ መደኅኖች በ66ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል ።
የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር አመቻችቶ ያቀበለው ባሲሩ ኡመር ከመስመር ያሻገረውን ኳስ በግንባር ተገጭቶ በዳንኤል ተሾመ የተመለሰውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ 3ኛው ግብ ከመረብ አሳርፏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ቀደም ብሎ ከነበራቸው በተሻለ ወደ ፊት ለመድረስ የቻሉበት ነበር ። ነገር ግን የጠራ የግብ ሙከራ ከመፍጠር አንፃር አሁንም ድሬዳዋ ከተማዎች ተቸግረው ቆይተዋል ።
የመጨረሻ ደቂቃዎች የድሬዳዋ ከተማዎች ጥረቶች ሳይሳኩ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድኅን የ3 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ25ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 14(ሰኞ) ከ12:00 ጀምሮ ድሬዳዋ ከተማ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ከ9:00 ጀምሮ ኢትዮጵያ መድኅን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታሉ ።